ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን እንዴት ያሳልፉ?

0
59

 ተማሪዎች በዓመቱ  ሲሰጥ የነበረውን  ትምህርት አጠናቀው ከመደበኛ ትምህርት ውጭ በሚሆኑባቸው ጊዜያት የቀጣይ ሕይወታቸውን መስመር በሚቀይሱ ሥራዎች ላይ እንዲሠማሩ ይጠበቃል:: ይህ ጊዜ አቅም የሚፈተሽበት፣ ፍላጎት የሚቃኝበት፣ ተሰጥኦ የሚዳብርበት  ነው።

በከተማ እና በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ተማሪዎች የክረምቱን የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በተለያየ መንገድ ነው:: በከተሞች አካባቢ የሚኖሩት አብዛኛውን ጊዜያቸውን የተለያዩ ጨዋታዎችን በመጫዎት፣ የቴክኖሎጂ አጫጭር ስልጠናዎችን በመውሰድ፣ የቋንቋ ትምህርት በመማር፣ የተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎችን በመጎብኘት ያሳልፋሉ::  በገጠሩ አካባቢ የሚኖሩት ደግሞ በአብዛኛው የአርሶ አደር እና  አርብቶ አደር ልጅ በመሆናቸው በልማት ሥራዎች ቤተሰባቸውን ያግዛሉ:: አንዳንዶች የተጣበበ ጊዜያቸውን አብቃቅተው የማጠናከሪያ ትምህርቶችን ይከታተላሉ:: የበዓላት ቀናትን ለይተው የእግር ኳስ እና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮችን ይጫወታሉ::

እኛም በዚህ እትማችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ተማሪዎች ቀሪ የእረፍት ጊዜያቸውን እንዴት ማሳለፍ እንዳለባቸው ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያገኘናቸውን ሀሳቦች ልናጋራቸው ወደድን::

 

ለቀጣይ ትምህርት ራስን ማብቃት

ተማሪዎች የዓመቱን ትምህርት እንዳጠናቀቁ የሚኖራቸውን ትርፍ ጊዜ የቀጣዩን የክፍል ደረጃ ትምህርት ይዘት ቀድሞ ለመቃኘት፣ የማጠናከሪያ ትምህርቶችን ለመከታተል እና ሌሎች ራስን በማብቂያ ሥራዎች ሊሆን እንደሚገባ ከክራፍቲንግ ስኮላርስ (craftingscholars.com) የተገኘው መረጃ ይጠቁማል:: በእነዚህ የእረፍት ወራት ትምህርት ቤቶች ለቀጣዩ የትምህርት ዓመት የሚሆኑ መጻሕፍትን ለተማሪዎቻቸው  ቀድመው ያሰራጫሉ:: ይህም በቤታቸው ቁጭ ብለው ይዘቶችን ቀድመው በመረዳት እርስ በርስ እንዲረዳዱ ዕድልን የሚሰጥ ነው:: ከኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎች ለእረፍት የሚመለሱ ተማሪዎችም የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለቀጣዩ የትምህርት  ዓመት  በሥነ ልቦና እንዲዘጋጁ ከማድረግ ጀምሮ በትምህርት ዘመኑ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከፍተኛ እገዛ ያደርጉላቸዋል::

ክራፍቲንግ ስኮላርስ የበይነ መረብ መረጃ እንደሚያመላክተው ተማሪዎች በክረምት ወቅት የማጠናከሪያ እና የማካካሻ ትምህርት ለመውሰድ ከማሰባቸው ቀደም ብለው በተጠናቀቀው የትምህርት ዓመት የነበራቸውን የትምህርት አፈጻጸም መገምገም ይገባቸዋል::  ተማሪዎች  በዓመቱ በየትኛው የትምህርት አይነት ከፍተኛ ውጤት እንዳስመዘገቡ እና በየትኛው ዝቅ ያለ ውጤት እንዳመጡ መለየት እንደሚገባቸውም መረጃው አስገንዝቧል:: ውጤታማ የሆኑባቸውን እና ያልሆኑባቸውን የትምህርት አይነቶች ከመለየት ባለፈም የትኛው ይዘት ላይ ተቸግረው  እንደከረሙ መለየት ለቀጣዩ የትምህርት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ያግዛቸዋል::

ተማሪዎች የዓመቱን የትምህርት እንቅስቃሴ በአግባቡ ከገመገሙ በኋላ ቀጥሎ የሚመጣው በደንብ የተዋቀረ እቅድ ማዘጋጀት ነው:: ዛሬ በትምህርትም ሆነ በሌሎች የሥራ ዘርፎች ስኬታማ የሆኑ ሰዎች መሠረታቸው ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችላቸውን ዕቅድ አዘጋጅተው የተጓዙ መሆናቸውን መረጃው አመላክቷል::

መረጃው ባለፉት ዓመታት ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገቡባቸው የትምህርት አይነቶች በቀጣይ ዓመትም ዘላቂነት እንዳይኖራቸው ተማሪዎች ራሳቸውን ከማሳመን ጀምሮ በበጎ ፈቃደኛ መምህራን እና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመጡ ባለሙያዎች የሚሠጡ ትምህርቶችን በትኩረት መከታተል የሚያስችል ሰፊ ጊዜን መመደብ ይጠበቅባቸዋል ይላል:: በተጨማሪም ተማሪዎች የሚሰጣቸውን የማጠናከሪያ ትምህርቱ በየዕለቱ ሰዓት በመመደብ ማጥናትን ይመክራል:: ለትምህርት አይነቶች የሚመደቡ ሰዓታት  ይዘትን መሠረት  ማድረግ ለውጤት ያበቃሉ:: ይህም በተደጋጋሚ አልገባ ያሉ ሐሳቦችን ጊዜ ሰጥቶ ለመረዳት ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው በመረጃው ተጠቁሟል::

ከትምህርት ውጪ የሆኑ ጊዜያትን ክህሎት ማሳደጊያ አድርጎ መጠቀም እንደሚገባም የክራፍቲንግ ስኮላርስ መረጃ ያሳያል:: የማንበብ፣ የመጻፍ እና የንግግር ክህሎቶችን በአካባቢው ከሚገኙ ልጆች ጋር በመሰባሰብ ማዳበር ይገባል:: በተለይ የንግግር ክህሎትን ለማሳደግ የተለያዩ መጻሕፍትን ማንበብ ተገቢ ይሆናል::

ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ በሚሆኑ ጊዜ የበይነ መረብ አማራጮችን በመጠቀም ከቤታቸው ሆነው መማር እንደሚችሉም የመረጃ አውታሩ ያስረዳል:: እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ያለው የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ፈታኝ ቢሆንም ችግሩን ተቋቁሞ ለቴክኖሎጂ መሠጠት ግን ራስን በዕውቀት ለማብቃት ጉልህ ሚና ይኖረዋል::

በተለይ በዚህ ጊዜ ያለውን ሰፊ ሰዓት ትኩረታቸውን ትምህርት እና ጠቅላላ ዕውቀት ላይ አድርገው የሚሠሩ የተለያዩ ድረ ገጾች /ዌብሳይቶችን እና የዩቱዩብ ቻናሎችን/ ተጠቅሞ ራስን ማብቃት እንደሚገባ ጽሑፉ አመላክቷል:: በተለያዩ ጊዜያት የወጡ የመመዘኛ ፈተናዎችን በቀላሉ ማግኘት መቻሉ ራስን እየመዘኑ ለማብቃት ተመራጭ መንገድ ነው:: ያለን ተሰጥኦ እና የፈጠራ አቅም ለማሳደግም ተመራጭ ናቸው ተብሎ ይታሰባል::

የቴክኖሎጂ አቅምን ማዳበር

ቴክኖሎጂ በራሱ ጥቅም እና ጉዳት አለው:: ጥቅም እና ጉዳቱ ግን የሚመነጨው አጠቃቀምን ተከትሎ በሚፈጠር ክስተት ነው:: እናም ተማሪዎች በእረፍት ጊዜያቸው የሚኖራቸው ሰፊ ጊዜ ላልተገባ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዳርጓቸው ሕይወታቸውን አደጋ ላይ እንዳይጥለው  መረጃዎች አመላክተዋል::

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳጋራው መረጃ ከሆነ የሰው ልጅ ከቴክኖሎጂ ውጪ መኖር አይችልም:: የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ደግሞ በተለይ በልጆች አዕምሯዊ እድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው:: ሕፃናት አዕምሯቸው ፈጣን እንዲሆን፣ የተሳትፎ መጠናቸው እንዲጨምር እና በጥልቀት ማሰብን እንዲለማመዱ የተክኖሎጂ እገዝ ቀላል እንዳልሆነ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያሳያል::

መረጃው እንደ ሚያመላክተው የቴክኖሎጂን አበርክቶ እና መልካም አጠቃቀም በወጉ ለመረዳት የክረምቱን ወቅት ለቴክኖሎጂ ስልጠና ማዋል ይገባል:: የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠናን ደግሞ እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም ይገባል:: የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር በመተባበር ይፋ ያደረጉት ይህ ሥልጠና የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ዜጋ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከማሻሻል ባለፈ በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቁ መረጃዎችን እውነተኛነት ለመመርመር እገዛው የጎላ ነው:: በመሆኑም ተማሪዎች የክረምቱን የእረፍት ጊዜያቸውን ለነገዋ ዲጅታል ኢትዮጵያ ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ማብቃት ይገባል::

በአጠቃላይ ተማሪዎች የክረምቱን ወቅት የእረፍት ጊዜ  በትምህርት እና በቴክኖሎጂ ከማሳለፍ በተጨማሪ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን በሚያጠናክሩ ግንኙነቶች እንዲሳተፉም ይመከራል:: ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሀብቶችን በመጎብኘት ታሪክን  ለመረዳት ወሳኝ ጊዜ ነው:: ከዚህ ውጪ ያሉ ትርፍ ጊዜያትንም በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በመሳተፍ ማሳለፍ ለማኅበራዊ ሕይወት መስተጋብር ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል::

ሠረቀ = ወጣ

ሰረቀ = ሰረቀ

አመት = አገልጋይ

ዓመት = ዘመን

ሰዐለ = ስዕል ሳለ

ሰአለ = ለመነ

መሀረ = አስተማረ

መሐረ = ይቅር አለ

ኀለየ = አመሰገነ

ሐለየ = አሰበ

ፈጸመ = ጨረሰ

ፈፀመ = ነጨ

ማኅሌት = ማመስገን

ማሕሌት = ማሰብ

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የነሐሴ 5  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here