የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም
ይህ ሰው በአንድ ወቅት የፕላኔታችን ቁጥር አንድ ቡጢኛ ነበር፤ በቡጢ ቀለበት ውስጥ እንደ አንበሳ ሲያገሳ ተጋጣሚዎቹን የሚያስበረግግ፤ ደፍረው ከገጠሙት ፋታ ሳይሰጥ ኩንታል በሚመዝን ቡጢው ከመሬት የሚደባልቅ፤ ፍርሀትን የማያውቅ፤ በአንድ ወቅት ዶናልድ ትራምፕን በንግድ አማካሪነት ቀጥሮ ያሠራ፤ በሀብት ከፍ ዝቅ ያለ ነው – ማይክ ጄራርድ ታይሰን።
በቅጽል ስሙ ብረቱ (the iron man) ወይም አውሬው ሲሉ ይጠሩታል። ከዓለማችን የምንጊዜም የከባድ ሚዛን ቡጢኞች መካከል ስሙ ከቀዳሚዎቹ ውስጥ ይቀመጣል። ማይክ ታይሰን እ.አ.አ በ1966 በአሜሪካ ኒውዮርክ ብሩክሊ ተወለደ። በአስከፊ ድህነት እና በወንጀል ተከቦ አደገ። ገና ከዐስር ዓመት እድሜው ጀምሮ ነበር ከቤት በመውጣት የጎዳና ህይወትን የተለማመደው።
በዚህ ወቅት በእድሜ ከሚበልጡት ወጣቶች ጋር መደባደብ እና ወንጀል መሥራትን የሙሉ ጊዜ ሥራው አደረገው። በኒውዮርክ ጎዳናዎች እያውደለደለ ድብድብን የዕለት ከዕለት ተግባሩ ያደረገው አውሬው ታይሰን በ13 ዓመቱ እስር ቤትን 38 ጊዜ ጎብኝቶታል። በዚህ መንገድ ህይወቱን ሲመራ የነበረው ታይሰን በመጨረሻ ግን ህይወቱን እስከ ወዲያኛው የሚቀይር ክስተት ተፈጠረ።
ያለርህራሄ ሰዎችን ጎዳና ላይ በቡጢ ሲዘርራቸው በተደጋጋሚ የተመለከተው የቀድሞው ቡጢኛ እና በኋላ ላይ አሰልጣኙ የሆነው ቦቢ ስትዋርት ማይክ ታይሰን የቡጢ ስፖርትን እንዲቀላቀል መንገድ ጠረገለት። በኒውዮርክ ጎዳና ከማፊያ፣ አደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪ እና ጎዳና ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ሲደባደብ ያደገው ታዳጊው ቡጢኛ ገንዘብ ተከፍሎት በቡጢ ቀለበት ውስጥ መፋለም ጀመረ። በ18 ዓመቱ ያከናወነውን የመጀመሪያውን የፕሮፌሽናል የቡጢ ውድድርም አሸነፈ።
በዓለም የቡጢ ካውንስል በየዓመቱ የሚዘጋጀውን የከባድ ሚዛን ሻምፒዮና በ1986 እ.አ.አ በ20 ዓመቱ በማሸነፍ አዲስ ክብረወሰን አስመዘገበ። በተለይ ደግሞ ከ1987 እስከ 1990 እ.አ.አ ባሉት ጥቂት ዓመታት በቡጢ ቀለበት ውስጥ እርሱን የሚያሸንፍ አንድም ቡጢኛ እንዳልነበር የፎክስ ስፖርት መረጃ አስነብቧል። በ1990 በፈረንጆች የአውሬውን ያለመሸነፍ ጉዞ ቡስተር ዳግላስ መግታቱን ታሪክ ያወሳል።
በቡጢው ዓለም ትልቅ ስም ያላቸውን የዓለም ቡጢኞች ማህበር (WBA)፣ የዓለም ቡጢ ካውንስል (WBC) እና ዓለም ዓቀፍ የቡጢ ፌዴሬሽን (IBF) ውድድሮች በአንድ የውድድር ዘመን በማሸነፍ የመጀመሪያው ቡጢኛ ሆኖ ስሙ በታሪክ መዝገብ ሰፍሯል። ብረቱ ሰው የቡጢ ቀለበት ውስጥ ምንም ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል ራሱ በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል።
ጨካኝ እና ርህራሄ እንደሌለውም ብዙዎች ይመሰክሩለታል። በ1997 እ.አ.አ ከኢቫንዳር ሆሊፊልድ ጋር በኔቫዳ ግዛት ድጋሚ በተገናኙበት መድረክ የስፖርቱ አፍቃሪ እስካሁን የማይዘነጋው ክስተት መፈጠሩ አይዘነጋም። ማይክ ታይሰን በሦስተኛው ዙር የተጋጣሚውን ሆሊፊልድ ቀኝ ጆሮ በጥርሱ በመንከስ ሰቅጣጭ ጉዳት አድርሶበታል። ይህ ትዕይንት ዛሬም ድረስ ከማይረሱ የስፖርት መጥፎ አጋጣሚዎች ውስጥ አንዱ ተደርጎ ይነሳል።
ማይክ ታይሰን በ20 ዓመታት የቡጢ ስፖርት ህይወቱ 57 ግጥሚያዎችን አድርጓል። ከእነዚህ ውስጥ 50ውን አሸንፏል፤ ካሸነፋቸው ፍልሚያዎች መካከል ደግሞ 44ቱን በዝረራ መሆኑን ግለ ታሪኩ ያስረዳል። በሰባቱ ደግሞ ተረቷል። የማይክ ታይሰን ጸሐይ መጥለቅ የጀመረችው በ2005 በፈረንጆች ነው። አይበገሬው ሰው ለመጨረሻ ጊዜ በቡጢ ቀለበት ከኬቨን ማክበርዲ ጋር ነበር ተፋልሞ የተሸነፈው። ከዚያ በኋላም ከቡጢ ስፖርት ለዓመታት ተሰናብቷል።
ማይክ ታይሰን በወጣትነት እድሜው ከሰው ልጆች ወጣ ያለ ባህሪ እንደነበረው ስለራሱ በተደጋጋሚ ምስክርነት ሲሰጥ ተደምጧል። ቡጢኛው ታይሰን በኒወርክ ከተማ በሚገኝ በአንድ የዙ ፓርክ (Zoo park) ሊጎበኝ ተገኝቷል። አንድ ግዙፍ ጉሬላ መሰሎችን አጣድፎ ሲደበድብ እና ሲያስጨነቃቸው ይመለከታል። ታዲያ ብረቱ ታይሰን ለዙ ፓርኩ ጠባቂዎች እና ኃላፊዎች ዐስር ሺህ ዶላር ልክፈልና ከበጥባጩ ጉሬላ ጋር ልደባደብ የሚል ጥያቄ ያነሳል፤ ጥያቄው ግን ተቀባይነት እንዳላገኝ ፎክስ ስፖርት ዘግቧል።
ታይሰን ሦስት የቤንጋል ነብሮች የነበሩት ሲሆን ለእነዚህ እንስሳት እንክብካቤ በወር 270 ሺህ ዶላር ያወጣ እንደነበረም ተሰምቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን በላስ ቬጋስ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆቴል አንድ ሚሊዬን ዶላር የያዘ የሊዊስ ቪተን ቦርሳ ረስቶ ወደ ኒወርክ ያቀናል። ይሁን እንጂ ገንዘቡን ከሆቴል ረስቶ መሄዱን ቢያስታውስም ያገኙት ሰዎች እስከሚደውሉለት ጠብቆ ገንዘቡን መረከቡንም መረጃዎች ወጥተዋል።
እ.አ.አ በ1990ዎች ታይሰን የምድራችን ከፍተኛ ተከፋይ ስፖርተኛ ነበር። በወቅቱ ጎበዝ ነጋዴ እና ጥሩ የንግድ አዕምሮ የነበረውን ሚሊዬነሩን ነጋዴ አሁን ላይ ድጋሚ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን የተመረጠውን ዶናልድ ትራምፕን የንግድ አማካሪ አድርጎ ቀጥሮት ነበር። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ በተለያዩ የውል ሰነዶች እና የንግድ ሥራዎች ላይ ታይሰንን ወክሎ ይፈራረም ነበር ተብሏል። 400 ሚሊዬን ዶላር ሀብት እንደነበረው ቢነገርም እ.አ.አ በ2003 ማይክ ታይሰን ከሀብት ማማ ወርዶ የ23 ሚሊዬን ዶላር ባለዕዳ መሆኑን አሳውቋል።
በ2010 በፈረንጆች ድጋሚ ወደ ሀብት ማማ ለመውጣት የአኒሜሽን የቲቪ ትዕይንት ጀመረ፤ “The Hangover” እና ሌሎች ፊልሞች እና ዶክመንተሪዎች ላይ በመሳተፍ ህይወቱን ማስተካከል ቻለ። እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር 2016 ጀምሮ በአንደንዛዥ እጽ ምርት በተለይ ካናቢስ በማምረት 160 ሚሊዬን ዶላር ሀብት ማካበት ችሏል። ከዚህ ኢንቨስትመንት በወር አንድ ሚሊዬን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያገኝ የፎክስ ስፖርት መረጃ አመልክቷል።
አውሬው አማሪካዊው ቡጢኛ ለመጨረሻ ጊዜ ቡጢ ቀለበት ውስጥ ሲገባ ባራክ ሁሴን ኦባማ የአሜሪካ ሴናተር ነበር፤ ዝነኞቹ የማህበራዊ የትስስር ገጾች ቲክ ታክ እና ኢንስታግራምም አልነበሩም። ታዋቂው ዩቲዩበር እና ቡጢኛ ጄክ ፖውል ደግሞ የስምንት ዓመት ልጅ ነበር። ከ19 ዓመታት በኋላ ወደ ቡጢ ቀለበት ፊቱን በማዞር ድራማ ነው የተባለውን ፍልሚያ ከዩቲዩበር እና ቡጢኛው ጄክ ፓውል ጋር በቅርቡ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
በ58 ዓመቱ ማይክ ታይሰን እና በ27 ዓመቱ ጄክ ፓወል መካከል የተደረገው ፍልሚያ በአሜሪካ ቴክሳስ ነበር የተከናወነው። ቡጢኞቹ ለ16 ያህል ደቂቃ በቡጢ ቀለበት ውስጥ ተፋልመዋል።ለእርጅና እጅ የሰጠው ማይክ ታይሰን በተጋጣሚው ብልጫ ተወስዶበት ታይቷል።
አዛውንቱ ማይክ ታይሰን ለጄክ ፓወል እጅ ሰጥቷል። በአጠቃላይ 18 ቡጢዎችን ብቻ በጄክ ፓወል ፊት ላይ ሰንዝሯል። በአንፃሩ የ27 ዓመቱ ቡጢኛ 78 ቡጢዎችን በማይክ ታይሰን ፊት አስርፏል። ስምንት ዙር በፈጀው ድብድብ የ27 ዓመቱ ዩቲዩበር እና ቡጢኛው ጄክ ፓወል አሸንፏል። ከዚህ ውድድር ጄክ ፓወል 40 ሚሊዬን ዶላር አግኝቷል። ማይክ ታይሰን ደግሞ 20 ሚሊዬን ዶላር ወደ ካዝናው አስገብቷል።
ፍልሚያው ግን በኔትፍሊክስ የተዘጋጀ ድራማ መሆኑን የስፖርት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ይህን መረጃ ያወጡ በርካታ ጋዜጦች ዙሩ ምን መምሰል እንዳለበት እና በየዙሩ የሚፈጠሩ ክስተቶች ቀድመው በተውኔት መልክ ተዘጋጅተዋል ባይ ናቸው። ያም ሆነ ይህ ግን ከ250 ዶላር እስከ 350 ሺህ ዶላር ትኬት ገዝተው በቀጥታ ውድድሩን የተመለከቱት የስፖርቱ አፍቃሪያን ጠንካራ ፉክክር ባለማየታቸው ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
የማይክ ታይሰን እና የጄክ ፓወል ግጥሚያ “የገንዘብ ፍልሚያ” እንደሆነ ብዙዎች ተናግረዋል። ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት ታላላቅ የገንዘብ ፍልሚያዎች መደረጋቸውን አልጀዚራ አስነብቧል። መረጃው በ2017 በፈረንጆች ሜይዌዘር እና ኮነር ማክግሪገር ያደረጉትን ግጥሚያ ያስታውሰናል። ያኔ አሸናፊው ሜይዌዘር 100 ሚሊዬን ዶላር ሲያገኝ ማክግሪገርም 30 ሚሊዬን ዶላር ወደ ካዝናው አስገብቷል።
በታይሰን እና ጄክ ፓወል መካከል የተካሄደው ግጥሚያ ድራማም ይሁን ትክክለኛ የስፖርት እና የመዝናኛውን ዓለም ግን እንደገና ማንቃቱን ብዙዎቹ ጋዜጦች አልሸሸጉም። በኔትፍሊክስ የተለቀቀው ይህ ግጥሚያ ከ277 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል። ይህም በብዛት ከታዩ የስፖርት ዝግጅቶች መካከል 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም