የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የተማሪ ምገባ የሐብት ማሰባሰቢያ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፤ መምሪያዉ “አንድም ሕጻን በምግብ እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታው እንዳይለይ ኃላፊነታችንን እንወጣ” በሚል መሪ ሐሳብ ነው የንቅናቄ መድረኩን ያካሄደው።
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ/ር) እንደገለጹት በትምህርት ዘመኑ 20 ሺህ ተማሪዎችን የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል። ይህንንም ዕውን ለማድረግ ሐብት ወሳኝ በመሆኑ ከመንግሥት ባሻገር የትምህርት ባለድርሻዎች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ባለፉት ዓመታት በከተማ አስተዳደሩ የተጀመረው የምገባ ፕሮግራም ዘርፈ ብዙ አበርክቶ እንዳለዉና የተማሪዎችን የማቋረጥ ምጣኔ ከሁለት በመቶ በታች እንዲወርድ ማድረጉንም ለፋይዳው ማሳያ በማድረግ አንስተዋል። አርፋጅ እና ደጋሚ ተማሪ እንዲቀንስ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የበጀት እጥረት ውጤቱ የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን በማሳደግ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በሆኑ ተማሪዎች ውስጥ በሚገለጠው የምገባ ፕሮግራም ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል። የመድረኩ ዋና ዓላማም የምገባ ፕሮግራሙ በበጀት እጥረት እንዳይስተጓጎል ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ለማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ በበኩላቸዉ ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዲማሩ፣ ሀገር እንዲገነቡ፣ ለሀገር ዋልታ እና ማገር እንዲሆኑ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ መንከባከብ ይገባል ብለዋል። በትምህርት ቤቶች የተጀመረው የተማሪ ምገባ ተደራሽነቱን እንዲስፋፋ ውጤቱም በተግባር የሚገለጥ እንዲሆን የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


