ብዊንዲ ብሔራዊ ፓርክ

0
268

የብዊንዲ ጥቅጥቅ ደን ብሔራዊ ፓርክ በኡጋንዳ ኪሶሮ፣ ካባሌ እና ካኑንጉ በተሰኙ ወረዳዎች  ነው የሚገኘው::

ጥቅጥቅ ደኑ ከ1,160 እስከ 2,607 ሜትር ከፍታ ባለው የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ በስተደቡብ ምእራብ ነው የተከለለው:: አጠቃላይ ስፋቱ 327 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል:: በመልካዓምድራዊ አቀማመጡ ገደላማ፣ አንሸራታች ሸለቆዎች ወይም አቀበት እና ቁልቁለትን አካቶ ይዟል::

“ብዊንዲ” የሚለው ቃል በኪንያርዋንዳ  “ጨለማ” ወይም “ጥቅጥቅ” በአገርኛው ቋንቋ “ሉኪጋ” ብዊንዲ “የማይቻል” ማለት መሆኑ ነው የተገለፀው:: በደኑ ውስጥ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ከመሆኑ አንፃር የተሰጠው ስያሜ መሆኑን ልብ ይሏል:: በደኑ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ጀብደኛ  መሆን ወይም ድፍረት እና የአካል ብቃትን አጣምሮ መያዝንም ይጠይቃል::

ፓርኩ በ1942 እ.አ.አ ብዊንዲ ጥቅጥቅ ደን በሚል ታውቆ በጋዜጣ ለህትመት በቅቷል:: ከሃምሳ ዓመታት  በኋላም ወደ ብሔራዊ ፓርክነት አድጓል::

ደኑ በዓለማችን ከሚገኙ 700 ከሚደርሱ ጐሬላዎች ግማሽ ያህሉን ማለትም በቁጥር 320 ይገኙበታል ተብሎ ተገምቷል:: ከተጠቀሱት በተጨማሪ ዝንጀሮ፣ ጦጣ እና ቺምፓንዚ ዝርያዎች መኖራቸው ተረጋግጧል::

በፓርኩ 347 የዓእዋፍ እንዲሁም 200 የተለያዩ ቀለማት ያላቸው የቢራቢሮ ዝርያዎች መገኘታቸውም ተዘግቧል::

እፅዋትን በተመለከተም በስፋቱ በአህጉሪቱ ተጠቃሽ የሆነው ጥቅጥቅ ደኑ 324 ዝርያዎች እንደሚገኙበት ተጠቁሟል:: ከተጠቀሱት 324ቱ አስሩ በዚያው በኡጋንዳ ፓርክ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ መሆናቸውም ነው የተጠቀሰው::

ፓርኩ በ1994 እ.አ.አ በተባበሩት መነግሥታት የአካባቢ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት ተፈላጊ፣ ተመራጭ ስነ ምህዳርነቱ ተረጋግጦ  ቀደም ብሎ በተለካው ስፋት ላይ 10 ኪሎ ሜትር እንዲካተት እና የፓርኩ ክልል እንዲጨምር ተደርጓል:: ፓርኩ በአማካይ በዓመት 2,390 ሚሊ ሜትር የተለካ ዝናብ ያገኛል::

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ብዊንዲ  ናሽናል ፓርክ፣ ደብሊው ኤች ሲ ዶት ኦርግ፣ ብዊንዲ ፎረስት ናሽናል ፓርክ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ጥቅምት 18  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here