ባሐራት

0
127

በዓለማችን በሕዝብ ብዛት አንደኛ፣ በቆዳ ስፋቷ ደግሞ ሰባተኛ የሆነችውን ሕንድ  በሽርሽራችን ልናስጎበኛችሁ ወደናል! የሕንድ ዋና ከተማ ኒው ዴልሂ ስትሆን ትልቋ የንግድ እና የሌሎች እንቅስቃሴዎች መነሀሪያዋ ሙምባይ ወይም በሀገሬው አጠራር ቦምቤይ ናት::

ሀገሪቱ በሦስት የተለያዩ ስሞች ትጠራለች፡- ሕንድ፣ ባሐራት እና ሂንዱስታን በመባል:: እነዚህ ስሞች እንደየሁኔታው እና እንደየ ቋንቋው ይወሰናሉ:: እንደአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2009 በታተመው ኦክስፎርድ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ኢንዲያ (ሕንድ) የሚለው ቃል ከጥንት ላቲን ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን ደቡብ እስያ የሚል ፍች እንዳለው አስቀምጧል:: ሳንስክሪት በተሰኘው የጥንት ሕንዶች (ኢንዶ አርያንስ) ቋንቋ በደቡብ የሚገኘውን የኢንደስ ወንዝ የሚገልጽ መሆኑን ያሳያል:: ባሐራት እና ሂንዱስታን የተሰኙት መጠሪያዎች ደግሞ የሰሜኑን ክፍል የሚገልጹ ናቸው::

የስነ ምድር ጥናት እንደሚያመለክተው ሆሞ ሳፒያንስ የተሰኘው  አሁን ላለነው የሰው ልጆች ተቀራራቢ ነው የሚባለው ሰው መኖር የጀመረው ከ55 ሺህ ዓመታት በፊት ነው:: ይህ ሰው ከ30 ሺህ ዓመታት በፊት ደግሞ ከአፍሪካ ወጥቶ ወደ ደቡብ እስያ ማቅናቱን እና ቅሪቶች መገኘታቸውን የስነ መሬት ጥናቶች ያመላክታሉ:: ከክርስቶስ ልደት በፊት በ6500 ዓ.ዓ እንስሳትን የማርባት እና ሰብሎችን የመዝራት እንቅስቃሴ በአሁኗ ፓኪስታን (እ.አ.አ ከ1947 በፊት ፓኪስታን  የሕንድ አካል ነበረች)  እንደነበር መረጃዎች አሳይተዋል:: ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሕንድ ስልጣኔ ሲነሳ እና ሲወድቅ እንዲሁም የተለያዩ ሥረወ መንግሥታት ሲፈራረቁባት ቆይተዋል::

በተለይ የመካከለኛው ዘመን ተብሎ በሚጠራው ማለትም ከስድስተኛው ክፍለ  ዘመን እስከ 16ኛ ክፍለ ዘመን የውስጥ መስፋፋቶች እና የርስ በርስ ሽኩቻዎች ነበሩ:: በዚህ ዘመን አያሌ ቤተ መንግሥቶች፣ የሂንዱ እና የኢስላም ቤተ አምልኮ፣ ኃውልቶች እና ሌሎች ቅርሶች ታንጸዋል::

ሕንድ በ1757 እ.አ.አ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር ወድቃለች:: ይህም ደግሞ ውስጣዊ አንድነቷ በተለያዩ ሽኩቻዎች በመናዱ እና በሃይማኖት እና በዘር የሚነሱ ግጭቶች እየተካረሩ መጨረሻ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ነው:: ይህ የተበጣጠሰ ውስጣዊ አንድነት እስከ አውሮፓዊያኑ ዘመን ቀመር 1957 ማለትም ለ190 ዓመታት በቅኝ ግዛት እንድትማቅቅ እና ዜጎቿ ለከፋ ረሀብ እንዲጋለጡ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቷ ያለቅጥ እንዲታለብ አድርጓል:: በመጨረሻም ከሁለት ተከፍላ ፓኪስታን በእንግሊዝ ሴራ ከእናት ሀገሯ እንድትገነጠል እና ራሷን የቻለች ትንሽ ሀገር እንድትሆን አድርጓል:: ለሕንድ ነጻ መውጣት የመሀተመ ጋንዲ ሰላማዊ ትግል አስተዋጽኦ ማድረጉን ብዙዎች ይገልጻሉ::

የሕንድ ህዝብ ብዛት ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን በላይ ሆኗል:: በሀገሪቱ ከሁለት ሺህ በላይ ጎሳዎች አሉ:: ከእነዚህ ውስጥ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚዎቹ ኢንዶ ዩሮፒያንስ (ከአውሮፓዊያን ጋር የተዳቀሉ)፣ ኢንዶ አርያንስ (ከፐርሻዊያን አሁን ኢራን ዝርያዎች ጋር የተዳቀሉ)፣  ሂንዱስታኒ፣ ቤንጋሊ፣ ማራቲ፣ ፑንጃቢ፣ ካሽሚሪ እና ሌሎች ጎሳዎች ይጠቀሳሉ:: በሕንድ 79 ከመቶ የሂንዱይዝም፣ 14 ከመቶ የኢስላም፣ 2 ከመቶ የክርስትና፣ አንድ ከመቶ የሲክ  እንዲሁም ሌሎች አያሌ የሃይማኖት ተከታዮች አሉ:: በሂንዱይዝም እምነት ሰው ከሞተ በኋላ  ሬሳው ይቃጠላል:: ይህ ሰውነት ከሞተ በኋላ ምንም ጥቅም የለውም፤ ይልቁንም ሰውነቱን ማቃጠል ነብሱ ዳግም ወደ ሌላ ሰውነት ገብታ የሞተው ሰው ዳግም በሌላ ሰውነት እንዲፈጠር ያግዘዋል ብለው ያምነናሉ::

የሕንድ ጠቅላላ ቆዳ ስፋት ሦስት ነጥብ ሦስት ሚሊየን ስኩየር ካሬ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፤ ይህም የዓለማችን ሰባተኛዋ ትልቅ ሀገር ያደርጋታል:: ሀገሪቷ ከ7500 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት እና ከ5400 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ያለው የባሕር ዳርቻ ያለው የባሕር በር አላት:: ታላቁ የሂማሊያ ተራራ እና የታር ምድረ በዳ ሕንድ ከሌሎች ሀገራት ጋር የምትጋራቸው ሥፍራዎች ናቸው:: የሕንድ የአየር ሁኔታ በሁለቱ አካባቢዎች ጸባይ የሚወሰን ነው:: በዚህም ሕንድ የተለያዩ የአየር ንብረቶች ያሉባት ሀገር ናት:: በረዷማ፣ ዝናባማ፣ ደረቅ እና በረሀማ የአየር ንብረቶች አሏት:: ይህ እንደየ ወቅቶቹ ሊፈራረቅ ይችላል:: በሙምባይ እና ኒው ዴልሂ ከተሞች የሙቀት መጠኑ እስከ 38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊደርስ ይችላል::

ሕንድ በተደጋጋሚ በጎርፍ አደጋ ከሚጠቁ ሀገራት መካከል አንዷ ናት:: ይህ በሀገሪቱ ካለው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ጋር የሚያያዝ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ:: ይህንንም ለመከላከል የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ማከናወን ከጀመረች ቆይታለች:: ግድቦች ማነጽ፣ መፋሰሻዎችን መገንባት እና ቅድመ ማስጠንቀቂያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የብዝሀ ሕይወት እና የአካባቢ ጥበቃዎችን እንደምታደርግ ሳይንስ ዳይሬክት አስነብቧል:: ሕንዶች ለዛፎች እና ለላሞች ልዩ ፍቅር አላቸው::

እ.አ.አ በ2025 የሕንድ ኢኮኖሚ 17 ትሪሊየን እንደደረሰ እና የነፍስ ወከፍ ገቢዋም ወደ 12 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እንደሚጠጋ የዓለም ገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ያወጣው መረጃ ያመላክታል:: ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ሁሉም ዜጎቿ እና አካባቢዎቿ የተመጣጠነ እድገት የላቸውም:: ኒው ዴልሂ እና ሙምባይ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች የተሻለ አድገት ሲኖራቸው የደቡቡ ክፍል ግን አብዛኛው በጉስቁልና ሕይወት ውስጥ ይኖራል:: ለዚህም ታሪካዊ የተሳሳቱ ፖሊሲዎች፣ ተፈጥሯዊ ምክንያቶች፣ አድሎአዊ ኢኮኖሚያዊ መዋቅሮች፣ የተበላሹ አስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ የተመጣጠነ የሀብት ምደባ አለመኖር እና ሌሎች ምክንያቶች ይጠቀሳሉ:: ቢሆንም ግን ሕንድ በጊዜ ሂደት እየተሻሻለ በመጣው የሥራ፣ የዴሞክራሲ እና የቁጠባ ባሕሏ በቀጣይ የዓለምን ኢኮኖሚ በመሪነት ይቆጣጠራሉ ተብሎ ከሚጠበቁት ሀገራት ተርታ ተመድባለች::

በሀገር ውስጥም ሆነ በሀገር ውስጥ የታለመውን የኢኮኖሚ ኃያልነት ለማሳካት ሕዝቦቿ እየጣሩ ይገኛሉ::  ለዚህም ማሳያ ሕንዶች ከሀገራቸው ወጥተው እንኳ የሌላ ሀገር ምርት ላለመግዛት እጅግ ይጥራሉ:: አልባሳት እና ሌሎች ትንንሽ እቃዎችን ሳይቀር ከሀገራቸው ማምጣትን እንደ ባሕል ይዘውታል:: ደሞዛቸውንም ቀጥታ ወደ ሀገራቸው በመላክ ይታወቃሉ::

በታሪክ የመጀመሪያው ዳይመንድ የተገኘው በሕንድ ነው:: እንቁው ከመሬት ተቆፍሮ የወጣው በአራተኛው ዓመተ ዓለም እንደሆነ ይገመታል:: ሆኖም ዳይመንዶች ከካርበንነት ተብላልተው አሁን ያላቸውን ቅርጽ እና ውበት የሚይዙት በሚሊየን ዓመታት ውስጥ መሆኑን ሳይንስ ያስረዳል::

ሕንዶች ሌላው የሚታወቁበት ነገር እውቀትን መሸጥ ነው:: የተማሩ ሰዎቻቸው  እና ከእውቀት ጋር የተያያዙ ነገሮችን ለመላው ዓለም ያቀርባሉ:: በተለይ በኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ፣ መተግበሪያ ልማት፣ ሳይንሳዊ ማማከር እና ሌሎችን ለመላው ዓለም ያቀርባሉ:: ሆኖም ግን ብዙ ሕንዳዊያን ምሁራን ሌላ ሰው የለፉባቸውን የጥናት ጽሑፎች እና ፕሮጀክቶች የራሳቸው አድርገው የማቅረብ የተሳሳተ ልምድ እንዳላቸው አቤቱታ የሚያቀርቡ አሉ::

ማሩቲ ሱዙኪ፣ ሀዩንዳይ፣ ታታ ሞተርስ እና ኪያ የሚባሉ የመኪና መሥሪያ ካምፓኒዎች አሏት፣ እነዚህ መኪኖች በርካሽ ዋጋ የሚቀርቡ እና ምቹዎች ናቸው:: በሀገራችን በስፋት የሚገኘው በተለምዶ ባጃጅ ተብሎ የሚጠራው እነሱ ቱክ ቱክ ይሉታል በሕንድ ሀገር ይመረታል::

ቦሊዉድ የሕንድ ትልቁ የፊልም ኢንደስትሪ ነው:: ቦምቤይ እና ሆሊዎድን በአንድ በማጣመር ቦሊዉድ በሚል ነው ስሙ የወጣው:: ቦሊውድ የሕንድ ብቸኛ የፊልም ኢንደስትሪ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ፤ ይሀ ግን ስህተት ነው:: ታሚለ፣ ተልጉ፣ ካናዳ እና ማላያላም እና ሌሎች የፊልም ካምፓኒዎች አሉ:: ሕንድ ከቦሊዉድ በታክስ ብቻ በየዓመቱ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊየን ዶላር ታገኛለች:: የፊልም ኢንደስትሪው ሕንድ በዓለም ታዋቂ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን አስተዋጽኦ አድርጓል:: በዚህ ኢንደስትሪ ተዋናይ የሆነው ሻሩክ ካሀን ከዓለማችን ሕዝብ ግማሹ ያደንቀዋል:: በዓለማችን በሁሉም አህጉራት ሽልማት ያገኙት ሻሩክ ካሀን እና ማይክል ጃክሰን ብቻ ናቸው ሲል ትሬድስ የተሰኘው ድረ ገጽ አስነብቧል::

እንደ ጎርጎሮሳዊያን አቆጣጠር በ2023 ሕንድን አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊየን የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገራት ጎብኝተዋታል:: በ2019 እ.አ.አ 10 ነጥብ ሰባት ሚሊየን የውጪ ሀገር ሰዎች ሕንድን ጎብኝተዋል:: የኮሮና ቫይረስ በተከሰተበት በሚቀጥለው ዓመት 75 ከመቶ ቀንሶ ወደ ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊየን አሽቆልቁሏል::

በ15ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው ታጅ ሜሀል የሀገሪቱ ዋነኛ የጎብኝዎች መዳረሻ ነው:: ቅርሱ በኒው ዴልሂ ከተማ የሚገኝ ሲሆን ያሙና ከተሰኘው በአጠገቡ ከሚያልፈው ወንዝ ጋር ሲታይ እጅግ ይማርካል:: ሙምባይ እና ጎአ የተሰኙ ከተሞች ደግሞ ከዴልሂ ቀጥሎ የጎብኝዎች መዳረሻ ናቸው:: በእነዚህ እና ሌሎች ከተሞች ጥንታዊ ቅርሶች፣ የባሕር ዳርቻዎች እና ተፈጥሯዊ ቦታዎች፣ የጥበብ፣ ባሕል እና ንግድ መዳረሻዎች በስፋት ይገኛሉ:: ለየት ባለ መልኩ ደግሞ በሕንድ የሕክምና ጉብኝት ተስፋፍቷል:: በዋጋው ርካሽነት፣ የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት ታካሚዎች ሕንድን ይመርጧታል:: በደቡብ እስያ የምትገኘውን ሕንድ በጥቂቱ እንዲህ አስቃኘናችሁ::

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here