ተላላፊ በሽታዎች

0
29

የክረምትን መውጣት ተከትሎ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ይከሰታሉ፤ በአማራ ክልልም እየተከሰተ ነው፤ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ከሚከሰቱ በሽታዎች መካከል ኮሌራ፣ ወባ፣ ጉንፋን እና ጉንፋን መሰል በሽታዎች ይጠቀሳሉ። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው።

በ2016/17 በጀት ዓመት ዋና የመተላለፊያ ወቅት ተብሎ በሚታወቀው ከመስከረም ወር ጀምሮ እስከ ሕዳር መጨረሻ እና ታኅሳስ አጋማሽ ከፍተኛ የወባ ስርጭት እንደነበር አመላክተዋል:: ይሁን እንጂ በነበረው ርብርብ ሥርጭቱን በመግታት የሰዎችን ሕይዎት መታደግ ስመቻሉ አንስተዋል።

የጤናው ሴክተር ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የትምህርት፣ ሴቶች እና ወጣቶች ቢሮ ቀበሌ ድረስ ርብርብ በማድረግ ሁሉም ጤና ጣቢያ ባለቤት በመሆን ወባማ ቦታዎችን በየአካባቢው የማፋሰስ እና የማዳፈን ሥራ ተሠርቷል:: በዚህም የወባ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ከሁለት ሚሊየን በላይ በሽተኛ ቢመዘገብም የተፈራውን ያህል ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ ተችሏል።

በዚህ ዓመትም ስርጭቱን ለመግታት እየተደረገ ባለው ቅንጅታዊ ሥራ ስርጭቱ ቀንሷል፤ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸውን 34 ወረዳዎች በመለየት የቀን ተቀን ዳሰሳ፣ ክትትል፣ የኬሚካል ርጭት እና በ27 ወረዳ አጎበር ተደራሽ ተደርጎ የቁጥጥር ሥራው ውጤታማ ሆኗል።

አሁን የምንገኝበት የመስከረም ወር ዝናቡ ሲያቆም ሙቀት እና ትንሽ የቆረ ውኃ ለትንኟ መራባት ስለሚረዳት ሁሉም የክልሉ ማኅበረሰብ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ በተለይ አርብ ጠዋት በመውጣት በእጁ ያለውን እና ብዙ ወጭ የማስወጣውን የቁጥጥር ሥራ እንዲያከናውን አሳስበዋል።

የወባ ስርጭት እስከ ታኅሳስ ወር ድረስ ሊቀጥል ይችላል፤ ይህ ወቅት ለትንኟ መራባት ምቹ ጊዜዋ ነውና:: በመሆኑም በክልሉ ያሉ 933 ጤና ጣቢያዎች፣ የጤና ድርጅቶች እና ሌሎች ባድርሻዎች በቅንጅት መሥራት፣ ነዋሪውም አካባቢውን ቢያንስ በሳምንት እንድ ጊዜ የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ማዳፈን እና ማፋሰስ ሥራን ሊሠራ ይገባል::

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በክልሉ ያሉ በተለይ ከፍተኛ ስርጭት የሚኖራቸው 40 ወረዳዎች ተለይተዋል፤ እነዚህ ወረዳዎች 68 በመቶ የክልሉን የወባ ጫና የሚሸፍኑ ናቸው:: ይህን ታሳቢ በማድረግም የሚመለከታው ሁሉ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል::

ሥርጭቱን ለመከላከል በ18 ወረዳዎች 530 ሺህ 282 ቤቶችን የወባ ኬሚካል ለመርጨት ታቅዶ እስከ አሁን 80 በመቶ የሚሆኑትን ማሳካት ተችሏል ። ለ26 ወረዳዎች ከተመደበው ግማሽ ሚሊዮን አጎበር በ20ዎቹ ቅድሚያ የተሠጣቸው ወረዳዎች እየተሠራጨ ይገኛል። ቀሪ የአጎበር ሥርጭት እና የኬሚካል ርጭቱን እስከ መስከረም መጨረሻ ለማጠናቀቅም እየተሠራ ነው፤ ቢሆንም ግን የአጎበር እና የኬሚካል እጥረት መኖሩን ነው አቶ በላይ የገለጹት።

ባለፋት ዓመታት ወባ ጠፍቷል በማለት የተፈጠረው ቸልተኝነት ለሥርጭቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለነበረው  ሰዎች የወባ ምልክቱን ሲያዩ ቶሎ ወደ ሕክምና በመሄድ እንዲታከሙ እና ቅድመ መከላከሉ ላይ ደግሞ አተኩረው እንዲሠሩ አሳስበዋል።

ሌላው የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ከሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች መካከል ኮሌራ አንዱ ነው፤ ቀጣይ ወራት በየኃይማኖቱ  በዓላት የሚከበሩባቸው ናቸው:: የአደባባይ በዓላት ደግሞ ብዙ ሰዎች የሚሰባሰቡባቸው ናቸው፤ ይህ ጥግግት ደግሞ ለኮሌራ በሽታ ስርጭት ምቹ ነው፤ በአሁኑ ወቅትም በአማራ ክልል ጥቂት ወረዳዎች የኮሌራ በሽታን ሪፖርት እያደረጉ ነው።

ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት በአማራ ክልል እስከ መስከረም ሁለተኛ ሳምንት ድረስ 39 ሕሙማን በኮሌራ በሽታ ተጠቅተዋል:: በሽታው አጣዳፊ ተቅማጥን እና ትውከትን የሚያስከትል ነው፤ በፍጥነት ሕክምና ካልተሰጠ ወዲያው ሊገድል ይችላል፤ በጣም በቀላሉም መከላከል የሚቻል በሽታ ነው።

ከበሽተኛው ሰው ጋር ንክኪ ካለ ወዲያውኑ እጅን በሳሙና እና ውኃ መታጠብ ይገባል፤ በተመሳሳይ እጅ ከአፍ ጋር ፈጣን እና ተደጋጋሚ ንክኪ ስላለው ቶሎ ቶሎ መታጠብ ይገባል:: በተለይ ትውከት እና ሰገራ ከተነካ ወዲያውኑ በአግባቡ መታጠብ ግድ ይላል::

ከዓለም ጤና ድርጅት ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው የኮሌራ በሽታ በተበከለ ምግብ ወይም ውኃ ነው የሚመጣው፤ በመሆኑም  አጣርቶ መጠቀም፣ ንክኪን ማስወገድ እንዲሁም የመፀዳጃ ቤትን ንፅህና ጠብቆ በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ነው ሲልም የድርጅቱ መረጃ ያስገነዝባል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክር በላይ በዛብህ እንዳሉት በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጡትን የመከላከያ  እና የመቆጣጠሪያ ዘዴዎችን መተግበር ይገባል፤ ጤና ተቆጣጣሪዎችም ሆቴል ቤቶችን እና ሌሎች የሕዝብ መገልገያ ቦታዎችን በአግባቡ መቆጣጠር ይገባቸዋል::

በብዛት ችግሩ የሚታይባቸው የፀበል ቦታዎች ስለሆኑ ከኃይማኖት አባቶች ጋር ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ነው፤ በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ደግሞ ትብብር ወሳኝ ነው።

በሽታው አጣዳፊ መሆኑን ያነሱት አቶ በላይ መዘናጋት ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችልም ነው ያሳሰቡት፤ በጥቂት ቀን በርካታ ሰዎችን ሊያጠቃ ስለሚችል በክልሉ ከችግሩ ሙሉ ለሙሉ እንዲወጣ (ዜሮ ለማድረግ) ከውኃና ኢነርጂ ቢሮ፣ ከጤና ተቋማት፣ ከኃይማኖት አባቶች እና በተዋረድ ካሉ ባለድርሻዎች ጋር በመናበብ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተመሳሳይ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ የአየር ንብረት መለዋወጥም ይኖራል፤ ይህም በአየር ንብረት መለዋወጥ ምክንያት ለሚከሰቱ በሽታዎች (በዋናነት ለቫይረስ ወለድ ሕሞች) ምክንያት ሊሆን ይችላል:: አስም፣ ጉንፋን እና ጉንፋን መሰል አየር ወለድ ሕመሞች ሊስፋፉ ይችላሉ፤ በመሆኑም የግል እና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ፣ ምግብን በአግባቡ አብስሎ መመገብ ይገባል::

 

ጤና አዳም

ተላላፊ በሽታዎችን እንዴት መከላከል ይቻላል?

ተላላፊ በሽታዎች የሚዛመቱ በሽታዎች ሲሆኑ፣ ልክ እንደ ጉንፋን ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ናቸው። ጉንፋን እና ጉንፋን መሰል ሕመሞችን ጨምሮ ኮሌራ እና ወባ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ኮሌራ

የኮሌራ በሽታ ቫይቢሪዮ ኮሌራ ተብሎ በሚጠራ ረቂቅ ተህዋስ የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነዉ። በተህዋሱ የተበከለ ምግብን ወይም መጠጥን በመጠቀም የሚተላፍ በሽታ ነው።

ዋና ዋና ምልክቶች

  • የቆዳ ድርቀት
  • የውኃ ከመጠን በላይ መጠማት
  • የሽንት መጠን መቀነስ
  • በጣም የሚሸትና ውኃማ ተቅማጥ
  • ማቅለሽለሽ

መከላከያ

  • ንፅህናውን የጠበቀ ምግብና ውኃ መጠቀም
  • የግል እና አካባቢን ንጽህና መጠበቅ

በበሽታው የተያዘ ግለሰብ ማድረግ ያለበት

  • በቂ ፈሳሽ ማግኘት
  • በሽታውን ወደ ሌሎች እንዳያስተላልፍ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ
  • የሕክምና ክትትል

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here