በቻይና መልካዓምድራዊ አቀማመጡ አቀበት ቁልቁለት በሚበዛው የጉይዞ ግዛት ተራሮችን በመላጨት የተደላደለ የፍጥነት መንገድ መገንባት መቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል፡፡
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2025 የባይፓን ወንዝ በፈጠረው ሁጂያን ሸለቆ አናት ከወንዙ ወለል 625 ሜትር ከፍታ ላይ መሸጋገሪያ ተንጠልጣይ ድልድይ መሰራቱ በዚሁ ዓምድ ለንባብ በቅቶ ነበር፡፡
ለምርቃ ከተቃረበው የድልድዩ ግንባታ ሂደት ባሻገር ወደ ድልድዩ የሚያደርሰው የሉአን የፍጥነት መንገድ ከፍተኛ ትኩረት እያገኘ መምጣቱን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
አስደናቂውን የመሰረተ ልማት ግንባታ የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ድረ ገፆች በመለቀቃቸውም ተመልካቾችን እያከራከረ የድጋፍ እና ነቀፌታ ትችቶች እየተስተናገዱ ነው፡፡
የሉአን የፍጥነት መንገድን በመስራት ላይ የሚገኙት ቻይናውያኑ መሀንዲሶች በተራራዎች ውስጥ ቆፍረው ማማዎችን ከመትከል እና ዙሪያውን ከመገንባት የተሻለ አማራጭ ያሉትን ገምግመው እና ፈትሸው ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል – ተራራውን ለመላጨት፡፡
ይህንኑ የተራሮችን ገጽ በስላሽ መቁረጥ ወይም መላጨትን የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ቀጣናው ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ያሳርፋል ሲሉ ተችተዋል፤ ተቃውመዋል፡፡ የሉአን የፍጥነት መንገድ ግንባታ ከፍተኛ ባለሙያዎች ግን ተራራዎቹን ከመላጨት ውጪ ሌሎች አማራጮች አለመኖራቸውን በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡ በያዙት አቋም የፀኑት ባለሙያዎቹ ከየአቅጣጫው ለተሰነዘሩ ቅሬታ እና የቢሆን ሀሳቦች ምላሽ በመስጠት መግፋታቸው በማደማደሚያነት ለንባብ በቅቷል፡፡፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም