ተማሪን ከትምህርት ቤቶች ጋር ለማገናኘት…

0
137

በአማራ ክልል የተከሰተው የሰላም እጦት የትምህርት ዘርፉን ዛሬም እየፈተነ ቀጥሏል፡፡ የ2017 የትምህርት ዘመን የአንደኛው ወሰነ ትምህርት በተጠናቀቀበት ወቅት ከአራት ሚሊዮን የሚበልጡ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደሆኑ የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡ እንደ መረጃው በትምህርት ዘመኑ ከተመዘገቡት ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ በትምህርታቸው ላይ የሚገኙት ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን አይበልጡም፡፡ ይህም ክልሉን በተሻለ የሰው ኀይል ተወዳዳሪ እንዳይሆን የሚገዳደር ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እያስተማሩ መመዝገብ እና ማብቃትን ወቅታዊ ሁኔታው ለፈጠረው ክስተት መውጫ መንገድ አድርጎ ለመሥራት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ እስከ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባ እንዲከናወን ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሁሉም ሰላም ያለባቸው አካባቢዎች ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ በዘመቻ እየሠሩ ነው፡፡ ታዲያ መጪዎቹ ቀናት የአራት ሚሊዮን ተማሪዎችን እጣ ፈንታ የሚወስኑ በመሆናቸው ሁሉም የክልሉ ውድቀት ያሳስበኛል የሚል አካል ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል፡፡

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ በ2017 ዓ.ም 89 ሺህ ተማሪዎችን መዝግቦ የማስተማር ዕቅድ ነበረው፡፡ የመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ተጠናቆ ሁለተኛው ወሰነ ትምህርት እስከሚጀመርበት የካቲት ወር መጀመሪያ ጊዜ ድረስ በተጨባጭ ማሳካት የተቻለው 18 ሺህ 901 ተማሪዎችን ብቻ ነው፡፡

የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አገኘሁ ጋሻው እንዳስታወቁት አሁንም 70 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት እንደራቁ ከአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ ይህም እንደ ክልል ያጋጠመው የጸጥታ መደፍረስ ውጤት መሆኑን አመላክተዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩ ተማሪ እና መምህራን ከትምህርት ተቋማት ጋር እንዳይገናኙ ማድረጉን ተከትሎ ተማሪዎች እና መምህራን ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጫና ተዳርገዋል፡፡ በተለይም ሴቶች ለጾታዊ ጥቃት እና ያለዕድሜያቸው  ጋብቻ እንዲፈጽሙ እንዲሁም ወጣቶች የሕገወጥ ስደት ሰለባ መሆናቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ወረዳው ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ከወረዳ አመራሮች፣ ከመምህራን፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከወላጆች እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰላምን መሠረት ያደረገ ተደጋጋሚ ውይይት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን የዳባት ወረዳ ትምህርት መምሪያም በሦተኛው ዙር የተማሪዎች ምዝገባ ከ33 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ እየሠራ መሆኑን ለአሚኮ አስታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ከመማር ማስተማር ውጪ ሆኖ የከረመው የምዕራብ ጎጃም ዞን በዚህ ዓመት ዕቅዱን ማሳካት አልቻለም፡፡ በትምህርት ዓመቱ 396 ሺህ 547 ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመለሳሉ የሚል ዕቅድ ነበር፡፡ እስከ ሁለተኛው ወሰነ ትምህርት መጠናቀቂያ ጊዜ ድረስ ማሳካት የተቻለው 28 ሺህ 931 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ መኩሪያው ገረመው ተናግረዋል፡፡

ከትምህርት ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ለመመለስ አሁንም ጥረቶች መቀጠላቸው ተጠቁሟል፡፡ የሦስተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባን አንዱ ተማሪዎችን የመመለሻ መንገድ ተደርጎ በዘመቻ እየተከናወነ ነው፡፡ ምክትል ኀላፊው ከየካቲት 3 ቀን እስከ 13/2017 ዓ.ም እየተካሄደ ባለው ምዝገባ 5 ሺህ 610 ተማሪዎች መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ዘግይተው ወደ መማር ማስተማር የሚመለሱ ተማሪዎችን ለማብቃት እና ተወዳዳሪ ለማድረግ  የትርፍ ሰዓት ትምህርት በመፍትሔነት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡ አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላትም ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ በዚህ ዓመት 713 ሺህ 610 ተማሪዎችን የማስተማር ዕቅድ እንደነበረው የመምሪያው ምክትል ኃላፊ ደመላሽ ታደሠ ለአሚኮ ተናግረዋል። በክልላዊ የጸጥታ ችግሩ ምክንያት ግን ከ628 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ ከትምህርት ውጭ የሆኑ ተማሪዎችን ለመመለስ በተከታታይ አንደኛ እና ሁለተኛ ዙር ምዝገባ በንቅናቄ በማካሄድ መመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁንም አብዛኛዎቹ ተማሪዎች እንዳልተመለሱ ተገልጿል፡፡

ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎች ላልተፈለገ እና ላለዕድሜ  ጋብቻ እየተዳረጉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ሦስተኛው ዙር የተማሪ ምዝገባ በንቅናቄ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለውጤታማነቱም ከወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ የትምህርት ባለድርሻዎችን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን፣ የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን በማወያየት መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ሥራ መገባቱን አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም ምክትል መምሪያ ኀላፊው ይህንን መረጃ ለአሚኮ እስከሰጡበት የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጊዜ ድረስ ከሁለት ሺህ 950 ተማሪዎች ተመዝግበዋል፡፡ ሦስት የአጸደ ሕጻናት፣ አምስት የአንደኛ ደረጃ እና ሦስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው የመማር ማስተማር እያከናወኑ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

መማር ማስተማሩን ለማስቀጠል አሁንም የጸጥታ ችግሩ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም አካል ትምህርት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነጻ  መሆኑን ተገንዝቦ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ሊያደርግ  እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቀሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት እንዳስታወቁት በክልሉ በ2017 ዓ.ም በ2017 የትምህርት ዘመን 3ሺህ 736 ትምህርት ቤቶች አልተከፈቱም፡፡  ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነዋል፡፡ ከ30 ሺህ በላይ መምህራን እና የትምህርት ቤት መሪዎች ወደ ሥራ ገበታቸው መግባት አልቻሉም፡፡

እንደ ሰብሳቢዋ ክልሉ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር አንጻራዊ ሰላም የታየበት ቢሆኑም የትምህርት ሥራ ግን አሁንም ችግር ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ማሳያ ያደረጉት ባለፈው ዓመት ከነበረው የ57 በመቶ አፈጻጸም የዘንድሮ 40 በመቶ ላይ መገኘቱን ነው፡፡ በመሆኑም መላው የክልሉ ሕዝብ የገጠመው የትምህርት ተሳትፎ ችግር በልጆች መጻኢ ዕድል ላይ የሚያመጣውን ጫና በመረዳት ያለምንም ማመንታት ልጆቹን  ወደ ትምህርት ቤት እንዲልክ ጠይቀዋል። ከክልል እስከ ትምህርት ቤት ያሉ የትምህርት መሪዎች፣ ባለሙያዎች እና መምህራን የጉዳዩን አሳሳቢነት አይተው ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በተቀናጀ አግባብ እንዲሠሩ እና የራሳቸውን ግዴታ በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በመማር ማስተማር ዘርፉ የገጠመውን ችግር ለመሻገር በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በሚቀጥሉት ወራት የትምህርት ዘርፉ ላይ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው ይታወሳል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 24  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here