ለባሕር ዳር ከተማ ውበት በርካታ መገለጫዎችን መዘርዘር ይቻላል። የተጎራበቷት ዓባይ እና ጣና ተፈጥሮ ለባሕር ዳር የለገሰቻቸው ፀጋዎች ናቸው። በከተማዋ ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች ግራ እና ቀኝ የተተከሉት ዘንባባዎችም የውበቷ ዋነኛ ድምቀት ሆነው ዓመታትን አስቆጥረዋል።
በአፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም ውስጥ ይካሄዱ የነበሩ የከተማዋ የስፖርት ክለቦች፣ የክፍለ ሃገር እና ሃገር አቀፍ ልዩ ልዩ የስፖርት ውድድሮች ለባሕር ዳር ከተማ የ1970ዎቹ አይረሴ መገለጫዎች ነበሩ።
ከሁሉም በላይ ውበታቸው በዘንባባዎቿ በሚደምቀው የባሕር ዳር ጎዳናዎች ይርመሰመሱ የነበሩት ብስክሌቶች ለባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች እና በተለያዬ ምክንያት ምድሯን ለረገጡት ሁሉ አይረሴ የውበቷ አድማቂ ነበሩ። ባሕር ዳር ሴት ወንድ፣ ህፃን ሽማግሌ፣ ድሃ ሃብታም … ሳይል ሁሉም በፍቅር ብስክሌት የሚያሽከረክርባት ውብ ከተማ ነበረች። ነበረች ማለቴ በምክንያት ነው። ሙሉ በሙሉ ቀርቷል ባይባልም ብስክሌት በባሕር ዳር በውስን ነዋሪዎቿ ብቻ መሽከርከር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በከተማዋ ያለው የመጓጓዣ አገልግሎት አስቸጋሪነት ያስከተለው ይሁን ሌላ ምክንያት ከቅርብ ወራት ወዲህ በጎዳናዎቿ ብስክሌት የሚያሽከረክሩት ነዋሪዎቿ ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል። ይህን መመልከቴ የቀደመውን የባሕር ዳር ከተማ ውበቶች ትውስታ እንዳሰላስል አነሳሳኝ። በተለይ የባሕር ዳር እና ብስክሌት ቁርኝት ብዙ ትዝታዎችን ጎተተብኝ። እንዲያው የብስክሌት ተገልጋዮች ቁጥር እንደ ድሮው ተበራክቶ ባሕር ዳር ያጣችውን ትመልስ ይሆን የሚል ጥያቄ የትውስታዬ መዳረሻ ሆነና የግሌን እይታ ለእናንተም ለማጋራት ተነሳሳሁ።
የባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች በባሕር ዳር ከተማ ብስክሌትን ዋና የመጓጓዣ ዘዴ አድርገው ተገልግለውበታል። ምክንያቱም ለሰራተኞቹ አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ አልነበረም። በዚህ የተነሳ በሶስት ፈረቃ በሚሰራበት ባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች (ወንድም ሴትም) ሁሉም ብስክሌትን በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ሲገለገሉ ማየት ለባሕር ዳር ውበት ተጨማሪ ድምቀት ነበር። ዛሬ ያ ትዕይንት በፋብሪካው ሰራተኞች አይስተዋልም። ምክንያቱም ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካው ለሰራተኞቹ የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ አቅርቧል።
በባሕር ዳር ከተማ የጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቀደምት ተማሪዎችም በትምህርት ቤት መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ብስክሌት ሲያሽከረክሩ መመልከት ከከተማዋ የጎዳና ላይ ዘንባባዎች ጋር ተዳምሮ የባሕር ዳርን ውበት ቁልጭ አድርገው ያመላክቱ ነበር።
ብስክሌት እና ባሕር ዳር ከተማ የነበራቸው ከፍተኛ ቁርኝት ከመጓጓዣ አገልግሎትም ባሻገር በከተማዋ ይካሄድ የነበረው የብስክሌት ውድድር የባሕር ዳር ውበት አንዱ ማድመቂያ ሆኖ አልፏል። ትዝታው ግን በባሕር ዳር ለኖረባት ሁሉ ዛሬም ድረስ እንደታተመ ነው።
የብስክሌት ውድድር የባሕር ዳር ከተማ እምብርት የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ዘወትር እሁድ ከሌሎች ቀናት በተለየ መልኩ ደምቆ ይውል ነበር። ምክንያቱ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ በቡድኖች በታቀፉ እና በግል ተወዳዳሪዎች፤ ከዚህም በላይ የጎጃም ክፍለ ሃገር እና ሃገር አቀፍ ውድድሮች በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄዱ መነሻ እና መድረሻቸው የባሕር ዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ነበር።
ውድድሩን ለመመልከት እሁድን በጉጉት የምንጠብቅ ብዙዎች ነበርን። ይህም በመሆኑ በውድድሩ መነሻ እና መድረሻ ስፍራ ቀድመን ለመገኘት ከየመኖሪያ አካባቢያችን ተነስተን መሰባሰብ የምንጀምረው ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነበር። በዚህ ስፍራ ተገኝቶ ውድድሩን መከታተል ያልቻለም የብስክሌት ውድድሩ ዙሮች በሚካሄዱበት በተለይም ከአፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም እስከ ዓባይ ምንጭ ሆቴል /አጂፕ ነዳጅ ማደያ/ ድረስ ባለው ዋና የከተማዋ አስፋልት መንገድ ግራ እና ቀኝ ሰብሰብ ብሎ የብስክሌት ውድድር መመልከት የተለመደ ነበር።
ተወዳዳሪዎች በሚንቀሳቀሱባቸው ጎዳናዎች ላይም አብረው የሚጓዙት ትራፊክ ፖሊሶች የሚያሰሙት የሞተር ብስክሌት ድምፅ ካለባበሳቸው ጋር ተዳምሮ ለውድድሩ ልዩ ድምቀትን ያላብሰው ነበር።
ነበር’ን አበዛሁ አይደል? ምን ላድርግ፤ አማራጭ አጥቼ ነው። ያ ሁሉ የባሕር ዳር ከተማ እና ብስክሌት ቁርኝት ከተቋረጠ ዓመታት ተቆጥረዋል።
አልፎ አልፎ በከተማ አስተዳደሩ ስፖርት ጽህፈት ቤት አማካኝነት የብስክሌት ውድድር ይካሄድ ነበር። አሁን ላይ ግን ባሕር ዳር እና የብስክሌት ስፖርት ውድድር ከተጠፋፉ ከሶስት ዓመት በላይ ተቆጠረ ብል ማጋነን አይሆንም። “ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ” እንዲሉ እንኳንስ የብስክሌት ውድድር ለመጓጓዣ ብስክሌት የሚያሽከረክር ሰው መመልከትም ብርቅ እየሆነ መጥቷል። ብስክሌትን ባሕር ዳር ላይ የፆታ ልዩነት ሳይታይ ሁሉም ሲያሽከረከር ውበቷን ያደምቀው እንዳልነበር ዛሬ ዛሬ ብስክሌት ቦታውን በመልቀቅ ሞተር ብስክሌት እና ባጃጅ የከተማዋን መንገዶች ሲርመሰመሱበት ይታያል።
በአማራ ክልል በተደነገገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በባሕር ዳር ከተማ ባጃጅ ለተወሰኑ ሳምንታት እንዳይሽከረከር ክልከላ ተጥሎ ነበር። የሞተር ብስክሌት እገዳው ግን ዛሬ ድረስ ቀጥሏል። በዚህ የተነሳ ብስክሌቱን አቁሞ ሞተር ብስክሌት ይጠቀም የነበረው ወደ ብስክሌት ፊቱን አዙሯል።
በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በከተማዋ የነዳጅ እጥረት ይፈጠራል። የከተማ የመጓጓዣ አገልግሎቱም በየጊዜው ዋጋው እየጨመረ ከፍተኛ ችግር ሆኗል። ይህም የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪን ወደቀድሞው የብስክሌት ተጠቃሚነት ፊቱን እንዲያዞር እያደረገው ነው። በነዚህ ምክንያቶችም የባሕር ዳር ጎዳናዎች የቀደመ መልካቸውን መላበስ ጀምረዋል። ለዚህ ነው ታዲያ ባሕር ዳር ያጣችውን ትመልስ ይሆን? የሚል ጥያቄ የዚህ ትዝብት ፅሑፍ አንኳር ነጥብ ሊሆን የበቃው።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በባሕር ዳር ከተማ እና ቀደምት የብስክሌት ቁርኝት ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ዘገባ አዘጋጅቶ አየር ላይ አውሏል። በኔ ዕይታ ጥሩ መሰናዶ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ምክንያቱም ባሕር ዳር እና ብስክሌት ሲነሳ ከህሊናችን የማይጠፉትን ቀደምት ብስክሌት አሽከርካሪዎች እና ተወዳዳሪዎች አቅርቦ ተውስታችንን ብርሃን እንዲጭርበት አድርጓል።
የቴሌቪዥን ዝግጅቱ የቀደመ ታሪክን ብቻ ሳይሆን ከከተማዋ ጠፍቶ አሁን ብልጭ ያለው የባሕር ዳር እና ብስክሌት ቁርኝት ቀጣይነት እንዲኖረው መከናወን ያለባቸውን ተግባራት በተመለከተም በሚመለከታቸው አካላት አስተያየት እንዲሰጥ አድርጓል።
ብስክሌት ማሽከርከር ከመጓጓዣ አገልግሎት ባለፈ ለጤና ያለውን ፋይዳም የስፖርት ሳይንስ ከፍተኛ ባለሙያዎች ሰፊ ትንታኔ እንዲሰጡበት አድርጓል። በኔ በኩል የአማራ ቴሌቪዥን አዘጋጅቶ ያቀረበው ይህ ዝግጅት የጋዜጠኝነትን መርህ መሰረት አድርጎ የተሰናዳ እና ማህበራዊ ፋይዳውም የጎላ መሰናዶ ነበር።
ሁሉም ዜጋ በባሕር ዳር ከተማ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ብስክሌትን ለመጓጓዣነት ቢጠቀም ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው። ለአብነት ያህል ብስክሌት በማሽከርከር የመጓጓዣ ወጭን መቀነስ ይቻላል። ብስክሌት በማሽከርከር የሚገኝ የሰውነት እንቅስቃሴም ለጤና ያለው ፋይዳ የጎላ ነው። ከዚህም በላይ የአየር ብክለትን ለመከላከል ያግዛል። አኔ ያለኝን ጠቀስሁ እንጂ በባለሙያዎች ቢገለጽ ደግሞ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ይሆናል።
በባሕር ዳር ከተማ ብስክሌት ማሽከርከር ከላይ ከጠቀስኳቸው ጠቀሜታዎች ባሻገር አንዱ የከተማዋ ውበት መገለጫ ነበር። ይሄው ይቀጥል ዘንድ በከተማዋ የሚገነቡ መንገዶች ብስክሌትን ግምት ውስጥ ያስገቡ ሊሆን ይገባል። የብስክሌት ዋጋ እጅግ የናረ መሆኑ ደግሞ ሌላው ሳንካ ሊሆን ስለሚችል መላ ሊዘየድለት ይገባል። በየስርቻው የተሸጎጡ የብስክሌት ጥገና ሰጭ ባለሙያዎችም ትኩረት ሊሰጣቸው ያሻል። ተገቢ የመስሪያ ቦታ ሊያገኙ ይገባል። ለዚህ ሁሉ ደግሞ ዋና ምላሽ ሰጭ የከተማ አስተዳደሩ ይሆናል። የባሕር ዳር ከተማ እና ብስክሌት ቁርኝት ተመልሶ ለማየት ያብቃን! እኔ በዚህ ቋጨሁ፤ እናንተም ያላችሁን ሃሳብ ቀጥሉበት!
(ጥላሁን ወንዴ)
በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም