ተስፋ ያልቆረጠዉ

0
329

ያቺን ጥቁር  ቀን ፈጽሞ አይረሳትም፤ ያኔ ዕድሜው  አራት ዓመት  ነበር፤ በመንደራቸው ባለ ቁልቋል በተባለ አነስተኛ ወንዝ ውስጥ ገላውን እየታጠበ ባለበት ወቅት ትልቅ ድንጋይ ቀኝ እግሩ ላይ ወደቀ:: በሁኔታው የተደናገጡት ቤተሰቦቹ በወቅቱ  ወደ ባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል አምጥተው ቢያሳክሙትም የልጃቸውን ቀኝ እግር ከመቆረጥ ግን ሊያድኑት አልቻሉም::

የዚህ አሳዛኝ ታሪክ ባለቤት  በደቡብ ጐንደር ዞን፣ ደራ ወረዳ፣ ሽሜ ቀበሌ ተወልዶ ያደገው ወርቅነህ ታረቀኝ ነው:: ወርቅነህ የደረሰበት አካል ጉዳት ከመማር እንደማያግደው ተገንዝቦ በቤተሰቦቹ እንክብካቤ እንደ እኩዮቹ ትምህርት ቤት ገባ::  ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን የተከታተለው በሽሜ ቀበሌ ማር ምድር ትምህርት ቤት ነው:: ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን ደግሞ ከሽሜ ቀበሌ በአምስት ኪሎ ሜትር በምትርቀው የአርብ ገበያ ከተማ አፈር ውኃ እናት ትምህርት ቤት ነው::

ወርቅነህ በሕጻንነቱ በደረሰበት የአካል ጉዳት ምክንያት ከሽሜ ቀበሌ እስከ አርብ ገበያ ከተማ ይመላለስ የነበረው በሰው ሠራሽ   እግር/ክራንች በመታገዝ ነበር:: ወጣቱ  ይሄኛውን የሕይወት ምዕራፉን ሲያጫውተን “የአንድ ሰዓት መንገድ በአንድ እግሬ ተመላልሼ መማሩ ለኔ በጣም አስቸጋሪ ነው:: ነገሮችን አቅልዬ እንዳያቸው የረዳኝ የወላጆቼ ማበረታቻ እና በዚያ መንገድ የሚመላለሱ አሽከርካሪዎች ለኔ ያሳዩኝ የነበረው በጐነት ነው” ብሎናል::

“በአራት ዓመቴ በመንደራችን አቅራቢያ ባለችው የቁልቋል ወንዝ ውስጥ ገላዬን እየታጠብኩኝ ሳለ በዳገት ላይ ተክቦ የነበረ ድንጋይ  ቀኝ እግሬ ላይ ወድቆብኝ የአካል ጉዳተኛ አድርጐኛል:: ቤተሰቦቼ ሳድግ እንደነገሩኝ ከሆነ ‘ቀኝ እግሬ በሐኪሞች የተቆረጠው ሕመሙ ወደ ሌላው አካሌ ከተዛመተ  ለሞት ሊዳርገኝ እንደሚችል ታምኖበት ነው’ ብለውኛል” ሲልም ወርቅነህ የጉዳቱን መንስኤ አብራርቶልናል::

በትምህርቱ መካከለኛ ደረጃ አላቸው ከሚባሉ ተማሪዎች ተርታ ሚመደበው ወርቅነህ በ2015 ዓ.ም በወሰደው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ  ፈተና ግን  አጥጋቢ ውጤት ባለማምጣቱ የልጅነት ህልሙ እስኪሳካ ሌላ የሕይወት ፈተናን ለመጋፈጥ ወደ ባሕር ዳር ከተማ በማቅናት የጫማ ማሳመር ሥራን አንድ ብሎ ጀምሯል::

በተማሪነት ሕይወቱ ውስጥ ወላጆቹ ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የክፍል ጓደኞቹ እና አስተማሪዎቹ ያበረታቱት እንደነበር የሚያስታውሰው ወርቅነህ አንድ እግሩን በአደጋ ማጣቱ የሕይወቱ ፍፃሜ እንዳልሆነ የተገነዘበው ገና በለጋ ዕድሜው ነው:: በተለይም ወላጆቹ የልጃቸው አንድ እግር በአደጋ እንደተቆረጠው ልቡ ተስፋ እንዲቆርጥ ፈጽሞ እንደማይፈልጉ ያደርጉለት ከነበረው እንክብካቤ እና ምክር ወርቅነህ ተገንዝቧል::

አካል ጉዳቱ ማንኛውንም ሥራ ከማከናወን እንደማያግደው ጠንካራ እምነት ያለው ወርቅነህ ከልጅነቱ ጀምሮ  እያለመ ያደገውን የንግድ ሥራ ለማሳካት አቅሙ በፈቀደው መጠን ጥረት እንደሚያደርግ ታዳጊው ተናግሯል::

ለዚሁ እውነታ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የወርቅነህ ወላጆች ባለ አንድ እግር በሆነው ልጃቸው ተስፋ ሳይቆርጡ ትምህርቱን እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ እንዲከታተል ማስቻላቸው ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ የወርቅነህ ወላጆች ልጃቸው በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ባለማምጣቱ ቅር ሳይሰኙ አቅሙ በፈቀደ መጠን ሠርቶ ይለወጥ ዘንድ የጫማ ማሳመሪያ እቃዎችን አሟልተው ባሕር ዳር ካሉ ዘመዶቹ ጋር ሆኖ እንዲሠራ እድሉን አመቻችተውለታል::

እኛም ህልመኛውን ወጣት  ያገኘነው በባሕር ዳር ከተማ፣ ጣና ክፍለ ከተማ   /በድሮ ስያሜው ቀበሌ 16/  ሆምላንድ ሆቴል ፊት ለፊት  አካባቢ ጫማ በማሳመር (ሊስትሮ) ሥራ ላይ ተሰማርቶ ነው:: የአካል ጉዳቱን ሰበብ አድርጐ ከሰዎች መለመንን በእጅጉ እንደሚጠየፍ ታዳጊው  አምርሮ ነግሮናል:: “የተጐዳ እግሬን እያሳየሁ ከምለምን ይልቅ ዛሬውኑ ብሞት ይሻለኛል” የሚለው ወርቅነህ እንኳን እሱ እንደዚህ ዓይነት አሳፋሪ ሀሳብ ሊኖረው ይቅርና በተፈጥሮም ይሁን በሌላ ጉዳታቸው ሰበብ የሚለምኑ ሰዎችን ሲያይ እንደሚንቃቸው ገልፆልናል::

በክልላችን ሆነ በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ በርካታ የአካል ጉዳተኞች በልመና ተግባር ላይ ቢሰማሩም እንደ ወርቅነህ ያሉ ጠንካራ ወጣቶች ደግሞ አቅም በፈቀደ መጠን ሠርቶ መለወጥን ሲያልሙ ማየት በእጅጉ ደስ ያሰኛል:: ታዳጊው እንደሚለው”ወላጆቼ በሕይወት እስካሉ ድረስ ምጽዋት ስጠይቅ ሊያዩኝ እንደማይፈልጉ እየነገሩኝ ነው ያደግሁት፤ ያም ብቻ ሳይሆን የእግሬን መጐዳት ሰበብ አድርጌ የምለምን ከሆነ ያን ጊዜ ከእግሬ በተጨማሪ አእምሮዬም መጐዳቱን ወላጆቼ እየነገሩኝ ስላደግሁ ልመናን ፈጽሞ የማልሞክረው ነገር ነው” ብሎናል ጠንካራው ብላቴና::

ከሽሜ ቀበሌ እስከ አርብ ገበያ ያለውን አምስት ኪሎ ሜትር ከእድሜ እኩዮቹ ጋር ሲጓዝ የእግር ጉዳተኛ ነኝ ብሎ እንደማያስብ እና የበታችነት ስሜት ፈጽሞ ተሰምቶት እንደማያውቅም ወርቅነህ አጫውቶናል:: “የምጽናናባቸው ከኔ የባሱ በርካታ የአካል ጉዳተኞችን ስለማይ እኔ ለአንድም ቀን ቢሆን ፈጣሪዬን በጉዳቴ ምክንያት አማርሬው አላውቅም:: እንዲያውም በተቃራኒው በኔ ተስፋ ሳይቆርጡ እኔ ተስፋ እንዳልቆርጥ የሚያደርጉ ወለጆቼን ስለሰጠኝ ፈጣሪዬን ሁሌም አመሰግነዋለሁ” ብሎናል::

ለአካል ጉዳተኞች ከንፈር በመምጠጥም ሆነ ሳንቲም በመስጠት ሕይወታቸውን መቀየር እንደማይቻል የሚናገረው ወርቅነህ ይልቁንም ጉዳተኞቹ በዘላቂነት ራሳቸውን የሚችሉበትን መላ መዘየድ ተገቢ ነው ብሎ እንደሚያምን ሀሳቡን አጋርቶናል:: “ለትምህርት ከሽሜ ቀበሌ እስከ አርብ ገበያ ስመላለስ የእግር ጉዳቴን እያዩ በመኪናቸው ያሳፍሩኝ ለነበሩ የዚያ አካባቢ አሽከርካሪዎች በሙሉ ምስጋናዬ ከልብ ነው! አስተማሪዎቼም በሚያደርጉልኝ ድጋፍ ሙሉ አካል ያለኝ ዓይነት ስሜት እንዲያድርብኝ አድርገዋልና ለእነሱም ምስጋና ይግባቸው!” በማለት ለዛሬ ላበቁት፣ ነገን በተስፋ እንዲናፍቅ ላስቻሉት ሁሉ ምስጋናው እንዲደርሳቸው ጠይቋል::

ብዙ ልጆች በሕጻንነታቸው ምን መሆን እንደሚፈልጉ ሲጠየቁ ዶክተር፣ ፓይለት፣ ኢንጂነር… ወይም ሌላ እንደሚሉ ያስታወሰው ወርቅነህ እርሱ ግን ከልጅነቱም ጀምሮ ነጋዴ የመሆን ምኞት እንደነበረው አጫውቶናል:: ነጋዴ ለመሆን ያነሳሳውን ምክንያት በውል ባያውቀውም አሁን ላይ አካል ጉዳተኛ በመሆኑ ብቻ ከምኞቱ የሚስተጓጐል እንደማይመስለውም ነው ወርቅነህ የገለፀልን::

በባሕር ዳር ጫማ ማሳመር /ሊስትሮነት/ ሥራን ከጀመረ ገና አጭር ጊዜው ቢሆንም ጫማ የሚያሳምርላቸው ሰዎች ጥንካሬውን በመመልከት የሚሰጡት  “አይዞህ!” የሚል የማበረታቻ ሀሳብ እና ድጋፍ ነጋዴ የመሆን ህልሙ መንደርደሪያ እንደሚሆነውም ወርቅነህ ተስፋ አድርጓል::

“ጫማቸውን የሚያስጠርጉኝ ሰዎች ጫማ ለመጥረግ ሥራ እንግዳ መሆኔን ካወቁ በኋላ አሠራሬን ከማውገዝ ይልቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደምሻሻል እና እንድበረታ ይነግሩኛል፤ ይሄ ለኔ ጫማቸውን አሳምሬ ከሚሰጡኝም ገንዘብ የበለጠ ትልቁ ስጦታዬ ነው” ያለን ወርቅነህ የሚያግዘው ተቋም ወይም ድርጅት ቢያገኝ ሠርቶ ለመለወጥ ዝግጁ መሆኑንም ገልፆልናል::

“ሠርቼ ልለወጥ ማለቴ እንደዘመናዊ ልመና እንዳይታይብኝ፤ በኔ ሠርቶ መለወጥ ምክንያት ብዙ የአካል ጉዳተኞች ለምነው ሳይሆን ሠርተው መለወጥን ያስቀድማሉ” ሲልም መረዳት የሚፈልግበትን አመክንዮ አስቀምጧል::

ወደ ባሕር ዳር ከተማ ከመጣ ገና አጭር ጊዜው በመሆኑ ከአካል ጉዳት ጋር የሚሠሩ ተቋማትንም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች የማግኘት እድል እንዳልገጠመውም አጫውቶናል:: እኛም እንደ ወርቅነህ ታረቀኝ ያሉ የአካል ጉዳተኞች ከአካል ጉዳታቸው በተጨማሪ የሥነ ልቦና ጉዳት እንዳይገጥማቸው አቅም በፈቀደ መጠን ማገዝ ይገባል እንላለን:: ያልሆኑትን ሆነው ወይም አስመስለው የሚለምኑ ሰዎች በበዙባት ሀገራችን ውስጥ በተቆረጠው እግሩ ተስፋ ሳይቆርጥ ከምኞቱ ጫፍ ላይ ለመድረስ የሚታትረውን ወጣት ወርቅነህ ታረቀኝንም መዳረሻ ግብ ስላለህ ካሰብክበት ቦታ እንደምትደርስም ባለ ሙሉ ተስፋ ነን ልንልህ እንወዳለን::

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here