ባንድ ልብ እንምከር!… ችግሮቻችንንም እንፍታ!

0
113

በግጭት ምክንያት ሰብዓዊ ጉዳት ሲጨምር፣ ማኅበራዊ መስተጋብር ሲላላ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ፣ መልካም የነበረ ገጽታ ሲጠለሽ የምክክር መድረክን በመውጫ መንገድነት ተጠቅመው ሰላማቸውን የመለሱ አገራት በርካታ ናቸው፡፡ በእስያ፣ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም ላቲን አሜሪካ የሚገኙ አገራትን ላብነት ማንሳት ይቻላል፡፡

አገራት በማያባራ ግጭት ውስጥ ሲገቡ አገራዊ ምክክርን በመፍትሄ አማጭነት የሚመርጡት መድረኩ በብዙ መልኩ ከሌሎች የግጭት መፍቻ መንገዶች ተመራጭ በመሆኑ ነው፡፡

አገራዊ ምክክር የሶስተኛ ወገንን ጣልቃ ገብነት አስወግዶ ያንድ አገር ዜጎች ራሳቸው ወይም በመረጧቸው ወኪሎቻቸው የሚሳተፉበት መድረክ መሆኑ አንዱ የመድረኩን ተመራጭነት የሚያረጋግጥልን እውነታ ነው፡፡

ከይድረስ ይድረስ ወይም ሆይ ሆይታ ይልቅ ሰፋ ያለ ጊዜን ወስዶ የሚካሄድና ስር ነቀል የመፍትሔ ሀሳቦች የሚመነጩበት፤ ስምምነትን መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንዲሁም  በዜጎች መካከል መተማመንን እያጎለበተ የሚሄድ የግጭት መፍቻ ዘዴ መሆኑም አገራዊ የምክክር መድረክን ተመራጭ ያደርገዋል።

አገራዊ የምክክር ሂደት አንኳር አንኳር አገራዊ አጀንዳዎችን ወደ መድረክ አምጥቶ ለጋራ መግባባት የሚሠራ መሆኑም ተመራጭነቱን የሚያሳይ ሌላው ባሕርይው ነው።

አገራዊ የምክክር መድረክ  ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ዜጎችን ስለሚያሳትፍ ዜጎች በሂደቱ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል። ዜጎች ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸውን በዘላቂነት የሚፈቱበትን መደላድል የሚፈጥር መድረክም ነው፡፡ የሰዎችን ግንኙነት እና ትብብርን በመገንባት በሰዎች መካከል የመከባባር፣ የመተማመን እና የመተሳሰብ ባህልን በማዳባር የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት፣ አንዱ የሌላውን ወገን ህመም በማጤን ለወገኑ ችግር በጋራ መፍትሔን ለመፈለግ በጋራ እንዲነሳ ያደርጋል፤ አገራዊ የምክክር መድረክ ባንድ ልብ  እስከተካሄደ ድረስ፡፡

አገራችን ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ እያጋጠማት ካለው ግጭት ለመውጣት አገራዊ የምክክር መድረክ በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡ የዚህ አካል የሆነውና ሰሞኑን በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር እየተካሄደ ያለው አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ያገራዊ የምክክር መድረክን ባሕርያት እና ፋይዳ በማጤን መድረኩን ማካሄዷ ተስፋን የሚያጭር መልካም ርምጃ ነው፡፡ መድረኩ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማገናኜት በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ ሲመላለሱ የነበሩ ጥያቄዎች ወደ አደባባይ እንዲመጡ የተደረጉበት፣ የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች የወከላቸውን የማኅበረሰብ ክፍል ሀሳብ መግለጽ የቻሉበት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

በምክክር መድረኩ የተነሱት አብዛኛዎቹ ሀሳቦች ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የሚያደርጉ እና ኢትዮጵያ የእኩልነት ምድር እንድትሆን፣ ዜጎቿም በየትኛውም የሀገራችን ክፍል በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዲችሉ ስንቅ የሚሆኑ እንደሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ በመድረኩ የአማራ ክልልን ጥንታዊ ወግ፣ ባህል እና እሴት ወደነበረበት የሚመልሱ እና የሚያጠናክሩ ሀሳቦችም ተነስተውበታል፡፡ ከእነዚህ የመድረኩ ሁነቶች መረዳት የሚቻለው አገራችን ኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር መድረኩ  ችግሮቻችን ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈቱበት እንዲሆን ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ስለመሆኗ ነው፡፡

አገራችን አገራዊ የምክክር መድረክን ግጭቶችን እና ግጭት ወለድ ችግሮችን ለማስወገድ መምረጧም ሆነ  መድረኩን እያካሄደች ያለችበት መንገድ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መልካም ርምጃ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት በመኖር እና ባለመኖር ሁለት ምርጫዎች ላይ ይገኛሉ፡፡  ባለፉት ዘመናት ያጋጠሙ ችግሮች በርካታ እሴቶቻችን ሸርሽረዋል፡፡ እናም ብቸኛው አማራጭ ባንድ ልብ መክሮ በጋራ ጉዳዮች የጋራ መግባባትን መፍጠር እና ሰላምን ማስፈን ነው። ባገራዊ የምክክር መድረኩ ከፍ የሚለው ፓርቲ፣ ግለሰብ ወይም ድርጅት ሳይሆን ኢትዮጵያ መሆን ይኖርባታል፡፡ ሁሉም ወገኖች ይህን እውነታ ተገንዝበው ያሏቸውን የተለያዩ ፍላጎቶች በምክክር መድረኩ ይዘው በመቅረብ  ምላሽ ያገኙ ዘንድ በጋራ ሊሠሩ ይገባል፡፡

ቀደምት ኢትዮጵያውያን በበርካታ ጉዳዮች ላይ በአንድ ልብ እየመከሩና እየተግባቡ ኢትዮጵያን እንዳስረከቡን ሁሉ እኛ ልጆቻቸውም ችግሮቻችንን ከልብ በመነጨ ቅንነት በምክክር እየፈታን ሰላሟ የተረጋገጠ፣ ልጆቿ በፍቅር፣ ባንድነት፣ በነጻነት፣ በእኩልነት፣ ያላንዳች ሰቀቀን የሚኖሩባትን ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ማውረስ አለብን! ፡፡

በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here