ቪክቶሪያ ኃይቅ በአፍሪካ አህጉር የሚገኝ ሲሆን ሦስት ሃገራት ማለምት ኡጋንዳ፣ ኬኒያ እና ታንዛኒያ የተፈጥሯዊ ሀብቱ ባለ ድርሻ ናቸው:: ኃይቁ በስተሰሜን ሀሳባዊውን የምድር ወገብ ይነካል፤ ከፍተኛ ጥልቀቱ 80 ሜትር፣ ጠቅላላ ስፋቱ ደግሞ 68,800 ኪሎ ሜትር ስኬዌር ተለክቷል::
በቪክቶሪያ ኃይቅ ተፋሰስ ሰላሳ ሚሊዮን ኗሪዎችም ይገኛሉ:: ኃይቁ የተስተካከለ ባይሆንም አራት ማእዘን ቅርጽን የያዘ ነው:: ከሰሜን እስከ ደቡብ 337 ኪሎ ሜትር ረዥሙ ልኬታው ነው:: የባሕር ዳርቻው የኃይቁ ዙሪያ 3,220 ኪሎ ሜትር አካባቢ ተለክቷል::
በምዕራባዊ እና በምስራቅ ስምጥ ሸለቆዎች መካከል በተዘረጋው አምባ ላይ ከባሕር ጠለል 1,134 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል:: ከፍተኛ ጥልቀቱም 82 ሜትር ነው::
በቪክቶሪያ ኃይቅ በርካታ ደሴቶችም ይገኙበታል:: በግምት አነስተኛ ስፋት ያላቸው እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ ደሴቶች እንዳሉት ድረ ገፆች አመላክተዋል:: በአብዛኞዎቹ ሰዎች የማይኖሩባቸው ሲሆኑ መጠናቸው ከፍ ባሉት ላይ ኗሪዎች ሰፍረውባቸዋል:: እያንዳንዳቸው በትልልቆቹ ደሴቶች ላይ የሰፈሩ ኗሪዎችም አንዳቸው ከሌላኛው የሚለዩ የራሳቸው ባህል፣ አኗኗር እና ታሪክ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ጐብኚዎችን የሚስብ ሀብት ሆኗቸዋል::
በቪክቶሪያ ኃይቅ ላይ ማፋንጋኖ ትልቁ ደሴት ሲሆን በጥንታዊ ኗሪዎች በድንጋይ ላይ የተሳሉ ስእሎች የደሴቱ መገለጫ መስህብ ናቸው:: በሀይቁ ሰሜናዊ ምዕራብ ጥግም 62 ውብ የሴሴ ደሴቶች የተሰኙ ይገኙበታል::
ለኃይቁ ውኃን ከሚገብሩ ወንዞች መካከል ካጄራ አንዱ ነው:: ወንዙ ከደቡብ ምእራብ በኩል 90 ሜትር ያህል ከፍ ካለ ጥግ የሚነሳ ደለል ተሸክሞ ወደ ኃይቁ ዳርቻ ሲደርስ የሚያስተኛም ነው::
ወደ ቪክቶሪያ ኃይቅ ከሚገቡ ባህር ገብ መሬቶች ቪክቶሪያ በስተሰሜን የሚገኘው የስፒክ ሰላጤ አንዱ ነው ከፍታው ሁለት መቶ ሜትር ከኃይቁ በላይ ተለክቷል::
ወደ ቪክቶሪያ ኃይቅ የሚገባ ሌላኛው ወንዝ ካቶንጋ ይሰኛል:: የኃይቁ ብቸኛ መውጫ ከሰሜናዊ የኃይቁ ዳርቻ የሚወጣው የቪክቶሪያው “አባይ” ነው::
አውሮፓውያን የአባይ ወንዝ ምንጭን ለመፈለግ በ1858 እ.አ.አ ባደረጉት አሰሳ እንግሊዛዊው አሳሽ ጆን ሃኒንግ ስፒክ ቪክቶሪያ ኃይቅን ለመመልከት ችሏል::
ከቪክቶሪያ ኃይቅ የሚወጣውን ውኃ በመገደብ ሁለት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተገንብቶም አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የድረ ገፆች ፅሁፍ አመላክቷል:: ለዘገባችን ታንዛኒያ ቱሪዝም፣ ግሎባል ኔቸር ሌክ ቪክቶሪያ ድረ ገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም