የተወለዱት በአዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ ስጋዲ በተባለ ቀበሌ ነው:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በስጋዲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቻግኒ እና ዳንግላ ከተሞች ተምረዋል:: በህግ ትምህርት ዲፕሎማቸውን ከዚያም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል- ጠበቃ አዳነ ታረቀኝ:: ጠበቃ አዳነ ታረቀኝ በህግ ሙያቸው የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት ይታወቃሉ፤ ደራሲ እና ገጣሚም ናቸው::
መጻሕፍትን ሰዎች እንዲያነቡ በማድረግም ይታወቃሉ:: የአራት ወንዶች እና የሁለት ሴቶች አባት ከሆኑት ከጠበቃ አዳነ ታረቀኝ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ!
ወደ ሕግ ትምህርት እና ሥራ እንዴት ገቡ?
ወላጆቼ በልጅነቴ ነው የሞቱት፤ እነሱን ካጣሁ በኋላ ብዙ ችግር አሳልፌያለሁ፤ በተለይ ራሴን ለመቻል በማደርገው ጥረት እየሠራሁ ነበር ትምህርቴን እማር የነበረው:: ሁለተኛ ደረጃ እየተማርኩ ጎን ለጎን ፍርድ ቤት በደጋፊ ሠራተኛነት ተቀጠርኩ፤ ለዚህም ደግሞ የተለያዩ የሕግ መጽሐፎችን ማንበቤ ጠቅሞኛል::
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከጨርሼ የኮሌጅ መግቢያ ውጤት አመጣሁ:: የሕግ ትምህርት ጋር ቀረቤታ ስላለኝ ወደዛው ተቀላቀልኩ:: ሙያውን በዋናነት የመረጥኩበት ትልቁ ነገር ሌሎችን የምትረዳበት በመሆኑ ነው:: የመማር የመጨረሻው ግቡ ሌሎችን ማገልገል ነው:: በጥብቅናው ዓለም ደግሞ ዋናው ነገር ከማገልገል አልፎ ሰዎችን መርዳት ነው:: ገንዘብ ከማግኘቱ እና ከመጠቀም በላይ ለሰዎች ፍትህ ማስገኘት ስትችል ትልቁ የአዕምሮ እርካታ ይሄው ነው:: አብዛኛው ሕዝባችን ችግረኛ ነው፤ ፍርድ ቤት ቀርቦ የሚያስፈልገውን አሟልቶ ለማቅረብ አቅም እና እውቀት ይፈትነዋል፤ በመሆኑም እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማገዝ አላማዬ አድርጌያለሁ፡፡
የሕግ አገልግሎት በክልላችን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
ሕግ ሲባል አንድ ተቋም ሳይሆን ብዙ አካላትን የያዘ ነው:: የጥብቅናው ዓለም ራሱን ችሎ አንድ ተቋም ነው፤ ፍርድ ቤት ደግሞ ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሌላ የራሱ መዋቅር አለው:: ፍትሕ ቢሮም የራሱ መዋቅር አለው፡፡
አገልግሎት አሰጣጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ያለው ቢሆንም የተገልጋዩ እርካታ አለ ወይ? ተብሎ ሲጠየቅ ግን ችግር አለ:: ከጥብቅና ሙያው ጋር ስንመጣ ደግሞ ለማኅበረሰቡ ፍትህን ለማሰጠት የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚንቀሳቀሱም አሉ:: እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የመጀመሪያው ትግል የሚጀመረው ከራስ ነው::እውነትን ይዞ መቆም ያስፈልጋል:: አለፍ ሲባል ከሌሎች ተቋማት ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊኖር ይገባል:: ከሙስና፣ ከጎጠኝነት እና ከመጠቃቀም መራቅ ያስፈልጋል:: ይህ ካልሆነ የፍትህ መጓደል አይቀርም:: ይህን ለማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ ነው:: ዳኞች፣ ጠበቆች እና ሌሎች የሕግ አካላት ነጻ እና ገለልተኛ መሆን አለባቸው::ይህን በማድረጋችን የምናጣው ነገር የለም::የኑሮውን ክብደት ለማቅለልም መንግሥት አቅም በፈቀደ በጀት መድቦ ማስተካከል አለበት፡፡
ብዙ ሰው ፍትህን በገንዝብ ማግኘት እንደሚችል በአስተሳሰቡ ተቀርጿል::ተገቢውን ማስረጃ አቅርቦ ፍትህን ከማግኘት ይልቅ ገንዘብ ከፍሎ አንዱ ካንዱ ተነካክቶ ጉዳዩ እንደሚፈጸም ያምናል:: ይህ የተሳሳተ ነገር ነው:: መቅረትም አለበት:: ሰው ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ ትክክለኛ ማስረጃ ይዞ ቀርቦ ፍትህን ማግኘት እችላለሁ ብሎ ማመን አለበት::
የታተመ የግጥም መድብል እና ሌሎች ሊታተሙ የተዘጋጁ መጽሕፎች አሉዎት፤ ስነ ጽሑፍ እንዴት እንደጀመሩ እና ስለመጽሐፎችዎ ይንገሩን?
ተማሪ እያለሁ ስነጽሑፍ እሞክር ነበር፤ ስነጽሑፍ ላይ ትልቁ ነገር ውስጥ ያለውን ማውጣት እና መግለጽ ነው:: ለእኔ ከሽያጭ እና ከገበያ ጋር የሚያያዝ አይደለም:: ፈጣሪ የሰጠህን አቅም ማውጣት ነው:: ቀደም ሲል አዲስ ዘመን እና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ እጽፍ ነበር:: አዲስ ዘመን ላይ አንዴ የጻፍኩት ነገር አሳስሮኛል፡፡
መጀመሪያ ያሳተምኩት “ሀገሬ ወዴት ነሽ” የሚል የግጥም መድብል ነው:: በግጥሞቼ በአብዛኛው ሀገራዊ ጉዳዮችን ነው የዳሰስኩት:: እኔ አንድ ተራ ዜጋም ብሆን ሀገር ሲባል ትልቅ ቦታ ነው ያለኝ:: ያለ ሀገር መኖር እንደማልችል ነው የምገነዘበው:: ኢትዮጵያ ማን እንደሆነች ታሪኳን መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ አንብቤ አውቄያታለሁ:: ከአወካት ሀገርክን እንዴት አትወዳትም? ስለዚህ ሀገራዊ ግጥሞቼ ሰፋ ያለውን ድርሻ ወስደዋል፡፡
ሌላው ደግሞ ሀገራዊ ስሜት እየተቀዛቀዘ መጥቷል:: በተለይ ከኢህአዴግ መንግሥት ወዲህ ክልሎች በመመስረታቸው ይመስለኛል ሀገራዊው ስሜት እየደበዘዘ መጥቷል:: ይህ ጭራሽ እንዳይጠፋ እና ዳግም ኢትዮጵያዊ ስሜት እንዲያብብ ነው ግጥሞቼ ሀገርን የሚመለከቱት፡፡
ቤትህ ውስጥ ቆሻሻ ብታይ ታጸዳዋለህ እንጂ ዝም አትለውም:: ለሀገር ያለኝ ፍቅር በዚህ የሚለካ ነው:: ልጆቼን በዚህ መንገድ ነው የማስተምራቸው:: ለመጣላትም ለመታረቅም ሀገር ያስፈልጋል፤ “ማነህ? ስትባል እኔ ነኝ! የማትልበት ቦታ ላይ አትገኝ ወይም አትቁም” የሚል ሀገራዊ አባባል አለ:: ኢትዮጵያዊነት ትልቅ ክብር አለው፡፡
በቀጣይ “የእናት ምክሮች” እና “አልጸነስም” የሚሉ መጽሐፎች ይወጣሉ:: ለትውልዱ ምክር እና ታሪክን የሚያስተምሩ ናቸው፡፡
እርስዎ ሌሎች እንዲያነቡ መጻሕፍትን ያቀርባሉ፤ ተንቀሳቃሽ ቤተ መጻሕፍት የሚል ቅጽል ስያሜም ተሰጥቶዎት ነበር፤ ይህን እንዴት ጀመሩ?
ማንበብ ብዙ ጊዜ የሚጀመረው ከትምህርት ቤት ነው:: መምህራን አንብቡ ይሉናል፤ በዚህ ምክንያት ማግኘት የምችለውን ሁሉ አናነባለን: :ከፍ እያልኩ ስመጣ መጽሐፍ ከሕይወት ጋር የተያያዘ መሆኑን ተረዳሁ:: እንደ መርህ ያደረኩትም ማንም ሰው ለመኖር እንደሚበላው ሁሉ ለአምሯችንም መጽሐፍ ማንበብ የዚያኑ ያክል ጠቃሚ ነው:: ሕይወትን እንደ ዛፍ የሚደግፍ ማንበብ ነው ብየ ነው የማምነው፡፡
ተንቀሳቃሽ ቤተ መጻሕፍት የሚለው ስያሜ የወጣልኝ ዳንግላ እያለሁ ጀምሮ ነው::ለራሴ ገዝቼ የማነባቸውን መጽሐፎች ሌሎችም ማንበብ እንዳለባቸው ተረዳሁ:: በተለይ ሕይወታቸውን መቀየር ያለባቸውን ሰዎች ሳገኝ ይሄን መጽሐፍ አንብቡ እያልኩ እሰጥ ነበር::መጽሐፉን አንብበው ሕይወታቸውን ሲቀይሩ ሳይ እጅግ በጣም እደሰታለሁ፤ የሚጠበቀውም መልካም ውጤት እሱ ነው:: በተለይ ተምረው ሥራ ማግኘት ያልቻሉ ሰዎች የሰጠኋቸውን መጻሐፎች አንብበው በግላቸው ውጤታማ ሲሆኑ ያስደስታል፡፡
ወደ ባሕር ዳር የመጣሁት ዳንግላ እየሠራሁ የነበረውን የመንግሥት ሥራ ለቅቄ በግሌ የሕግ ጥብቅና ለመጀመር በመወሰኔ ነበር:: ቤቴ እና በቢሮዬ ውስጥ ያሉ መጻሕፍትን ለሰዎች አስነብባለሁ:: በተለይ ከታሪክ፣ ከሕግ እንዲሁም ራስን ከማስተማር እና ከመቀየር ጋር የተያያዙ መጽሐፎችን አስነብባለሁ፡፡
የቀድሞውን እና የአሁኑን የንባብ ባሕል እንዴት ያነጻጽሩታል?
ቀደም ባለው ጊዜ አንባቢ ትውልድ ነበር፤ ይህን ስል አሁን ያለው ሁሉም አያነብም እያልኩ አይደለም:: ከንባብ ባሕል አንጻር እውነቱን ለመናገር አሁን እጅግ ተጎድተናል:: እኔ እንደማስበው አንዱ የጎዳን ነገር ቴክኖሎጂን ያላግባብ መጠቀም ይመስለኛል:: ረጅሙን እና ሙሉውን ከማንበብ ይልቅ አጫጭር እና የተቆነጸለ ነገር መፈለግ ጀምረናል:: ወደ ጥልቁ ገብቶ ከመማር እና ከመመራመር ይልቅ በትንሽ ነገር መርካት ጀምረናል፡፡
የቤተ መጻሕፍት ቁጥርም ከሕዝቡ አንጻር ትንሽ ነው፤ በየሰፈሩ የሚያስነብቡ ሰዎችም እየጠፉ ነው::መጻሕፍት ገዝቶ ለማንበብም ዋጋቸው ውድ ነው:: የሚፈለጉ እና ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ መጻሕፍትም የሉም፤ ለገበያ ፍጆታ የሚሆኑ ናቸው አብዛኞቹ::
አንባቢው ረጂም ነገር ለማንበብ ትዕግስቱም ጊዜውም የለውም:: ነገር ግን በቀን ቢያንስ ከ40 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ለንባብ መስጠት ብንችል ከፍተኛ ለውጥ እናመጣለን:: ከእንቅልፍ ጊዜያችን ቀንሰን ለንባብ ብናደርግ ጥሩ ነው የሚል ሀሳብ አለኝ:: ኑሮን ለመግፋት የሚያባክን እና የሚያሯሩጥ ነገር ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ጊዜን በአግባቡ መመደብ ወሳኝ ነው፡፡
ልጆችዎን በስነ ምግባር አሳድገው ለቁም ነገር አብቅተዋል፤ ይሄን ያደረጉበትን መንገድ በአጭሩ ቢነግሩን?
ልጆች ሥነ ምግባራቸው የሚቀረጸው ከቤት ነው::ወላጅ ልጆቹን ዛሬ ምን ተማራችሁ? ብሎ መጠየቅ አለበት:: ልጆቻቸውን ከጌሞች፣ ከማኅበራዊ መገናኛዎች ማራቅ አለባቸው::ልጆች መፍጠር እንዳይችሉ የሚያደነዝዙ ናቸው:: ለልጆቼ ለትምህርት ብቻ ሲሆን በተመጠነ ሰዓት በእኔ እገዛ አሳያቸዋለሁ:: ከዚህ ውጪ ለልጆች የበዛ ነጻነትም የበዛ ገደብም አያስፈልግም፤ ሲያጠፉ በተገቢው መንገድ መገሰጽ አለባቸው፤ ከአደጉ እና መረን ከለቀቁ በኋላ መመለሱ ከባድ ነው፡፡
ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም