የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም ገብረእየሱስ፣ የአሜሪካ የህክምና የበላይ ኃላፊ (Surgeon General) ዶ/ር ቪቬክ ሙርቲ እና የአፍሪካ ህብረት የወጣቶች ተወካይ ቺዶ ምፐምባ ለአልጀዚራ በጋራ በሰጡት መግለጫ ብቸኝነት ከግል ስሜት የዘለለ እንደ ማጨስ ሁሉ ለጤና አደገኛ የሆነ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ጤና ስጋት መሆኑን አስታውቀዋል።
እነዚህ ከፍተኛ የጤና መሪዎች ብቸኝነትን እንደ ግለሰብ ችግር ብቻ ከመመልከት ወጥቶ መንስኤዎቹን እና መፍትሔዎቹን በማህበራዊና ፖለቲካዊ መነጽር መፈተሽ እንደሚገባ አሳስበዋል:: በዚሁ ዙሪያ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የብቸኝነት የጤና ጉዳት በቀን 15 ሲጋራ ከማጨስ ጋር የሚስተካከል ነው፡፡ ለልብ ህመም፣ ለስትሮክ፣ ለአእምሮ መዛባት (dementia) እና ለሌሎች በርካታ በሽታዎች ተጋላጭነትን በእጅጉ ይጨምራል። ብቸኝነት ለከፍተኛ ጭንቀት (anxiety) እና ለድብርት (depression) ዋነኛ መንስኤ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በኢኮኖሚ ጫና ሰዎች ለኑሮ በሚያደርጉት ሩጫ ምክንያት ለማህበራዊ ሕይወት የሚሰጡት ጊዜ መቀነስ፣ እንደ ቤተ-መጻሕፍት እና የማህበረሰብ ማዕከላት ያሉ ሰዎች የሚገናኙባቸው ቦታዎች በመንግሥታት የበጀት ቅነሳ መዳከማቸውም አንዱ ተጽዕኖ መሆኑን ገልጸዋል። ሌላው ደግሞ የከተሞች አሰፋፈር ዘመናዊ የከተማ ፕላኖች ከጎረቤቶቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከሚያጠናክሩ ይልቅ ግለሰቦችን የሚያገልሉ ሆነው መሠራታቸው እንደሆነም ተመላክቷል። የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ደግሞ እውነተኛውን የሰው ለሰው ግንኙነት በመተካት የይስሙላ ቅርርብን በመፍጠር የብቸኝነት ስሜትን ማባባሳቸው በጥናቱ እንደ ምክንያት ተጠቅሷል።
ከዚህ ዓለም አቀፍ ችግር በመነሳት በተለያዩ ምክንያቶች እየተስፋፋ ስለመጣው የብቸኝነት ችግር ለመውጣት ምን መደረግ እንደሚገባው በኵር በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይኮሎጂ መምህር አቶ አውግቸው ሽመላሽን አነጋግራለች፡፡
ብቸኝነት ምንድን ነው?
አቶ አውግቸው እንደሚሉት ብቸኝነት በቀላሉ ሲገለፅ አንድ ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያቆራኙት ማህበራዊ መስተጋብሮች ወይም የስሜት ድጋፎች በተገቢው መንገድ እንዳልተሟሉ ሲሰማው /ሲያስብ/ የሚፈጠር ራስን የመነጠል ተግባር ነው። ብቸኝነት (Loneliness) የሰው ልጅ በውስጡ የሚያስተውለው የመንፈሳዊ እና የስሜታዊ ግለኝነት ነው። ይህም ማለት ብቸኝነት የየግለሰቡ አረዳድ እና ግንዛቤ ሲሆን አንድ ግለሰብ በብዙ ሰዎች መካከል እንኳ ሆኖ ብቸኝነት ሊሰማው ይችላል። ይህም ማለት ብቸኝነት ማለት የሰው ልጅ በሚፈልገው የስሜት ልክ እና በሚያገኘው እውነታ መካከል ያለው ልዩነት ነው።
የብቸኝነት መንስኤዎች
ብቸኝነት ከብዙ ምክንያቶች የሚመነጭ ነው። ለአብነት በራስ የመተማመን ችግር ፣ ለራስ ዝቅተኛ ግምት መስጠት፣ ራስንም ሆነ ሌሎችን ሰዎች በተገቢው መንገድ አለመረዳት፣ ከልክ በላይ መጨነቅ፣ የሕይወት ለውጦች (ሥራ መቀየር ወይም መቋረጥ) ፣ የቤተሰብ ድጋፍ እጥረት፣ የማህበራዊ መስተጋብር እጥረት፣ መድሎ እና መገለል፣ ከአብሮነት ወደ ግላዊነት የሚያመራ የከተሜነት ልምድ፣ ከፍተኛ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ምክንያት እውነተኛ ግንኙነት መጥፋት… (virtual connectedness but real isolation) ዋና መንስኤ ናቸው፡፡ ባለሙያው እንደሚሉት ታዲያ ከምክንያቶቹ በአንዱ የመጣው ይሄ የብቸኝነት ስሜት ደግሞ በጤና ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ይኖራል፡፡
የብቸኝነት ስሜት በአእምሮ ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት
ማንኛውም ሰው ስር የሰደደ የብቸኝነት ስሜት (Chronic Loneliness) በአእምሮ ጤና ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ ከፍተኛ ነው። ከብዙ በጥቂቱ ከፍተኛ ጭንቀት ያመጣል፣ የእንቅልፍ መዛባትን ይፈጥራል፣ እንቅስቃሴ ያላቸው የስሜት ክፍሎች ( amygdala and hippocampus) በብቸኝነት በጣም ይታወካሉ፣ በዚህም ለምሳሌ የውስጣዊ ሆርሞን የኮርቲሶል /Cortisol/ ለውጦች ያመጣል፤ ይህም የአእምሮና የሰውነት ጤናን ያዛባል፣ ማህበራዊ መስተጋብርን ይቀንሳል፣ ከፍተኛ የድባቴ ስሜት ያመጣል፣ ሰዎች ራሳቸውን እንዲጠሉ እና ራስን የማጥፋት ሙከራ እንዲያደረጉ ይገፋፋቸዋል፣ በመጨረሻም ራስን ለማጥፋት ይዳርጋል፡፡ ለዚህ መፍትሔው ምን መሆን ይገባዋል? ለሚለው ደግሞ የባለሙያው ምክር ማህበራዊ መስተጋብርን ማሳደግ ነው፡፡
ማህበራዊ መስተጋብር ለአእምሮ ጤና
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ማህበራዊ መስተጋብር (Social Interaction) በዚህ በኑሮ ሂደት በጋራ የሚኖረን ግንኙነት የአእምሮ ጤናን በብዙ መንገዶች ያጠናክራል። ለምሳሌ ስሜታዊ ድጋፍ (Emotional Support) በተለይም ከቤተሰብ እና ጓደኛ ጋር ያለ መስተጋብር የጭንቀት እና ድባቴ መጠንን ይቀንሳል፣ ሰዎች ላይ ተስፋ እና እምነት ይጨምራል፤ የኔነት ስሜትን ያጎለብታል፤ ከሰዎች ጋር የሚኖረን የጋራ ስሜት /አብሮነት/ ለእውቀት መዳበር ጉልህ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ መሥፋፋት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ቢኖሩትም ግለኝነትን የማስፋት እና ማህበራዊ መስተጋብርን የመቀነስ ችግርን እንደሚያስከትል ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡ ይህም በብዙ ሰዎች እየሰፋ የመጣው ከልክ በላይ የሆነ ጊዜን ማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ማሳለፍ በግለሰቦች መካከል የስሜት መቆራኜትን ይቀንሳል፡፡ አይነተኛ እና የማይወሰን ስሜታዊ እጥረት ይፈጥራል፣ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ በርካታ ማህበራዊ ግንኙነት እና ጓደኛ ቢኖራቸውም በእውነታው ዓለም ግን በከፍተኛ ብቸኝነት ይዋጣሉ፡፤ ማህበራዊ ሚዲያ የእውነተኛ መስተጋብርን በመቀነስ የአብሮነት መንፈስን ይጎዳል። የግለሰብ እና የማህበረሰብ እሴቶችን በመሸርሸርም ብቸኝነትን ያመጣል።
ብቸኝነትን ለማስወገድም ማህበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር በቤተሰብ፣ በጓደኛ እና በማህበራዊ ቡድኖች ውስጥ መተዋወቅ፣ በራስ መተማመን፣ ለራስ ተገቢውን ክብርና ግምት መስጠት፣ ራስንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን በተገቢው መንገድ መረዳት፣ ስፖርታዊ የእንቅስቃሴ ቡድን መቀላቀል፣ በእምነት ተቋማት ባሉ መርሃ-ግብሮች መሳተፍ፣ ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም ከሰዎች ጋር ተሰባስቦ ለመጨዋወት ትኩረት መስጠት የመፍትሔ መንገዶች መሆናቸውን ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡
መረጃ
ብቸኝነት የሚያስከትላቸው የጤና ጠንቆች
የሰውነት በሽታ መከላከል አቅም መዳከም
ደም ግፊት እንዲጨምር ያደርጋ
አካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማዘውተርን ያስከትላል
የአእምሮ ፍጥነት ይቀንሳል
ሱስ ውስጥ እንዲገባ መንገድ ይፈጥራል (ለማጨስ፣ለአልኮል)
የልብ በሽታ ያስከትላል
ለድብርት ይዳርጋል
ክብደት መጨመር
ለእንቅልፍ እጦት ይዳርጋል
አልኮል እና እጾች ብቸኝነትን ለመቀነስ ከሰው ጋር የሚቀራረቡበትን ጊዜ ለመፍጠር ይሞክሩ። ቼዝ አብሮ መጫወት፣ የመጸሐፍ ክበብ መቀላቀል፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን መጀመር… ከሰው ጋር ይበልጥ እንዲተዋወቁ ያደርጋሉ። እራስዎን ይንከባከቡ። አካል ብቃት እንቅስቃሴን ማዘውተር፣ በጊዜ መተኛት እና ተመጣጣኝ ምግብ መመገብ የብቸኝነትን ስሜት ይቀንሳሉ።
ምንጭ-ዶክተር አለ
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


