ቤሪንግ የባህር ወሽመጥ

0
158

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

የባህር ወሽመጦች በሁሉም ውቅያኖሶች ወይም ልቅ የውሃ ክፍሎች ያለ የተለመዱ መልከአምድራዊ ገፅታዎች ናቸው።  የባህር ወሽመጥ ማለት ሁለት ትላልቅ የውሃ አካላትን የሚያገኛኝ ጠባብ የውሃ መንገድ ወይም ቻናል ነው። እንዲሁም የባህር ወሽመጥ ሁለት ትላልቅ የመሬት አካላትን የሚያለያይ ጠባብ የውሃ አካል   ተብሎም ሊገለጥም ይችላል። የባህር ወሽመጥ በሁለት የውሃ አካላት መካከል ውሃ ያቀያይራል ወይም ውሃ እንዲገናኙ የሚያደርግ እና ምናልባትም እንደ በሁለት የምድር አካላት መካከል እንዲወሰን መለያነትም ያገለግላል።

እንደ ውቅያኖሶች፣ ባህሮች እና ባህረ ሰላጤዎች ያሉ ክፍት የውሃ አካሎችን የሚያለያዩ በርካታ የባህር ወሽመጦች አሉ። ሰላማዊ ውቅያኖስም ብቻውን ርዝመት እና ስፋታቸው የሚለያዩ 19 የባህር ወሽመጦች አሉት። ከእነዚህ መካከል በሰላማዊ ውቅያኖስ ውስጥ የሚገኘው አንዱ እና ዋነኛው ቤሪንግ የባህር ወሽመጥ ይባላል። ሁለት የዓለማችንን ትላልቅ ሀገሮች አሜሪካን እና የሩሲያን የሚለያይ ጠባብ የውሃ መተላለፊያ ነው።

ቤሪንግ የባህር ወሽመጥ

የቤሪንግ የባህር ወሽመጥ ሰሜናዊው የሰላማዊ ውቅያኖስ ጫፍ የሆነ እና እስያን እና ሰሜን አሜሪካን ፣ በዋናነት የሩሲያን እና የተባበረች አሜሪካን ይለያል። ወደመጡበት ቤሪንግ ባህርን የአርክቲክ ውቂያኖስ አካል ከሆነው ከቹክቺ ባህር ጋር ያገናኛል። በባህር ወብመጡ ጠባብ ጫፍ ላይ እስያ እና ሰሜን አሜሪካ ማለትም ሩሲያ እና ዩ ኤስ አሜሪካ 85 ኪ.ሜትር ብቻ ይራራቃሉ። በጣም ጠባቡ ክፍል አላስካ ካለው በኬፕ ፕሪንስ ኦፍ በዌልስ እና በሩሲያው ኬፕ ዴዥኔቭ መካከል ያለው ነጥብ ነው። በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የድንበር ወሰን በቤሪንግ የባህር ወሽመጥ እና በቤሪንግ ባህር አቋርጦ ያልፋል።

በአንፃራዊነት የቤሪንግ ባህር ወሽመጥ ጥልቅ አይባልም፣ በመሆኑም አላቀረቡም ጥልቀቱ 50 ሜትር ነው። ጥልቅ የበሚባለው ክፍሉ 90 ሜትር ይጠልቃል። አንዴ በበረዷማው ዘመን  ቤሪንግ የባህር ወሽመጥ በሰሜን አሜሪካ እና በእስያ መካከል የነበረ  የየብስ ድልድይ እንደነበር መላ ምት ይሰጥ ነበር። በዚህ ወቅት፣ የየብስ ድልድይ በመፍጠር የባህሩ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ፣ ይህም ዛፎች እንዲበቅሉ እና እንስሳትም ወደ ሁለቱም አቅጣጫ እንዲንቀሳቀሱ አስችሎ ነበር።

የባህር ወሽመጡ፣ የዳዮሜድ ደሴቶችን እና ሴንትራል ላውረንስ ደሴቶችን ጨምሮ በርካታ ደሴቶች አሉት። ሁለቱ የዳዮሜድ ደሴቶች በባህር ወሽመጡ እምብርት ላይ ይገኛሉ። በመካከላቸው 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ሲኖር ትልቁ የዳዮሜድ ደሴት የሩሲያ ሲሆን ከአጠገቡ ያለው ትንሹ ዲያሜድ ደሴት ደግሞ የአሜሪካ አካል ነው። የዓለማቀፍ የቀን መስመር በሁለቱ ደሴቶች መካከል የሚያልፍ ሲሆን በሩሲያ እና በአሜሪካ በኩል የተለያዩ የቀን ስሌቶች እንዲከተሉ አድርጓል። በራሺያ ወገን ያለው የሰአት አቆጣጠር ከአሜሪካው በ21 ስአት ይቀድማል። ሴንትራል ላውረንስ ደሴት በትልቅነቱ ስድስተኛ የሆነ የአሜሪካ ደሴት ነው።

ቦታውን የተለያዩ  አሳሾች በተለያዩ ጊዜያት መጥተውበት እንደነበር ታሪክ ያሳያል፤ ይሁን እንጂ ቦታው በስሙ እስኪሰየምለት የደረሰ አንድ ሰው አለ፡፡  እርሱም በ1720 ዓ.ም ወደ ባህር ወሽመጡ የገባው ዴንማርካዊ ካርቶግራፈር ቪተስ ቤሪንግ ነው። ከእርሱ በፊት በ17ኛው ክፍለ ዘመን ያቋረጠው ሴምዮን ዴዝንዮቭ ሲሆን የእርሱን ገድል የተመለከቱ  በርካታ ሳይንቲስቶች እንደ ሚያምኑት ሰዎች ከእስያ ወደ ሰሜን አሜሪካ በእግር አቋርጠው እንደገቡ ይነገራል፡፡ ይህ ደግሞ አብዛኛው ውሃ አካል በበረዶ ተሸፍኖ በነበረት ወቅት ነው። ይሁን እንጂ በቤሪንግ ባህር ወሽመጥ አካባቢ ብዙ ሰው አይኖርም ። በጥቅሉ ይህ አካባቢ የተበታተነ አኗኗር ያለበት ነው። አልፎ አልፎ ብቻ ትናንሽ መንደሮች ይገኛሉ። ብዙ ሰዎች አለበት ከሚባሉት ውስጥ 230 ሰዎች ብቻ ያሉት ቴለር እና 3ሺ800 ሰዎች የሚኖርባት ኖም የተባሉት የአሜሪካ ከተሞች ይጠቀሳሉ። የራሺያ ከተሞች ደግሞ ላቨረንቲያ እና ሎሪኖ የተባሉት ከተሞች ይገኛሉ። ሴንት ላውረንስ ደሴት ወደ አንድ ሺህ ሰዎች ኖርባታል፤ ሊጽል ዳዮሜድ ደሴት ደግሞ 135 ሰዎችን አስጠልላ ትገኛለች። የቤሪንግ ባህር ወሽመጥን በዋና ማቋረጥ የቻሉ አልጠፉም።

በ1979 ዓ.ም ላይ ሊን ኮክስ የተባለ ታዋቂ የኦሎፒክ ዋናተኛ ከአላስካ ወደ ሩሲያ 4.3 ኪሎ ሜትር ዋኝቶ አቋርጧል፤ ይህ ተግባሩም ሩሲያ እና አሜሪካ የነበራቸውን የቀዝቃዛው ጦርነት ውዝግብ ማብረድ የቻለ ተብሎለት ነበር።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የህዳር  16  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here