ባሕል ጠባቂዉ ዩኔስኮ

0
29

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሪዎች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፤ የደረሰብንን ውድመት ለማካካስ ምን ዓይነት ማኅበረሰብ መገንባት አለብን በሚል ሐሳብ በጋራ ተመካከሩ። ዳግም ጦርነቶች እንዳይቀሰቀሱ በሚል እ.አ.አ በ1942 የዓለም መሪዎች በትምህርት፣ ባህል፣ ሳይንስ እና በመረጃ ዘርፎች አማካይነት ዘላቂ ሰላምን የሚገነባ ድርጅት የማቋቋም ራዕይ ሰነቁ። በ1945 ድርጅቱ ተመሠረተ።

ዩኔስኮ (UNESCO) የተባበሩት መንሥስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ሆኖ ሲመሠረት በትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ዘርፎች ዓለም አቀፍ ትብብርን በመጠቀም ሰላምን ለመገንባት የሚጥር ልዩ ድርጅት ሆነ።

“ጦርነቶች የሚጀምሩት በወንዶችና በሴቶች አእምሮ ውስጥ ነው፣ የሰላም መከላከያዎችም መገንባት ያለባቸው በወንዶችና በሴቶች አእምሮ ውስጥ ነው” በሚል መሪ ቃል ነበር በእንግሊዝ የተመሰረተው። በኋላ ዋና መስሪያ ቤቱን ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ አዛውሯል።

ዩኔስኮ በአምስት ዋና ዋና  ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት ሰላምን የማስጠበቅ አጀንዳውን ለማሳካት ይጥራል። የመጀመሪያው ትምህርት ነው። ለሁሉም ሰው፣ በሁሉም የእድሜ ልክ  ጥራት ያለው  ትምህርትን እንዲያገኝ ይሠራል። ሁለተኛው የትኩረት መስኩ ሳይንስ ነው። ሳይንሳዊ እውቀትን እና ፖሊሲዎችን ለዘላቂ ልማት መጠቀም ላይ ይሠራል። በሦስተኛ ደረጃ የሚያተኩርበት ባህል ነው። የባህል ብዝኀነትን፣ ባሕላዊ ውይይቶችንና የሰላም ባህልን ለማጎልበት ይሠራል። ማኅበራዊና ሰብዓዊ ሳይንሶችን ማጎልበት በአራተኛ ደረጃ የሚሠራበት መስኩ ነው። በዚህም ፍትሐዊ እና አካታች ማኅበረሰቦችን ለመፍጠር እውቀትን እንደመሳሪያ ይጠቀማል። የማኅበረሰብ እውቀቶችን ያጎለብታል።

መረጃና ኮሙዩኒኬሽን ድርጅቱ በአምስተኛ ዘርፍነት የሚሠራበት መስክ ነው። ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ማስፋፋትና ለሁሉም ሰው የመረጃ ተደራሽነትን በመደገፍ ይተጋል።

ዩኔስኮ ከላይ የተዘረዘሩ ዓላማዎቹን ለመደገፍ መጋቢት ስምንት የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን፣ በግንቦት ሶስት የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን እና በጥቅምት አምስት የዓለም የመምህራን ቀን የመሳሰሉ 40 ዓለም አቀፍ ቀናትን ያከብራል።

የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ጥበቃ ስምምነት እ.አ.አ በ1972 ሲመሠረት፤ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን ለመከላከልና ለመጠበቅ በማለም ነው። በዚህም ተፈጥሯዊ ቦታዎች፣ ጥንታዊ ከተሞች፣ ታላላቅ መልክዓ ምድሮች፣ ደሴቶች፣ ካቴድራሎች፣ ቤተመንግሥቶች፣ ቤተመቅደሶች፣ ታሪካዊ የድሮ ከተሞች እና አስደናቂ ስፍራዎችን ይጠብቃል።

በዚህም በ170 ሀገሮች ውስጥ 1248 የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ቦታዎች ሆነው ተመዝግበዋል። ከዚህ መካከልም  967 ባህላዊ ቦታዎች፣ 227 ተፈጥሯዊ ቦታዎች እና 54 የሁለቱም ድብልቅ የሆኑ ቦታዎች ይገኙበታል።

ጣሊያን 61 ቦታዎችን በድርጅቱ በማስመዝገብ ዝርዝሩን ትመራለች፡፡ ቻይና በ60 ቦታዎች ትከተላለች። የዓለም ቅርስ ጥበቃ ስምምነቱን የተፈራረሙት 196 ሀገራት ቢሆኑም እንኳን ከስምምነት ተዋዋይ ሀገሮች ውስጥ 28ቱ እስካሁን ምንም የዩኔስኮ ቅርሶችን ወይም ባህሎችን አላስመዘገቡም።

ዩኔስኮ እ.አ.አ በ1978 የመጀመሪያዎቹ 12 ቦታዎችን መዝግቧል። ከእነዚህ መካከል የኢኳዶር ጋላፓጎስ ደሴቶች፣ የጀርመን አቸን ካቴድራል እና የኢትዮጵያ የላሊበላ የድንጋይ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ይገኙበታል።

በኪሪባቲ የሚገኘው የፎኒክስ ደሴቶች ጥብቅ ስፍራ 408 ሺህ  ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ትልቁ ቦታ ነው፣ በቼክ ሪፐብሊክ ኦሎሞክ የሚገኘው ቅዱስ ሥላሴ ቤተክርስቲያን 200 ሜትር ስፋት ያለው ትንሹ ስፍራ ነው።

በዩኒስኮ ከተመዘገቡት ስፍራዎች መካከል በጣም የሚጎበኘው  በቻይና ቤጂንግ የሚገኘው የተከለከለው ከተማ ተብሎ የሚጠራው ጥንታዊ ቤተመንግሥት ነው። በየዓመቱ በአማካይ 15 ሚሊዮን ጎብኚዎች አሉት። በ1400ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተገነባው ይህ የንጉሣዊ ቤተመንግሥት ውስብስብ የሚንግ እና ኪንግ ሥርወ መንግስታት ንጉሠ ነገሥታት መኖሪያ ነበር። ባህላዊ የቻይና ሥነ ሕንፃው፣ ወርቃማ ጣሪያዎቹ እና ሰፋፊ አደባባዮቹ ልዩ ናቸው። በቤጂንግ እምብርት ውስጥ ይገኛል።

የአውሮፓ በጣም የሚጎበኘው ቦታ ደግሞ በፓሪስ የሚገኘው የሴይን ወንዝ ዳርቻ ነው።

ድርጅቱ ድንበር ተሻጋሪ ቦታዎችንም መዝግቧል። ባጠቃላይ 51 የዓለም ቅርስ ቦታዎች ብሔራዊ ድንበሮችን የሚያልፉ ናቸው። ለምሳሌ የኡቭስ ኑር ተፋሰስ ሞንጎሊያ እና ሩሲያ አህጉሮችንም ይዘልቃል። እ.አ.አ በ2007 ኦማን የሚገኘው የአረቢያ ኦሪክስ ጥብቅ ስፍራ ነዳጅ ዘይት ተገኘበት። ይህን ተከትሎ የሀገሪቱ መንግሥት የጥብቅ ስፍራውን 90 በመቶ በመቀነሱ ከዩኔስኮ ዝርዝር የተወገደ የመጀመሪያው ቦታ ሆኗል።

ባዝ ከእንግሊዝ፣ ቬኒስ ከጣሊያን እና ኪቶ ከኢኳዶርን ጨምሮ ዘጠኝ ከተሞች ሙሉ በሙሉ በዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ተመዝግበዋል። በዚህም ሙሉ በሙሉ የዩኔስኮ ቦታ የሆኑ ከተሞች ተብለው ይጠራሉ።

የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ቦታዎች አካላዊ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን  የማይዳሰሱ ቅርሶችንም አካቷል። የጣሊያን የናፖሊታን ፒዛ አሠራር፣ የአርጀንቲና ታንጎ ጭፈራ እና የፊንላንድ ሳውና ባህል የመሳሰሉት የማይዳሰሱ ባህላዊ ወጎች በዩኔስኮ ተመዝግበዋል።

የጀርመኑ ዲ ደብሊው የዘገባ ምንጭ በአፍሪካ የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ቦታዎች እጥረት አለ ሲል ዘግቧል። በዩኔስኮ የተመዘገቡት የአፍሪካ ቅርሶች እና ቦታዎች ከ9 በመቶ በታች የሚሆኑት ናቸው ብሏል። ለዚህም በርካታ ምክንያቶችን ጠቅሷል።

የመጀመሪያው አውሮፓዊያን የሚዘውሩት መሆኑ ነው። የኬንያው አርኪኦሎጂስት ጆርጅ አቡንጉ እንደሚሉት፤ የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ስምምነት በ1972 ሲመሰረት መሥራቾችም ይሁኑ ሂደቱን የሚመሩት ነጮች ነበሩ። በዚህም ዩኔስኮ አፍሪካዊ ሳይሆን አውሮፓዊ ሆነ ይላሉ።

የአፍሪካ ሀገሮች ቦታዎቻቸውን በዝርዝሩ ውስጥ ለማስገባት “ለሰው ልጅ ያላቸውን እጅግ የላቀ ዋጋ በምዕራባዊ አመለካከት ማረጋገጥ አለባቸው” ይላሉ። ይህም ሌላ ፈተና ሆኖ ቀጠለ።

ቀጥሎ የሚመጣው ችግር የማመልከቻ ደብዳቤ ጉዳይ ነው። የዩኔስኮ ማመልከቻዎች በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ገጾች ያሉት ፋይሎችን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ በቂ እውቀት፣ ልምድ እና ፋይናንስ ለሌላቸው የአፍሪካ ሀገሮች አስቸጋሪ ነው።

የፖለቲካ ፍላጎት እና የልማት ስጋቶች ቀጥሎ የሚመጣው ችግር ነው። በአፍሪካ ያሉ መንግሥታት ኢኮኖሚን ማሳደግ፣ ክትባቶችን መግዛት እና ሥራ መፍጠር ላይ ያተኩራሉ። የዓለም ቅርስ ቦታ የመሆን ፍላጎት የሚቀንስበት አንዱ ምክንያት፣ ቦታው ከተመዘገበ በኋላ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ  ቦታ የመቸገር ስጋት ነው። ሲል ዲ ደብሊው ዘግቧል።

በዩኔስኮ የተመዘገበን ቅርስ መጠገን የሀገራት ወይም የአካባቢ መሪዎች የሚያደርጉት ተግባር አይደለም። ራሱ ድርጅቱ ነው የሚጠግነው። ይህ ደግሞ ረጂም ጊዜ ስለሚወስድ ዩኔስኮ እስከሚደርስ ቅርሶች የበለጠ ሊጎዱ ይችላሉ። የጎንደር አብያት መንግሥታት እና የላሊበላ ውቅር አብያት ክርስቲያናት ጉዳት ደርሶባቸው በቀላሉ መጠገን አልተቻለም ነበር። ቅርሶችን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ዩኔስኮ በመሆኑ እሱ ሲፈቅድ እና ሲፈልግ ነው የሚጠግናቸው። ይህ ሌላው ዩኔስኮ ውስጥ የመግባት ችግር ነው።

በአሁኑ ጊዜ ዩኔስኮ ከመዘገባቸው ቦታዎች ውስጥ 54 ያህል አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው። 38ቱ የባህል እና 16 የተፈጥሮ ቦታዎች ናቸው።  200 አባላት አሉት። አሜሪካ ዩኔስኮን ፖለቲካዊ ጫና ያሳድራል በሚል መውቀስ የጀመረችው እ.እ.አ በ1983 ነበር። በዚህም ከድርጅቱ አባልነት ወጣች። ወዲያውም እንግሊዝ እና ሲንጋፖር የአባልነት ክፍያ በዛብን ብለው ወጡ። ከዓመታት በኋላ አሜሪካ በ2003፣ እንግሊዝ በ1997፣ ሲንጋፖር በ2007 ድርጅቱን ተቀላቀሉ። ከ383 በላይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ይሰራል። ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝቷል።

 

ማረፊያ

የተማረ ሆኖ እውነቱን የማይገልጥ

ባለ ጸጋ ሆኖ ገንዘቡን የማይሰጥ

ደሃ ሆኖ መሥራት የማይሻ ልቡ

ሦስቱም ፍሬ ቢሶች ለምንም አይረቡ።

ከበደ ሚካኤል

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here