ቦክሲንግ ዴይ ምንድነው? ቦክሲንግ ዴይን በ1833 እ.አ.አ ቻርለስ ዲክንስ የተባለ ግለሰብ ነው ያስተዋወቀው። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ባለፀጋ ቤተሰቦች በገና ማግስት (በፈረንጆች ታህሳስ 26 ቀን) ለአገልጋያቸው የተጠቀለለ ስጦታ የሚሰጡበት ቀን ነው። እነዚህ አገልጋዮች ደግሞ ስጦታቸውን ይዘው ቤተሰቦቻቸውን የሚጠይቁበት ነው። በጊዜ ሂደት ይህ ቀን የሕዝብ በዓል ሆኖ መከበር ጀመረ።
ብዙ እግር ኳስ ደጋፊ ቦክሲንግ ዴይ (Boxing Day) የእግር ኳስ ጨዋታ የሚደረግበት መርሀ ግብር እንደሆነ ነው የሚገነዘቡት። በእርግጥ የውድድር መርሀ ግብር ከሆነ ብዙ ዓመታትን አስቆጥሯል። አሁን ደግሞ አድጎ ወደ ባህል ተሸጋግሯል። በአውሮፓ ባሉ ሌሎች ታላላቅ ሊጎች ተጫዋቾች ከገና እና አዲስ ዓመት በዓል ባለፈ ይህ ወቅት የእረፍት ቀን ሲሆን በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከበዓል ባለፈ የጨዋታ ቀን ነው።
ቦክሲንግ ዴይ በእንግሊዝ ከፈረንጆች የገና በዓል ማግስት የሚከበር በዓል ሲሆን በአሜሪካ ደግሞ “የባንክ በዓል” ብለው ይጠሩታል። ያ ማለት ብሄራዊ በዓል እንደ ማለት ነው። በዚህ በዓል አብዛኞች ሱቆች፣ ድርጅቶች ይዘጋሉ፤ ሠራተኞችም እረፍት ይሆናሉ። ለበዓሉ ማድመቂያም እግር ኳስን ጨምሮ ልዩ ልዩ ጨዋታዎች ይከናወናሉ።
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልኩ ከተደራጀበት ከ1992/93 እ.አ.አ በኋላ በቦክሲንግ ዴይ ( ታህሳስ 26 በፈረንጆች) ማንቸስተር ዩናይትድ ብዙ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ባለ ክብረ ወሰን ነው። እስካሁንም 21 ጨዋታዎችን አሸንፏል። 183 ግቦችን ደግሞ ከመረብ አገናኝቷል። ይህ ደግሞ ከየትኛውም የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ በላይ ያደርገዋል።
ሊቨርፑል 18፣ አርሴናል 17፣ ቸልሲ እና ቶትንሀም ደግሞ 13 ጨዋታዎችን አሸንፈዋል። ኒውካስትል ዩናይትድ በቦክሲንግ ዴይ ቀን 15 ጨዋታዎችን በመሸነፍ መጥፎ ክብረ ወሰን ይዟል። አስቶንቪላ 14 እና ሊሲስተር ሲቲ 12 ጨዋታ በመሸነፍ ከቀዳሚዎች ተርታ ተሰልፈዋል።
ከፈረንጆች ገና ማግስት በኋላ ከሚከበረው የቦክሲንግ ዴይ በዓል ጀምሮ ለ12 ተከታታይ ቀናት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እስከ አራት መርሀ ግብር ይደረጋል። እነዚህ መርሀ ግብሮችም የበዓል ሰሞን ጨዋታዎች ወይም( Festive period ) ተብለው ይጠራሉ። የመጀመሪያው የበዓል ሰሞን ጨዋታ በ1860 እ.አ.አ ነው የተከናወነው። በሸፊልድ ዩናይትድ እና በሀላም መካከል መደረጉን መረጃዎች አመልክተዋል። በ1888 እ.አ.አ ዌስትብሮም ከፕሪስተን ኖርዝ ኢንድ መጫዎታቸውን ታሪክ ያስረዳናል።
እ.አ.አ ከ1957 ጀምሮ ደግሞ የበዓል ሰሞን ጨዋታዎች እየተባለ በውድድር መርሀ ግብር ውስጥ ተካቶ መደረግ እንደ ጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ። በ1963 እ.አ.አ የተደረገው የበዓል ሰሞን ጨዋታ በርካታ መርሀ ግብር የተደረገበት እና ብዙ ግቦች የተቆጠሩበት ነበር። አሥር መርሀ ግብር ሲከናወን 66 ግቦችም ከመረብ ተገናኝተዋል።
በወቅቱ ፉልሀም ኢፕስዊች ታውንን ዐስር ለአንድ ያሸነፈበት ጨዋታ በበዓል ሰሞን ከሚታወሱት መካከል ይገኝበታል። በዘመናዊ እግር ኳስ የበዓል ሰሞን ጨዋታዎች የብዙ ደጋፊዎችን ትኩረት እየሳበ መጥቷል። በ2022 የውድድር ዘመን የበዓል ሰሞን ጨዋታዎች መርሀ ግብር ለማስጠበቅ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ከተደረገ ከስምንት ቀናት በኋላ መጀመሩ አይዘነጋም።
የበዓል ሰሞን ጨዋታ ለክለቦች እና ለተጫዋቾች ፈታኝ ወቅት ነው:: በበዓል ሰሞን ጨዋታዎች ብዙ የመርሀ ግብር መደራረብ ይፈጠራል። በ12 ቀናት ውስጥ ክለቦች እስከ አራት የሚደርሱ ጨዋታዎችን ያከናውናሉ። ይህም በተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ ድካም ይፈጥራል። ተጫዋቾችም በቀላሉ ለጉዳት ይጋለጣሉ።
የቢቢሲ መረጃ እንደሚያመለክተው በበዓል ሰሞን ጨዋታዎች በ24 ሰዓት ስድስት ተጫዋቾች እንደሚጎዱ አስነብቧል። ተጫዋቾች ከጉዳታቸው ለማገገም ደግሞ ቢያንስ ከ10 ያላነሱ ቀናት ያስፈልጓቸዋል። ለአብነት እ.አ.አ በ2020 ኒውካስትል ዩናይትድ በበዓል ሰሞን ጨዋታዎች ዘጠኝ ተጫዋቾችን በጉዳት ማጣቱ አይዘነጋም።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በበዓል ሰሞን (Festive period) ከአራት ሺህ በላይ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። በበዓል ሰሞን ጨዋታዎች ታሪክ ዌስትብሮም በርካታ ጨዋታ በማከናወን ባለክብረ ወሰን ነው። ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልኩ ከተጀመረ ወዲህ እንደ ታሪኩ ማደር የተሳነው ማንቸስተር ዩናይትድ 86 ጨዋታዎችን አድርጓል- በበዓል ሰሞን።
ከእነዚህ ውስጥ በ56ቱ አሸንፏል። በ21ዱ ሲሸነፍ በዘጠኙ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል። ይህም ብዙ ጨዋታዎችን ያሸነፈ ቀዳሚው ክለብ ያደርገዋል። አርሴናል ባለፉት 32 ዓመታት 89 የበዓል ሰሞን ጨዋታዎችን በማከናወን ቀዳሚ ክለብ ነው። ከእነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ 51ዱን አሸንፏል። በ24ቱ አቻ ሲለያይ በ14ቱ ተሸንፏል።
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በበዓል ሰሞን ጨዋታዎች የሊጉ አናት ላይ ሆኖ ያሳለፈ ክለብ ካለፉት 32 የውድድር ዘመናት ዋንጫውን ማንሳት የቻሉት በ16ቱ የውድድር ዘመናት መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል። በቀሪዎቹ ዓመታት በበዓል ሰሞን ጨዋታዎች ፕሪሚየር ሊጉን የመራ ክለብ ዋንጫውን ማሳካት አልቻለም። በእርግጥም ባለፉት ስድስት የውድድር ዘመናት በገና ወቅት የፕሪሚየር ሊጉ አናት ላይ የነበሩ ሁለት ክለቦች ብቻ ናቸው በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ዋንጫውን ማንሳት የቻሉ።
ለአብነት ባለፉት ሁለት ዓመታት መድፈኞቹ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከማንቸስተር ሲቲ በልጠው የሊጉ አናት ላይ በመቀመጥ ነበር የገና በዓልን የተቀበሉት። ይሁን እንጂ በመጨረሻ ዋንጫውን በፔፕ ጓርዲዮላው ክለብ ማንቸስተር ሲቲ ተነጥቀዋል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ የበዓል ሰሞን ጨዋታዎችን ያሳለፈው የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል ነው።
ሊቨርፑል ዘንድሮም በበዓል ሰሞን ጨዋታዎች የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ እየመራ ማሳለፉ አይዘነጋም:: ታዲያ በአረኔ ሰሎት የሚመረው ክለብ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ዋንጫውን ያሳካል? በውድድር ዓመቱ መጨረሻ የሚመለስ ጥያቄ ነው:: ቀዮቹ ከባለፉት ዐስር ዓመታት ውስጥ የዘንድሮውን ጨምሮ አራት ጊዜ በበዓል ሰሞን ጨዋታዎች የሊጉ አናት ላይ ሆነው እንደነበር የሚታወስ ነው። ነገር ግን ከእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ሊጉን ማንሳት የቻሉት አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
በ2019/20 የውድድር ዘመን ሊቨርፑል ሻምፒዮን የሆነበት ጊዜ እንደነበር አይዘነጋም። ወራጅ ቀጠና ውስጥ የገቡትን ክለቦች በተመለከተ ደግሞ ባለፉት 20 ዓመታት ወራጅ ቀጠና ውስጥ ገብተው የበዓል ሰሞን ጨዋታዎችን ያሳለፉ ክለቦች በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን የወረዱ በአራት የውድድር ዘመን ብቻ ነው።
በ16ቱ ዓመታት ከበዓል ሰሞን ጨዋታዎች በኋላ ራሳቸውን በማጠናከር ከመውረድ ሊተርፉ ችለዋል። የዘንድሮውን የበዓል ሰሞን ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ሆነው የጨረሱት ሌሲስተር ሲቲ፣ ኤፕስዊች ታውን እና ሳወዝአምፕተን በውድድር ዓመቱ መጨረሻ እጣ ፈንታቸው ምን የሆናል? አብረን የምናየው ይሆናል::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም