ባሕር ዳር እና ጂምናዚየም

0
17

ለሰዎች እንደ መሰረታዊ ነገር የሚቆጠረው ጂምናዚየም በባህርዳር ከተማ ለውጥ እየታየበት ነው።    ብዙዎች የጂምናዚየሞችን አስፈላጊነት ሲገልጹ እንደ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ሁሉ መረጃና ጂምናዚየም በጣም አስፈላጊ ስለመሆናቸው ይናገራሉ። እንደ ችግር የሚነሳው ጂምናዚየም የማዘውተር ባህላችን መሆን በሚጠበቅበት ልክ ሆነን አለመገኘታችን ነው። ኢንስትራክተር አብርሃም ካሳሁን በቴኳንዶ ስፖርት በባህር ዳር ብሎም በአማራ ክልል አንቱታን ያተረፈ ተወዳዳሪ ብሎም አሰልጣኝ ነው። በተለይም ከ1990 መጨረሻ ጀምሮ ተወዳጅ በነበረው የቴኳንዶ ስፖርት ላይ ሀገሩን ወክሎ  ኮሪያ በመሄድ የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈ ጠንካራ ተወዳዳሪ ነው። በስፖርቱ ለአመታት የለፋው አብርሃም ካሳሁን በስፖርቱ ላበረከተው አስተዋጾኦ የጂምናዚየም ማዕከል የሚገነባበት ቦታ እንዲሰጠው የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያን ይጠይቃል።

ከብዙ ልፋትና ውጣ ውረድ በኋላ በ2012 ዓ/ም መጨረሻ በአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የተዘጋጀለትን የመስሪያ ቦታ ተረከበ። በአቅም ማነስ ምክንያት አምስት አመታት ለግንባታ የዘገየው የጂምናዚየም ማዕከል ከስሞኑ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተገንብቶ ስራ ጀምሯል። አብርሽ ጅም የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።እኔም ጂምናዚየሙን ለመመልከት በቦታው በተገኘሁበት ወቅት የተለያዩ ነገሮችን ተመልክቻለሁ። ለምሳሌ አንድ ጂምናዚየም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመክፈት ከቦታ በተጨማሪ በርካታ ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል።

ሌላው እንደ አብርሽ ጂም መሰል ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት ቤት መከፈት የወጣቶች ወይም የተጠቃሚዎች ግንዛቤ እየተቀየረለ መምጣቱ ምክንያት እንደሚሆን አስተውያለሁ። ጂምናዚየሙ አዲስ ቢሆንም ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸው ሴቶች እና ወንዶች ስፖርት  በትኩረት እየሰሩ ነበር። በእለቱ ሀሳባቸውን ለእኔ ለማጋራት ፈቃደኛ የነበሩት በሰጡኝ ሀሳብ “እንደዚህ ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት መስሪያ ቤቶች በባህርዳር ብሎም:: በአማራ ክልል በጣም ጥቂት ናቸው ምክንያቱም የመስራያ ማሽኖቹ ብዙዎች በሚሊዮን ዋጋ ማውጣታቸው ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጊዜ ምርት መሆናቸው ነው ብለውኛል”። በቤቱ  ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሁለት ቦታዎች ላይ የሚገኙ የመሮጫ ማሽኖች ሶስቱ እዚህ አብርሽ ጂም ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ተመልክቻለሁ።

እኔ በተገኘሁበት እለት ከተገኙት መካከል አቶ ቶማስ ታምሩ የባህርዳር ከተማ  አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አንዱ ነው።አቶ ቶማስ በሰጠኝ ሀሳብ የከተማዋን የስፖርት ቱሪዝም አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ የጀምናዚየም ማዕከል በመከፈቱ ደስ ብሎኛል ካለ በኋላ እንደ ከተማ አስተዳደር መሬቱን በመስጠታችንና መሬቱም  ለታለመለት አላማ በመዋሉ ደስተኛ ነኝ ሲል ሀሳቡን ነግሮኛል።

በከተማችን ባህርዳር በዚህ አመት ብቻ በጣም ጥሩ የሚባሉ አራት ጂምናዚየሞች ተከፍተዋል:: ይህም ለነዋሪው አማራጭ ይሰጣልና የበለጠ እንዲስፋፋ እንሰራለን” ያለው ቶማስ ታምሩ የመስሪያ ቦታ ወስደው ስራ ያልጀመሩትን ለመጠየቅና ያለባቸውን ችግር ለመፍታት አብርሽ ጅም አነሳስቶናል በማለት አጫውቶኛል።

“የቴኳንዶ ስፖርተኛና አሰልጣኝ እያለሁ ወደ ፊት ዘመናዊ ጂምናዚየም የመክፈት እቅድ ነበረኝ፤ አሁን ያሳካሁት ያን ህልሜን ነው” የሚለው የጅምናዚየሙ ባለቤት ኢንስትራክተር አብርሃም ካሳሁን “ገና ብዙ የማሳካቸው ነገሮች አሉኝ” ሲል የወደፊት እቅዱን ገልጾልኛል። ጂምናዚየም ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃት ምንም ገንዘብ ለሌለው ባለሞያ አይደለም ሀብት እና አቅም ላለው ሰው ራሱ ከባድ ነው የሚለው ኢንስትራክተር አብርሃም ሒደቱ በቀላሉ የማይጠናቀቅ ትዕግስትን የሚፈታተን የስፖርት ኢንቨስትመንት መሆኑን ተናግሯል። በሌላ በኩል ስራው ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ደግሞ ለበርካቶች የስረ እድል ከመፍጠር ባለፈ ሆስፒታሎች እና የጤና ተቋማት የሚሰሩትን ቅድሚያ የመከላከል ስራ በስፖርት አማካኝነት ማሀበረሰብን ማነጽ ማስተማር እና አምራች ዜጋ ማድረግ ከምንም በላይ የሚገኘው ትርፍ ነው ብሏል አብርሃም።

በአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የማህበራት ማደራጃና ማስፋፊያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ሉሌ በሰጡት ሀሳብ ደረጃቸውን የጠበቁ መሰል ጂምናዚየሞች በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች መስፋፋት እንዳለበት ጠቁመው በተለይም ከንቲባዎች በሀላፊነት እያሉ ለወጣቱ ብሎም ለነዋሪው የሚሆን ጠብ የሚል ነገር እንዲሰራ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው ብለዋል።ከጥቂት አመታት ወዲህ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ናቸው ያሉት አቶ ሙሉጌታ እነዚህን ገዳይ በሽታዎች ለመከላከል የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት የቅድመ መከላከልን ስራ ለመስራት ስፖርት መስራት ወሳኝ ነው ብለው ይህን መጀመሪያ የመስሪያ ቦታ በበቂ ሁኔታ ማመቻቸትና ቅድሚያ የሚሰጠውን ማስቀደም ተገቢ ነው ብለዋል።

በባህርዳር ከተማ ለበርካታ ወጣቶች በስፖርት ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የመስሪያ ቦታ ተሰጥቷል፤ ነገር ግን ምን ያህሉ ሰርተዋል? ምን ያህሉስ በምን ሁኔታ ላይ ናቸው? የሚለው ጉዳይ የተሟላ መረጃ አልተገኘም።በእርግጥ አብዛኞቹ ስፖርተኞች ከእውቀት ባለፈ የስፖርት ማዕከላትን ገንብቶ ለአገልግሎት ለማዋል የገንዘብ አቅም የላቸውም።

ስለዚህ ከከተማ አስተዳደሩ የሚጠበቀው የወጣቶችን ችግር መፍታትና ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ቀዳሚው ሲሆን ለጂምና ለተለያዩ የስፖርት ማከናወኛ ተብሎ የተሰጡትን ቦታ ከሁለተኛ ወገን ማጽዳትና ማረጋገጫ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ለክልሉ በስፖርት ውለታ የሰሩ ነገር ግን ህንጻ ተከራይተው የሚሰሩ ግለሰቦች በተመሳሳይ የጂምናዚየም የመገንቢያ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል። ለምሳሌ በቅርጫት ኳስ ከክልሉ አልፎ ሀገርን የወከለው ሀብታሙ አሰፋ በጎንደር፣ በደሴና በባህርዳር ቤት ተከራይቶ እየሰራ ይገኛል።አሁን ባለው የገቢያ ሁኔታ በውድ  ዋጋ ህንጻ ተከራይቶ የስፖርት ኢንቨስትመንት በማከናወን አትራፊ ለመሆን አስቸጋሪ ነው።ሆኖም በረጅም ጊዜ የሚገኘው ዋነኛ ትርፍ ማሀበረሰቡን ከተለያዩ በሽታዎች መጠበቅ ግባቸው ስለመሆኑ ይናገራሉ።ኢንቨስትመንት ደግሞ የወጣበትን መመለስ ካልቻለ ሌሎች በስፖርት ኢንቨስትመንት ሊሰማሩ ያሰቡትን ላያበረታታ ይችላል።

ለዚህ ጽሁፍ መነሻችን የሆነው የኢንስትራክተር አብርሃም ካሳሁን “አብርሽ ጂም” በባህርዳር ከተማ አባይ ማዶ መከፈት ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ በስፖርት ላይ የሚገኙ ወጣቶች ተስፋ ሳይቆርጡ መዝለቅ ከቻሉ ወደ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል ማሳያ ነው።የጅሙ አሰልጣኝ የሆነው አሸናፊ ጨርቆስ በከተማዋ የተለያዩ ጂሞችን ተዟዙሬ የመጎብኘት እድሉ ገጥሞኛል:: በዚህ አጋጣሚ ወጣቶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ወደ ጅሞች ሄዶ የመስራት ፍላጎትና ልምድ እየጨመረ መምጣቱን አጫውቶኛል።ማሀበረሰቡ በየቦታው እየተከፈቱ ባሉጂሞች ራሱን በመጠበቅ ጤናውን ማስተካከል ይጠበቅበታል ያለው አሸናፊ በሚመለከተው አካል የተጀመረው ተግባርም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲል ተናግሯል።

 

(መልሰው ጥበቡ)

በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here