ቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ በኮንጐ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምስራቃዊ ቀጣና የሚገኝ ሲሆን በዓለማችን ካሉ በብዝሃ ህይወት ሀብት ታዋቂ ከሆኑ ቀዳሚዎች መካከል ተጠቃሽ ነው::
ፓርኩ በ1925 እ.አ.አ ተመስርቶ በዓለም አቀፍ የአካባቢ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት በ1979 እ.አ.አ ነው የተመዘገበው:: ይህም ከአፍሪካ ቀደምት ፓርኮች ረድፍ አሰልፎታል::
የፓርኩ ክልል በሰሜን የሰሜሊኪ ወንዝ ተፋሰስን እና የአልበርቲን ሸለቆ ደን ያጠቃልላል:: የመገኛው ከፍታ አነስተኛው 680 ሜትር ከፍተኛው የስታንሊ ተራራ 5109 ሜትር ተለክቷል:: ደቡባዊው ቀጣና የኪቡ ኃይቅ፣ ኒራጎንጎ እና ማይካኖ የመሳሰሉ በእሳተገሞራ የተፈጠሩ ሳር ለበስ ተራራዎችን አካቷል::
በአየር ንብረቱ ከ23 እስከ 28 ዲግሪ ሴልሺየስ የተመዘገበ ሲሆን ከመጋቢት እስከ ግንቦት አጋማሽ እና ከመስከረም እስከ ህዳር የዝናብ ወራቶች ናቸው:: አማካይ የወሩ ከ30 እስከ 40 ሚሊሜትር ተለክቷል በደረቅ ወራት፤ በዝናባማው ወራት ደግሞ 220 ሚሊሜትር በአማካይ ያገኛል::
በቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ 2077 የእፅዋት ዝርያዎች ይገኛሉ:: በተራራማ አቀበት እና አናት 264 የዛፍ ዝርያዎች፤ 230 ዎቹ ደግሞ በዝቅተኛ ሸለቆ የሚገኙ የእፅዋት ዝርያ መሆናቸው ተረጋግጧል::
በዱር እንስሳት 196 አጥቢ፣ 706 የአእዋፍ ዝርያዎች፣ 109 ተሳቢ እና 65 የውኃ ውስጥ እንስሳት መኖራቸውም ተለይቷል::
በሳር ለበሱ ሜዳማ የፓርኩ ቀጣና በኮንጐ ብቻ የሚገኘው (okapi) የተሰኘው (ብር ቅዬ) ሳላ መሰል እንስሳት መገኛ ነው:: ሳር ለበሱ የፓርኩ ቀጣና አቅፎ በያዘው ብዝሃ ህይወት ማለትም በእፅዋት እና እንስሳት ሀብቱ በቀዳሚነት ተጠቃሽ መሆኑንም ነው ድረ ገፆች ያስነበቡት::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ደብሊው ኤችሲ፣ ዩኔስኮ፣ ቪሩንጋ፣ ቪዚት ቪሩንጋ ድረገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም