ይህ ስም ባለፉት አራት ዓመታት በስፖርቱ ዘርፍ ተደጋግሞ ተነስቷል፣ እርሱ በተሳተፈበት መድረክ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ክብረ ወሰኖችም ተሰብረዋል። ገና 24 ዓመት እድሜ ላይ ቢገኝም እስካሁን ስምንት ክብረ ወሰኖችን አሻሽሏል፣ በትውልዱ ማንም ላያወርደው ስሙ ከፍ ብሎ ተሰቅሏል። የጋዜጦች እና የመጽሔቶች አለፍ ሲልም የተለያዩ ሚዲያዎች ወግ ማድመቂያ ከሆነም ሰነባብቷል- ስዊድናዊው የምርኩዝ ዝላይ አርማንድ ዱፕላንቲስ።
አርማንድ ዱፕላንቲስ ወይም በቅጽል ስሙ ሞንዶ በምድራችን በምርኩዝ ዝላይ ስፖርት ክስተት የሆነ ስፖርተኛ ነው። ታሪኩ ከዚህ ይጀምራል፤ ዱፕላንቲስ በ1999 እ.አ.አ ከአሜሪካዊው አባቱ እና ከስዊድናዊት እናቱ አሜሪካ ውስጥ ተወለደ፤ አባቱ አርማንድ ጉስታቭ የቀድሞ የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ የነበረ ሲሆን እናቱም የቀድሞ የቮሊቦል ስፖርተኛ እንደነበረች ከታሪክ ማህደራቸው የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከስፖርተኛ ቤተሰብ የወጣው ዱፕላንቲስ ገና በልጅነት እድሜው ነበር የምርኩዝ ዝላይ ስፖርትን መለማመድ የጀመረው። በግል የታሪክ ማህደሩ እንደሰፈረውም ከሦስት ዓመታት እድሜው ጀምሮ የምርኩዝ ዝላይ ስፖርትን በቤት ውስጥ አባቱ ያለማምደው እንደነበረ ተቀምጧል።
በሰባት ዓመቱ ደግሞ የወደፊት የዓለማችን ቁንጮ የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ የሰጠበት እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል። ምንም እንኳ ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ከስድስት እስከ 19 ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊዎች የሚያስመዘግቡትን ክብረ ወሰን መመዝገብ ቢያቆምም ዱፕላንቲስ እስከ 12 ዓመቱ ድረስ ከእድሜ እኩዮቹ ጋር በመወዳደር 13 ክብረ ወሰኖችን አሻሽሏል።
በወቅቱም የታዳጊውን አቅም እና ብቃት የተመለከቱት ስዊድን እና አሜሪካ ሀገራችውን እንዲወክል ሽሚያ ውስጥ ገብተዋል። በመጨረሻ ግን ታዳጊው ዱፕላንቲስ ስዊድንን መርጧል። በ2015 እ.አ.አ በኮሎምቢያ ካሊ በተደረገው ከ18 ዓመት በታች የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ በመወዳደር አምስት ሜትር ከ30 ሴንቲ ሜትር በመዝለል የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር አሸንፏል።
እ.አ.አ በ2018 በተሳተፈበት ከ20 ዓመት በታች የዓለም ሻምፒዮና ደግሞ ከስድስት ሜትር በላይ በመዝለል ዓለምን ጉድ አሰኝቷል። ውጤቱም በመድረኩ የአውሮፓውያን የመጀመሪያው ትልቁ ውጤት እንደነበረ አይዘነጋም። ዱፕላንቲስ በወቅቱ የዘለለው ስድስት ሜትር ከአምስት ሴንቲሜትርም በምርኩዝ ዝላይ ስፖርት ታሪክ አምስተኛው ትልቁ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል።
የምርኩዝ ዝላይ ኮከቡ በሚወዳደርባቸው መድረኮች ሁሉ በየጊዜው አዳዲስ የዓለም ክብረ ወሰኖችን ማስመዝገቡን ቀጥሏል። በፈረንጆች 2020 ሚያዚያ ወር ክብረ ወሰን ባሻሻለበት በ11 ቀናት ልዩነት ሌላ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በመስበር ዓለምን ጉድ አሰኝቷል። በፍጥነት እያደገ እና እየተሻሻለ የመጣው ወጣቱ ስፖርተኛ በ2021ዱ የቶኪዮ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፉም የሚታወስ ነው።
በዱፕላንቲስ ብቃት እና ችሎታ ተመልካች ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪዎቹም እንደሚደነቁ ይነገራል። በእግር ኳስ ስፖርት ታላላቆቹ ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ያበረከቱትን ያህል አስተዋጽኦ ዱፕላንቲስ በምርኩዝ ዝላይ ስፖርት እንደ ተረት የሚተረክ አስደናቂ ገድል እየፈጸመ ስለመሆኑ ተፎካካሪዎቹ ሳይቀር ይመሰክሩለታል።
በየትኛውም መድረክ ዱፕላንቲስ ካለ ተፎካካሪዎቹ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ለመጨረስ እንደሚወዳደሩ ይነገራል። “ሞንዶ የተለየ ነው፣ እርሱ በውድድሩ ካለ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ለማጠናቀቅ እንደሚፎካከሩ ኮሜንታተሮች ሳይቀር ይመሰክራሉ” ሲል በቶኪዮ ኦሎምፒክ በምርኩዝ ዝላይ የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ክሪስ ኒል ከዓለም አትሌቲክስ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።
እስካሁን በተሳተፈባቸው ሦስት የዲያመንድ ሊግ ውድድሮች በሰፊ ልዩነት አሸናፊ ሆኖ አጠናቋል። በቻይና ዣሚን በተከናወነው በዘንድሮው የዲያመንድ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በመስበር ጭምር ነው ያሸነፈው። ዱፕላንቲስ ስድስት ሜትር ከ24 ሴንቲ ሜትር የዘለለ ሲሆን ስምንተኛ ክብረ ወሰኑ ሆኖ ተመዝግቧል።
በምርኩዝ ዝላይ ስፖርት ታሪክ በተከታታይ 15 ውድድሮችን በማሸነፍም ቀዳሚው ባለታሪክ ስፖርተኛ ነው። ስዊድናዊው ስፖርተኛ በ2023ቱ የዋንዳ ዲያመንድ ሊግ ስድስት ሜትር ከ23 ሴንቲ ሜትር መዝለሉ አይዘነጋም። ዘንድሮ ግን ገና በመጀመሪያው ዙር ባሳየው አስደናቂ ብቃት በቀጣይ ባሉት 14 የዲያመንድ ሊግ ዙሮች በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።
የዘርፉ ባለሙያዎችም በቀጣይ የዲያመንድ ሊግ ውድድሮች የራሱን ክብረ ወሰን በማሻሻል ከዚህም ከፍ ባለ ደረጃ ሊቀመጥ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል። በእርግጥ ዱፕላንቲስም ህልሙ ስድስት ሜትር ከ30 ሴንቲ ሜትር እና ከዛ በላይ ከፍታ የመዝለል አቅም እንዳለው ከሲኤን ኤን ስፖርት ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ ተናግሯል። “በታሪክ የበላይ መሆን እፈልጋለሁ፤ እያንዳንዱን ውድድር ለማሸነፍ እና ክብረ ወሰን ለማሻሻል እየሰራሁ ነው” ሲል ተደምጧል።
አብዛኞች ስፖርተኞች በአስራዎች የእድሜ ክልል ውስጥ ይህንን ስፖርት እንደሚጀምሩ ይነገራል። ታዲያ የ24 ዓመቱ ስዊድናዊ ገና በእግሩ መሄድ ሲጀምር ከስፖርቱ ጋር መተዋወቁ አሁን ለደረሰበት ስኬት አስተዋጽኦ እንዳደረገለት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የምርኩዝ ዝላይ ስፖርት ፍጥነት፣ ጥንካሬ፣ የመተጣጠፍ ችሎታ፣ ድፍረት፣የአዕምሮ ብስለት እና አካላዊ ዝግጅት ይፈልጋል።
ባለ ተሰጥኦው የምርኩዝ ዝላይ ስፖርተኛው ዱፕላንቲስ ስፖርቱ የሚጠይቀውን ሁሉ ማሟላቱ ውጤታማ እንዲሆን አስችሎታል። ባለፉት አራት ዓመታትም በምርኩዝ ዝላይ ስፖርት ወደር አልተገኝለትም። አንድ ኦሎምፒክ፣ አራት የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም 22 ጊዜ ከስድስት ሜትር ከፍታ በላይ በመዝለል አጃኢብ አሰኝቷል።
ለአብነት በ2023 በፈረንጆች ብቻ 11 ውድድሮችን ስድስት ሜትር ከፍታ እና ከዛ በላይ መዝለሉን መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ ወቅትም አትሌቱ ከፍተኛ የብቃት ደረጃ የደረሰበት ወቅት እንደነበር ተገልጿል። ሁለት የቤት ውስጥ እና የውጪ ውድድሮችን በማሸነፍ በምርኩዝ ዝላይ ስፖርት ገና በወጣትነት እድሜው ቁንጮ ላይ ተቀምጦ በርካታ ክብሮችን ተጎናጽፏል።
በዘርፉ አስደናቂ ታሪክ ያለው የቀድሞው የምርኩዝ ዝላይ ስፖርተኛ ሰርጌ ቡብኬ ቀዳሚው ነው። ዩክሬናዊው የቀድሞ ስፖርተኛ በተከታታይ አራት የዓለም ሻምፒዮናዎችን በማሸነፍ ባለክብረ ወሰን ነው። በተመሳሳይ በኦሎምፒክ መድረክ የበርካታ ሜዳሊያዎች ባለቤት ጭምር ነው።
ቡብኬ በ38 ዓመቱ ነበረ ከስፖርት ራሱን ያገለለው። ታዲያ ሞንዶ ዱፕላንቲስ ገና ብዙ ታሪኮችን ሊያስመዘግብ እንደሚችል በብዙዎች ተስፋ ተጥሎበታል። የቀድሞው ባለተሰጥኦ በምርኩዝ ዝላይ ህይወቱ ከ60 የሚልቁ ውድድሮችን ስድስት ሜትር እና ከዛ በላይ ከፍታ መዝለሉን መረጃዎች አመልክተዋል።
እናም በዱፕላንቲስ ተሰጥኦ የተደመሙ ሁሉ ከቀድሞው የምርኩዝ ዝላይ ስፖርተኛ ሰርጌ ቡብኬ ጋር እያመሳሰሉት ይገኛሉ። ገና እድሜው 24 በመሆኑ በዘርፉ የተሻለ ስፖርተኛ የመሆን ሰፊ ዕድል እንዳለው ጭምር በመናገር።
በ2018 እ.አ.አ ዱፕላንቲስ የአውሮፓ እና የዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ ምርጥ ወንድ ስፖርተኛ ሽልማትን አሸንፏል። የዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ ምርጥ አትሌት በመባል ሦስት ጊዜ መመረጥ ችሏል። ይህም በታሪክ ሽልማቱን ሦስት ጊዜ የወሰደ ሦስተኛው አትሌት ሆኗል።
የ2024ቱን የዲያመንድ ሊግ ለአራተኛ ጊዜ ያሽንፋል? በመጪው ክረምት በፓሪስ ኦሎምፒክ ምን ዓይነት ብቃትስ ያሳያል? የሚለውን የስፖርት ቤተሰቡ በጉጉት የሚጠብቀው ነው።
13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ባሳለፍነው የካቲት ወር መከናወኑ የሚታወስ ነው። ሀራችንም ከተሳተፈችባቸው ስፖርቶች መካከል የምርኩዝ ዝላይ አንዱ ሲሆን በአበራ ዓለሙ አማካኝነት የብር ሜዳሊያ ማግኘቷ አይዘነጋም። በዘርፉ የተገኘው ውጤትም በሀገራችን ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ እና ደቡብን በመሳሰሉ ክልሎች ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ ተፎካካሪ በመሆን ተጨማሪ ሜዳሊያዎች ሊመዘገቡበት የሚችል ዘርፍ መሆኑን ተመልክተናል፡፡
ሲኤን ኤን ስፖርት፣ ዩሮ ሰፖርት እና የዓለም አትሌቲክስን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም