በአሜሪካ የቴክሳስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ተማሪዎችን ያለእረፍት በአንድ ሰዓት 400 “ፑሽአኘ” እንዲሰሩ በማስገደዱ ባጋጠማቸው የጤና እክል ሆስፒታል መግባታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል፡፡
የሮክ ዎልሄዝ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት “ጁኒየር ቫርስቲ” የእግር ኳስ ክለብ የቀድሞው አሰልጣኝ ጆን ሃረል እና ረዳት አሰልጣኞች በ50 ደቂቃ የተጫዋቾች የስልጠና ቆይታ 400 “ፑሽአኘ” ያለምንም ረፍት እና ውኃ መጠጫ ጊዜ ሳይሰጣቸው በመስራታቸው ለቀናት ሆስፒታል እንዲተኙ ተዳርገዋል፡፡
ለህመም ከተዳረጉት ተጫዋቾች የአንዱ ወላጅ ባቀረበው ክስ አንድ ተጫዋች በሰራው አንድ ስህተት 16 “ፑሽአኘ” እንዲሰራ መገደዱ ወንጀል በመሆኑ አሰልጣኙ ሊቀጣ እንደሚገባ ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡
በስልጠናው ወቅት 23 ስህተቶች በመፈፀማቸው 26ቱ ተጫዎቾች እያንዳንዳቸው 368 “ፑሽአኘ” እንዲሰሩ ቅጣት ተጥሎባቸዋል – በአሰልጣኙ፡፡ በመሆኑም በታዘዙት ከባድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ 26 ተጫዋቾች በተደረገላቸው ምርመራ “ራሃአብዶም ዮሊሲስ” የተሰኘ የጡንቻ ህብረ ህዋሳት መፈንዳት እና የደም መፍሰስ ምልክቶች ታይተውባቸዋል፡፡ ተጫዋቾቹ ፈፀሟቸው ከተባሉት “ስህተቶች” መካከል “የተሳሳተ አለባበስ፣ ከአሰልጣኝ እና ከዳኞች ጋር አሉታዊ ግንኙነት፣ መጥፎ አመለካከት” ወ.ዘ.ተ የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ለአሰልጣኙ አካላዊ ቅጣቶች በተማሪዎች ላይ እንዳይፈፅም ቢያስጠነቅቀውም በቸልተኝነት መፈፀሙን አረጋግጧል፡፡ ተማሪዎቹ ፈጣን ጥብቅ የጤና ክትትል እና ህክምና ካላገኙ በኩላሊት እና በልብ ህመም ተጠቅተው እስከ ሞት ሊያደርሳቸው እንደሚችል ነው በድረ ገጹ የተጠቆመው፡፡
አሰልጣኞች በትምህርት ቤት እና ከትምህርት ቤት ውጪ ከሳሾች ክሳቸውን እንዲያነሱ ዛቻ እና ማስፈራሪያ አድርሰውባቸዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ በሰልጣኞቹ ላይ በአጭርም ሆነ በረዢም ጊዜ የከፋ የጤና እክል ማስከተሉ አይቀሬ መሆኑ ነው የተጠቆመው፡፡ “ቀድሞ ነበር እንጂ…”
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም