ኢትዮጵያ ብዙ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ፀጋ ያላት ሀገር ናት፡፡ ከተፈጥሮ ፀጋዎቿ መካከል ብዛት ያላቸው ሰንሰለታማ ተራሮች፣ አምባዎች፣ ሸለቆዎች፣ ሐይቆች፣ ወንዞች፣ ፏፏቴዎች፣ እንስሳት፣ እፅዋት እና አእዋፋት ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሲነሳ ደግሞ ቀድመው የሚጠቀሱ ድንቅ የመስህብ ሃብቶችን አቅፎ የያዘው አማራ ክልል ነው።
በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋ ከታደሉ እና በግንባር ቀደምትነት ከሚጎበኙ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች መካከል የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አንዱ ነው። ፓርኩ ኢትዮጵያ በዓለም ፊት ደምቃ ከምትታይባቸው ውብ የተፈጥሮ ፀጋዎች መካከል ቀዳሚዉ ነው። ተፈጥሮ የለገሰቻቸው ተራሮች እና በውቡ ሥፍራ የሚኖሩ ብርቅዬ እንስሳት አካባቢው በጎብኝዎች እንዲወደድ እና የዓለምን ቀልብ እንዲስብ አድርገውታል። በኢትዮጵያ ካሉ 13 ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ የስሜን ብሔራዊ ፓርክ ሲሆን በውስጡ ከአንድ ሺህ 200 በላይ የተለያዩ የእፅዋት ዝርያዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኘው ፓርኩ በኢትዮጵያ ከፍተኛውን የተራራ ጫፍ ራስ ደጀንን እና የዓለም ዐይኖችን የሚስቡ በውስጡ ብርቅዬ እንስሳትን አቅፎ ይዟል። ቀይ ቀበሮ እና ዋልያ ደግሞ ከቀዳሚዎቹ መካከል ናቸው። ፓርኩ በደባርቅ፣ በጃንአሞራ፣ በበየዳ፣ በጠለምት እና በአዳርቃይ ወረዳዎች የሚገኙ 38 ቀበሌዎችን ያካትታል።
ብዙዎች ባሕር እየሰነጠቁ፣ የብስ እያቋረጡ ወደ ዚያ ውብ ሥፍራ ተጉዘዋል፤ እየተጓዙም ነው። ባዩት ውብ ሥፍራ እና በውስጡ በሚገኙት ብርቅዬ እንስሳት፣ እጽዋት… ተደንቀዋል።
ፓርኩ በ1959 ዓ.ም በብሔራዊ ፓርክነት የተከለለ ሲሆን በ1962 ዓ.ም በትእዛዝ ቁጥር 59/62 ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ በ1970 ዓ.ም ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኒስኮ) በዓለም አቀፍ ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡
የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን አስደናቂ ካደረጉት መካከል አስገራሚ መልክዓ ምድራዊ አቀማምጡ፣ የብዝኃ ሕይወት ስብጥሩ እንዲሁም ተራሮቹን ፣ ሸለቆዎቹን እና ፏፏቴዎችን በአንድነት አስተሳስሮ መያዙ ነው። ፓርኩ በውስጡ የዋልያ አይቤክስ (Walia Ibex)፣ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ የሚኒሊክ ድኩላ እና ሌሎች ብርቅዬ የዱር እንስሳት መገኛም ነው።
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ “አማራ ድንቅ ምድር” በተሰኘው መጽሐፉ ፓርኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ አንጋፋ ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ መሆኑን አስፍሯል። የአካባቢውን ድንቅ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እና ብርቅዬ እንስሳትን ለማየትም በርካታ ጎብኝዎች ወደ ሥፍራው እንደሚሄዱ ጠቁሟል።
ይሁን እንጂ ፓርኩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ታዲያ በዚህ ድንቅ ሥፍራ የሚኖሩ ብርቅዬ እንስሳቱ እና በተፈጥሮ መስህቡ ላይ ተደጋጋሚ ችግሮች እየተፈጠሩ አሳሳቢ አድርጎታል። እነዚህ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ብርቅዬ እንስሳት ተደጋጋሚ ችግር እየገጠማቸው ነው። በተለይም ዋልያ አደጋ ስለተጋረጠበት ልዩ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው በተደጋጋሚ ተነስቷል። ባሁኑ ወቅት የዋልያ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ከ800 ወደ 300 አሽቆልቁሏል፡፡ ለዚህ ቁጥር መቀነስ ዋነኛ መንስኤው ደግሞ ሕገ ወጥ አደን መሆኑ ተረጋግጧል።
ዋልያ “አይቤክስ” በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኝ ብርቅዬ እንስሳ ነው። ዋልያ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በሕገ ወጥ አደን ምክንያት ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መሆኑን የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል። ከሰሞኑም በተፈጸመ ሕገ ወጥ አደን ዋልያዎች ተገድለዋል። ይህ ደግሞ በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አሳስቧል።
የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ እንዳሉት ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ቅርስ መዝገብ እንዲሰፍር ካደረጉት መስፈርቶች መካከል ብርቅዬ የዱር እንስሳትን እና እጽዋትን አቅፎ የያዘ በመሆኑ ነው። ከእነዚህ ብርቅዬ የዱር እንስሳት መካከል ዋልያ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ነው የተናገሩት። “የተፈጥሮ ሃብት የትውልድ ሃብት ነው!” ያሉት ኃላፊው “ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን በዝምታ መመልከት በታሪክም ሆነ በመጭው ትውልድ ተጠያቂ ያደርጋል!” በማለት ፓርኩ እና በውስጡ ያሉ ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
“ዋልያ በአንድ አካባቢ የሚኖር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዝርያው እንዳይጠፋ፤ በቅርብ ቀን የጸደቀው የዋልያ የጥበቃ ስልት እና የጥበቃ ዝርዝር ተግባራት ዕቅድ በ‘ጊዜ የለንም‘ መንፈስ በፍጥነት ሊተገበር ይገባዋል” ያሉት አቶ ተስፋሁን፤ የልማት ጥበቃ ስልት እና ተግባራት ለመፈጸም የበርካታ አጋር አካላትን ተሳትፎ ስለሚጠይቅ ለአፈጻጸሙ ድርሻ ያላቸው አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ጸጋዬ በበኩላቸው አብዛኞቹ ጎብኝዎች ወደ ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚመጡት ዋልያ እና ሌሎች ብርቅዬ እንስሳትን ለመጎብኘት መሆኑን ተናግረዋል። ከሰሞኑ በስስት በሚታዩት እና የጎብኝዎችን ቀልብ በሚስቡት ዋልያዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግድያ የአካባቢውን ፀጋ በማሳጣት የቱሪዝም ሃብቱን ስለሚጎዳው ሁሉም አካል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የዋልያ ቁጥር በአደን እና በሌሎች ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች እየተመናመነ መምጣቱ ቱሪዝሙን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳው ተናግረዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በዩኒስኮ ከተመዘገበበት መዝገብ ላይ ሊያስወጣው የሚችል አደጋ ይፈጥራል ነው ያሉት። የደረሰው ጉዳትም አስደንጋጭ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሕግ አስከባሪዎች በዚህ ተግባር የተሳተፉ አካላትን መያዛቸውን እና ለሕግ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፤ ይህም ተገቢ መሆኑን ነው ኃላፊው ያመላከቱት፡፡ በቀጣይ ጊዜያትም የዋልያዎችን ህልውና ለመጠበቅ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መተግበር እንዳለባቸው አንስተዋል።
በስሜን ተራራዎች ዙሪያ የሚገኝ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማኅበረሰብ ከቱሪዝም ተጠቃሚ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ፓርኩን እና በፓርኩ ውስጥ ያሉ ብርቅዬ እንስሳትን መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ “የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በተገቢው መጠበቅ የማንችል ከሆነ ብርቅዬ እንስሳትን ማጣታችን አይቀሬ ይሆናል”በማለትም ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በፓርኩ ዙሪያ ያሉ ወገኖች ወደ ፓርኩ ዘልቀው እንዳይገቡ፣ የአደን እንቅስቃሴን ለመከላከል ጠንክሮ መሥራቱን የተናገሩት አቶ መልካሙ፤ የተሠራው ሥራ ግን በቂ እና አጥጋቢ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡
በደርግ ዘመነ መንግሥት በነበረ ግጭት ዋልያ ቁጥሩ ቀንሶ እንደ ነበር ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡ ከዓመታት በኋላ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የቁጥጥር ሥራ መላላት መኖሩ እና ፓርኩን የሚያሥተዳድረው አካል ተገቢውን የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ ባለመሥራቱ ችግሩ መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡
ውብ የተፈጥሮ ገጽታን የተላበሰ፣ በውስጡም ብርቅዬ እንስሳትን የያዘ፣ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያስገኝ፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለሚፈጥረው ፓርክ ጥበቃ እና እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ ኃላፊው አሳስበዋል።
“ዋልያ ቀላል ነገር አይደለም፣ ዋልያ የሀገር ምልክት ነው፣ ዋልያ የብሔራዊ ቡድናችን መጠሪያ ነው፣ የበርካታ ድርጅቶች ስያሜ ነው። በመሆኑም ብሔራዊ ምልክት እና ውበት የሆነውን ዋልያ ከጥፋት ለመታደግ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ ይገባል” በማለት አቶ መልካሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም