በዓለም ላይ የሚገኙ ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን አስከብረው በተሻለ ቁመና ለመቀጠል ብሄራዊ ጥቅምን ቀይ መስመራቸው ያደርጋሉ:: ሀገርን ዋና ጉዳዩ የሚያደርገው ብሄራዊ ጥቅም ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚሰነዘሩ ጣልቃ ገብነቶችን ለመመከት፣ በምጣኔ ሐብት ተወዳዳሪ ለመሆን፣ ከሌላው ሀገር ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እና ለማጠናከር ትልቅ ኅይል ነው::
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ትኩረቱን ምን ላይ ያደረገ ነው? ብሄራዊ ጥቅም ምንነት፣ ስጋቶች እና ማን ምን ሊሠራ እንደሚገባ ይህ ጽሑፍ ምላሽ ይዟል:: ሀገር ለአንድ ዜጋ ወሳኝ ሀብት መሆኑን በማስቀደም ብሄራዊ ጥቅም ደግሞ አንድ ሀገር እንደ ሀገር ለመቀጠል መሠረት መሆኑን የነገሩን የብልፅግና ፓርቲ ሕዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒሥትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ናቸው:: ሚኒሥትሩ ስለ ብሄራዊ ጥቅም ያጋሩን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን 30ኛ ዓመቱን ባከበረበት ወቅት ነው::
እንደ ሚኒሥትሩ ገለጻ ሀገር በአንድነት ተባብሮ የሚኖር ሕዝብ፣ የተከለለ ድንበር ያለው፣ የጠንካራ እና ቅቡልነት ያለው መንግሥት ባለቤት፣ በሉዓላዊነቱ ተከብሮ የሚኖር ሕዝብ ማለት ነው:: ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ችግር ከገጠመው ሀገር እንደምትዛነፍ፣ ችግር ውስጥ እንደምትወድቅ ነው ያስረዱት:: በዚህም አገላለጽ መሠረት ሀገር የምትቀጥለው ብሄራዊ ጥቅሞቿን አውቃ፣ ቆጥራ እና አስከብራ ስትኖር ብቻ ነው::
ብሄራዊ ጥቅም ከዓለም አቀፍ ግንኙነት አንጻር የሀገር ግብ፣ ፍላጎት እና ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል:: የሀገርን ህልውና፣ ደኅንነት፣ ብልጽግና እና በዓለም የሀገራት አሰላለፍ ውስጥ ተገቢውን ክብር እና ቦታ ለማግኘት ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ ያሉ ሀገራት የሚከተሉት አቅጣጫ መሆኑንም አስረድተዋል:: ይህም ብሄራዊ ጥቅም የሀገርን የውስጥ እና የውጭ ፖሊሲ አቅጣጫን የሚወስን የሀገር ተከብሮ መኖሪያ መሠረት ነው:: ኢትዮጵያ በየጊዜው የምታወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና ዕቅዶችም ከብሄራዊ ጥቅሞቿ የሚቀዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል::
ብሄራዊ ጥቅም የፖለቲካ ፓርቲ ጉዳይ አይደለም፤ የአንድ ሀገር ሕዝብ እና ትውልድ አጀንዳ እንጂ ብለዋል ዶ/ር ቢቂላ:: ብሄራዊ ጥቅም ከፓርቲ፣ ከቡድን፣ ከመሪዎች፣ ከወቅታዊ መንግሥታት በላይ የሆነ ትውልድ እና ዘመን ተሻጋሪ የሀገር አጀንዳ መሆኑንም ሁሉም መገንዘብ እንደሚኖርበት ገልጸዋል::
ሀገራት ብሄራዊ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር አሉ የሚሏቸውን አማራጮች ሁሉ እንደሚጠቀሙ ዶ/ር ቢቂላ ገልጸዋል:: አንድ ሀገር ያለው ራሱ ለራሱ ነው በሚል እሳቤ የኅይል አማራጭን ከመጠቀም ጀምሮ ከሌሎች ሀገራት ጋር መተባበርን፣ መተጋገዝን፣ መደመርን፣ ሰጥቶ መቀበልን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል:: በሀገራት የእረዥም ጊዜ የርስ በርስ መሰናሰል እና ግንኙነት ውስጥ አዲስ እሳቤ ይፈጠራል፤ ሀገራት ሊዋሀዱ ይችላሉ፣ ለብሄራዊ ጥቅማቸው ሲሉ ወደ አንድ ሊመጡ ይችላሉ የሚለው እሳቤም ለብሄራዊ ጥቅማቸው መሳካት መውጫ መንገድ አድርገው እንደሚሠሩበት ነው የገለጹት::
ሀገራዊ ህልውና እና ደኅንነት፣ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና፣ ፖለቲካዊ አቅም እና ተጽእኖ ፈጣሪነት፣ የባህል ነጻነት እና ተጽእኖ ፈጣሪነት፣ የሕዝብ ማኅበራዊ ልማት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መሠረታዊ ግቦች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል::
የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት በማረጋገጥ በሰላም ወጥቶ የመግባት ነጻነትን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት የሚያስተጓጉል ማናንኛውም ኅይል ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም በተጻራሪ የቆመ ተደርጎ እንደሚወሰድም ጠቅሰዋል::
ራስን በኢኮኖሚ መቻል፣ ከድህነት እና ተረጂነት መውጣት፣ የኢኮኖሚ ብልጽግናን ማረጋገጥ የብሄራዊ ጥቅም አንዱ አካል መሆኑንም አንስተዋል:: ኢትዮጵያ በኢኮሚያዊ ብልጽግና የሚመጣባትን የትኛውንም ኀይል እንደማትታገስ ያለፉ እና በቀጣይ ሊከናወኑ በታሰቡ የልማት ሥራዎች ላይ የተቃጡ ውጫዊ እና ውስጣዊ ጫናዎች አስረጂ ናቸው:: ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውስጣዊ አቅሟን በማስተባበር እና በማቀናጀት ትልልቅ የልማት ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች:: ለአብነት ብሄራዊነት በተግባር የተገለጠበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለማስተጓጎል ለ14 ዓመታት የዘለቀው የውጭ ጫና ኢትዮጵያ በብሄራዊ ጥቅሟ ተጠቃሚ እንዳትሆን፣ ባላት ጸጋ ልክ ዕድገቷን አረጋግጣ በዓለም ዐደባባይ ከፍ ብላ እንዳትታይ ያለን ፍላጎት ያንጸባረቀ ተደርጎም ይወሰዳል::
የባህር በር ጥያቄውም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር አንደኛው አጀንዳ ሆኖ ከተነሳ ሰነባብቷል:: በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀይ ባህር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልካዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን አንስተዋል:: ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ያጣችበት መንገድ ውሳኔው በካቢኔ፣ በምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕዝበ ውሳኔ ለመሆኑ ማስረጃ እንዳልተገኘ ጠቁመዋል። በአጠቃላይ ቀይ ባሕርን ያጣንበት መንገድ የሕጋዊነት ችግር እንዳለበት ማሳያው ተቋማት አልገቡበትም፤ ካቤኒውም አያውቀውም፤ የባሕር በር የማግኘት ነገር የኅልውና ጉዳይ በመሆኑ በቀላሉ ሊታይ እንደማይገባም አንስተዋል።
በፖለቲካ፣ በአስተሳሰብ፣ በአይዲዮሎጂ፣ በምንከተለው የሥርዓተ መንግሥት አሠራር ተከብሮ እና ታፍሮ መኖርም የብሄራዊ ጥቅም አካል ነው:: ሀገር በባህሏ፣ በወጓ፣ በታሪኳ፣ በኪነ ጥበብ በዓለም ላይ ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር የባህል ነጻነት እና ተጽእኖ ፈጣሪነትንም በብሄራዊ ጥቅም መካተቱን ተመላክቷል::
የሕዝብ ማኅበራዊ ልማትም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መሠረታዊ ግብ ነው:: የተማረ፣ ጤናው የተጠበቅ፣ ማኅበራዊ ዋስትናው የተጠበቀ፣ የማይለምን፣ ያልተበተነ፣ አንድነቱ የተጠበቀ፣ ወንድማማችነቱ የተረጋገጠ ሕዝብ መገንባትን ያጠቃለለ የብሄራዊ ጥቅም መሠረታዊ ግብ ነው:: ዛሬ ላይ ትምህርትን የሚያስተጓጉል አካል በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም የመጣ ኀይል መሆኑን ገልጸዋል:: ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የሚከለክል፣ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ያደረገው ኀይል በግልጽ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም በተቃራኒ የቆመ ኅይል መሆኑን አንስተዋል:: ዛሬ ያልተማረ ትውልድ ነገ መብት እና ጥቅሙን አሳልፎ የሚሰጥ ትውልድ የሚፈጥር በመሆኑ ትምህርት እንዲጀመር መሥራት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ግብ መቆም ነው::
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ባለፉት ዘመናት ጉዳት ሲደርስባቸው እንደኖሩ ዶ/ር ቢቂላ ያስረዳሉ:: የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ያልተገራ ፍላጎት፣ የባንዳዎች ለዘመናት ለታሪካዊ ጠላቶች መገዛት፣ የኢትዮጵያ ጂኦ ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታ አለመጠናቀቅ፣ ድህነት እና ኋላቀርነት፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችንም ለጥቅሞቿ ዋነኛ ፈተናዎች በማድረግ አንስተዋል:: እነዚህም ሀገራዊ ደኅንነትን እና የሰላም ማጣትን፣ ድህነትን፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሰናከልን እና ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የሚገባትን ቁመና እንዳታገኝ ማድረጉን ነው የገለጹት::
ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሁሉም ሀገር የራሱ ብሔራዊ ጥቅም እና ብሔራዊ ስጋት እንዳለው ከሰሞኑ በተካሄደው የምክር ቤት ስብሰባ አንስተዋል:: እነዚህ ሁለት ጉዳዮች የሚበየኑት ሀገራቱ ባላቸው መረጃ እና ዕውቀት ልክ መሆኑንም ጠቁመዋል:: ሀገራት ይህንን መሠረት አድርገው ዛሬ ብሔራዊ ጥቅም ወይም ስጋት ያሉትን ጉዳይ ሊያሰፉ ወይም ሊያጠቡ እንደሚችሉ ነው ያስታወቁት:: ኢ- ርዕታዊ፣ ኢ- ፍትሐዊ፣ የበደል የመጨረሻው በደል የተፈጸመበት ሀገር ናትም ብለዋል፡
ዶ/ር ቢቂላ አሁን ያለው ትውልድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ፈተና የሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ለመፍትሔው መሥራት እንደሚገባም ሚኒሥትሩ ጠቁመዋል:: ለዚህም ውስጣዊ አንድነትን ማጽናት፣ ሰላም እና ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ባሕልን ማዘመን፣ የሃሳብ ፖለቲካን ማስፈን፣ ከፖለቲካ ኀይሎች ጋር ሰላማዊ አማራጭ መከተል፣ ሀገራዊ መግባትን መፍጠር፣ የጋራ ትርክትን በጋራ ጥቅም ላይ መገንባትን ለትውልዱ በመፍትሔነት ጠቁመዋል::
ምጣኔ ሃብታዊ አቅምን ማሳደግ፣ ከድህነት ነጻ የሆነ ትውልድ መፍጠር፣ የዲፕሎማሲያዊ አቅምን ማረጋገጥ፣ ሚዲያዎችም ብሄራዊ ጥቅም አጀንዳ እንዲያደርጉ መሥራት ለብሄራዊ ጥቅም መረጋገጥ መሠረት መሆናቸውን ጠቁመዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


