“ቤተ ክርስቲያን የዓለማዊውም ሆነ የመንፈሳዊ ዕውቀት ምንጭ ናት” ብጹዕ አቡነ አብርሃም

0
103

በባሕር ዳር ከተማ ዓባይ ማዶ ሰፈነ ሰላም ቅድስት አርሴማ እየተባለ ከሚጠራው ቦታ ላይ የአራቱ ጉባኤያት ኮሌጅ እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል። የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም ናቸው።

በዕለቱ ንግግር ያደረጉት ብጹዕ አቡነ አብርሃም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረቶቿ የአብነት ትምህርት ቤቶች ናቸው ብለዋል። ቤተ ክርስቲያን የዓለማዊውም ሆነ የመንፈሳዊ ዕውቀት ምንጭ እንደሆነችም ገልጸዋል። በዘመናዊውም ሆነ በመንፈሳዊ ዕውቀቱ የበሰለ ትውልድን ለማፍራት የእነዚህ አይነት ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች እንቅፋቶች ገጥመውት የነበረው ይህ ኮሌጅ ሕጋዊ አሠራርን መሠረት አድርጎ መጓዝ በመቻሉ ፍሬ ማፍራት እንዲጀምር አስችሎታል ነው ያሉት። ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ሁሉ ውብ ተፈጥሮ እና ልምላሜ አለ ያሉት ብጹዕነታቸው በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድን ማፍራት ዐቢይ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

“የቤተ ክርስቲያን መገለጫዋ አንድነት፣ ሰላም፣ ፍቅር እና ችግርን ተጋግዞ ማለፍ ናቸው፤ በመተጋገዝ እና አብሮ በመቆም እንደነዚህ አይነት ለበጎ ዓላማ የቆሙ ተግባራትንም ማከናወን ይቻላል” ነው ያሉት። የመሠረት ድንጋዩ ከመቀመጡ ቀደም ብሎም በመሠራት ላይ ሚገኙ ተግባራት እንዳሉም ብጹዕነታቸው ጠቁመዋል። ለአብነትም የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን ማስተማር መጀመሩን አንስተዋል።

ሊቀ ጠበብት ስጦታው አያሌው በባሕር ዳር ከተማ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ናቸው። ዛሬ መሠረተ ድንጋዩ የተቀመጠው የቤተ ጉባኤ ኮሌጅ እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል። ተግባሩ የማኅበረሰብ መሠረት ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።

የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህሩ ኃይለ ማርያም ዘውዱ እንዲህ አይነት ኮሌጆች እውነተኛ ሰዋዊ ባሕርይን የተላበሱ ዜጎችን ለማፍራት ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ነው ብለዋል። የተማረ ትውልድ በጎ ነገሮችን እንደሚሠራ በማንሳት ሊደገፍ የሚገባው ተግባር ስለመሆኑ ገልጸዋል። የሕግ ምንጭ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ለትውልዱ ለማስተላለፍም ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የመሠረተ ድንጋይ የተቀመጠለት የቤተ ጉባኤ ኮሌጅ እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በቤተ ክርስቲያኗ እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የሚተገበር ነው ተብሏል። በመንፈሳዊው በኩል አራቱ ጉባኤያት የሚማሩበት ሲሆን በዘመናዊው ትምህርት ቤት ደግሞ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ለማስተማር ዕቅድ ያለው ተቋም እንደሆነም ተገልጿል።

(ሰለሞን አንዳርጌ)

በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here