ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች የርስ በርስ ግጭቶች ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላሉ፡፡ በርስ በርስ ግጭቱም በርካታ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡ ክቡሩ የሰው ሕይወት ይጠፋል፤ ለዘመናት ተደክሞበት የተፈራ ሀብት ይወድማል፡፡
የሀገራቱን የርስ በርስ ግጭት ውስጥ መግባት ተከትሎም የሰላም ስምምነቶች ይፈረማሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ስምምነቶቹ ብዙ ጊዜ ተግባራዊ ሲሆኑ አይታዩም፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ ስምምነቶቹ ባሕላዊ እሴቶችን መሠረት ያደረጉ አለመሆናቸው ነው፡፡
ባንጻሩም ለሰላም መስፈን ሲባል የሚደረጉ ስምምነቶች ባሕላዊ ዕሴቶችን መሠረት ካደረጉ ውጤታማ የመኾን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
ለምሳሌ በአፍሪካ እና በእስያ ሀገራት በባሕላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ባሕላዊ ዕሴቶች ግጭትን በመፍታት ረገድ ከመደበኛው ሕግ ይልቅ እስከ 80 በመቶ የሚደርስ ስኬት ማስመዝገባቸውን አመላክተዋል፡፡ የእኛ ሀገር የዘመናት ተሞክሮ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ
ግጭቶች ሲከሰቱ በባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ስትፈታ እና ሰላምን ስታሰፍን ኖራለች፡፡ ዛሬም ቢሆን የበርካታ ባሕላዊ ዕሴቶች ባለቤት የሆነችው ሀገራችን ግጭት መለያዋ ሊሆን አይገባም፡፡
በኢትዮጵያ ባሕል መሠረት የሀገር ሽማግሌዎች ከፍተኛ ተሰሚነት አላቸው፡፡ ስለሆነም በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው ግጭቶች ይፈቱ ዘንድ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖችን በማቀራረብ ግጭት ውስጥ ያስገባቸውን ችግር ከእነ ምክንያቱ፣ ግጭት ውስጥ በመግባታቸው የደረሰባቸውን ጉዳጥ እንዲሁም ከግጭት መውጫ መንገዱን በማሳየት ሁለቱ ወገኖች ይቅር እንዲባባሉ እና ከግጭቱ እንዲወጡ የማሳመን ሥራ መሥራት ከሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
ባሕላዊ ሽምግልና ትኩረቱ ጥፋተኛን መቅጣት ሳይሆን የተሰበረውን ግንኙነት መጠገን ነው፡፡ ስለሆነም የሀገር ሽማግሌዎች በግጭት አፈታት ሂደቱ ላይ የተቋረጠውን የሁለቱን ወገኖች ግንኙነት ማደስ ላይ አተኩረው ግጭቱን ለመፍታት መጣር ይኖርባቸዋል፡፡
ግጭቶችን ባሕላዊ ዕሴቶችን ተጠቅሞ ከመፍታት ጎን ለጎንም ችግሮቹ በዘላቂነት ይፈቱ ዘንድ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንዲሁም አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን መተግበር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
የሕግ የበላይነት ከተረጋገጠ ዜጎች ሕጉን ቢተላለፉ በሕጉ መሠረት ይዳኛሉ፤ ወደ ርስ በርስ ግጭት የመግባታቸው ዕድልም በእጅጉ ይቀንሳል፡፡
አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶችም በመላው አፍሪካ በስፋት ተግባራዊ የሚደረጉ እና አለመግባባቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መፍታት ያስቻሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የሕገ መንግሥት መሠረት አላቸው።
በአማራ ክልልም አሥራ አምስት ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች በጥናት ተለይተዋል፡፡ እነዚህን አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች መተግበር ግጭቶችን ከመፍታት ባሻገር ፍርድ ቤቶች ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖችን ጉዳይ በመመርመር እና በመዳኜት ፍትሕን ለማስፈን በሚያደርጉት ጥረት የሚያጋጥማቸውን የሥራ ጫና በማቃለል፣ ወጪን በመቆጠብ፣ በማሕበረሰቡም ውስጥ መተማመንን እና ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ስለሆነም እነዚህን ሀገር በቀል አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች መተግበር ይገባል፡፡
በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


