በባሕር ዳር ከተማ የጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች በጎ አድራጎት ክበብ የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ500 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች የምሳ ግብዣ አድርጓል፡፡
የተማሪዎች ክበብ በየዓመቱ አቅመ ደካሞችን የምሳ ግብዣ ያደርጋል። በምሳ ግብዣው ያገኘናቸው ወይዘሮ ፍቅራዲስ ካሳ “የተደረገልን ግብዣ ከምሳ ባሻገር መልካም ትርጉም አለው ነው” ያሉት። ተማሪዎቹ ለዓይነ ሥውሮች መንገድ በማሻገር አርዕያ ናቸው ብለዋል። በጎነታቸውን ስላሳዩን ለተማሪዎች ክብር አለኝ ብለዋል፡፡
ሌላዉ በምሳ ግብዣው ያገኘናቸው አቶ ታደሰ ቸኮል በበኩላቸው ጧሪ የሌላቸው እና በቤተክርስቲያን ተጠልለው የሚኖሩ እና ምንም ዓይነት መተዳደሪያ የሌላቸው መሆናቸውን ነግረውናል። የተደረገላቸው የምሳ ግብዣ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑን አስታውሰዋል። በተደረገላቸው የምሳ ግብዣም ተማሪዎችን እና ያስተባበሩትን በሙሉ ከልብ አመስግነዋል፡፡
ተማሪ አቡበክር እስማኤል በጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአሥረኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ የበጎ አድራጎት ክበብ አስተባባሪ መሆኑን ነግሮናል፡፡ ክበቡ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ ከትንሳኤ በዓል ማግስት በዕለተ ሐሙስ (አዳም) በተሰበሰበው ወርሃዊ መዋጮ፣ ከከተማዋ ነዋሪዎች እና ከበጎ አድራጊ ተቋማት በተገኘ ገንዘብ ለአቅመ ደካሞች የምሳ ግብዣ መርሐ ግብር ማድረግ ነው ብሏል። መደጋገፍ እና መረዳዳት መጎልበት እንዳለበት ተናግሯል። ተማሪዎች በክበቡ የየራሳቸው የሥራ ድርሻ እንዳላቸው ገልጿል።
የበጎ አድራጎቱ መሥራች እና ሰብሳቢ መላከ ሕይወት ቆሞስ አባ ፍቅረማርያም የጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ናቸው፡፡ ከ500 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች እና ረዳት ለሌላቸው ወገኖች የምሳ ግብዣ እንደተደረገላቸው ገልፀዋል። የተሰበሰው ገንዘብ ከተማሪዎች፣ በከተማዋ ካሉ በጎ ፈቃደኛ ተቋማት፣ ከግለሰቦች እና ከትምህርት ቤቱ የተሰበሰበ ነው፡፡ ሌሎች ወገኖችም ከእነዚህ በጎ አሳቢ ተማሪዎች መልካም ነገር ማድረግን ሊማሩ እንደሚገባ አስረድተዋል።
የጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሙጨ ባዘዘው የበጎ አድራጎት ክበቡ በትምህርት ቤቱ ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም በበጎ ሥራ ጎልቶ የታየው ግን ከአምስት ዓመት ወዲህ እንደሆነ ተናግረዋል። ትምህርት ቤቱ ለዚህ የተቀደሰ ሀሳብ የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ነው ብለዋል።
ክበቡ ተጠናክሮ ወደ በጎ ሥራ እንዲገባ የትምህርት ቤቱ ተማሪ የሆኑት መላከ ሕይወት ቆሞስ አባ ፍቅረማርያም ተማሪዎችን በማስተባበር ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ መተሳሰብ እና መረዳዳት መጎልበት እንዳለበትም አሳስበዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም