አምላኩን አምኖ ሰማዩን አይቶ ወደ እርሻ የሄደው አርሶ አደር የድካሙን ውጤት በመሰብሰብ ላይ ነው:: አሁን ከተፈጥሮ ዶፍ እና በረዶ በጸሎት የተረፈለትን ምርቱን የመሰብሰቢያው መኸር ወቅት ገብቷል:: ምንም እንኳን ባለፈው ዓመት የተጀመረው የአማራ ክልል ግጭት ስጋት ቢፈጥርበትም ሀገር መጋቢው አርሶ አደር ተስፋ ሳይቆርጥ ከአምላኩ ተማክሮ ሲያመርት ክርሟል::
ለሀገሪቱ ትልቅ የምርት ድርሻ ያለው የአማራ ክልል አርሶ አደት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የእርሻ ሥራቸውን የከወኑት የሰላም ተስፋን ይዘው ነው:: በሰላም እንሰበስበዋለን እያሉ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ አርሰዋል፤ በከባድ ወቅቶች ዘርተዋል፤ በስጋት ውስጥ ሲያርሙና ሲኮተኩቱ ከርመዋል፤ የልፋታቸውን ፍሬ ምርታቸውን ለመሰብሰብ ደግሞ ተዘጋጅተዋል:: መሰብሰብ የጀመሩም አሉ::
በስጋት የዘሩትን የድካም ፍሬ በደስታ እንዲያጭዱ በሰላም ወጥተው እንዲመለሱ ሰላም ያስፈልጋል:: በግብርና ላይ የሚደረግ የትኛውም ጥቃት ይሁን ግጭት በጉሮሮ ላይ ማመጽ ነው:: አጉራሾቻችን የዘሩትን የልፋት ውጤት በሰላም እንዲሰበስቡ የሰላም ፋታ እና ሰላማዊ ከባቢ ያስፈልጋል:: “በመከራ የዘሩ በደስታ እንዲያጭዱ መፍቀድ” ሀገርን ከከፋ የኢኮኖሚ ጫና መታደግ ነው::
80 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ አርሶ አደር የሆነባት ሀገር ኢትዮጵያ ግጭቶች ገጠሩን ማዕከል ማድረጋቸው የግብርና ሥራ እንቅስቃሴን በእጅጉ ያውከዋል:: በግጭቶች ምክንያት አጉራሽ እጆች ለልመና እና ለጦርነት እንዳይዘረጉ የአርሶ አደሩን ሰላም መጠበቅ እና ምርቱን እንዲሰበስብ ማድረግ ከሁሉም ወገን ይጠበቃል::
የግብርናው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎችን በብርቱ ጡንቻዎቹ ለመመከት ሞክሯል:: በዚህ ትግል አልፎም ሀገር እየመገበ ነው:: ቢያንስ ሰው ሠራሽ ችግሮቹ በሰው መቆም አለባቸው:: ተፈጥሮው መቼ አነሰውና:: ለአርሶ አደሩ ምርቱን በሰላም እንዲሰበስብ ዕድል መስጠት የሀገርን ሰላም ማስጠበቅ ነው:: የምርት አሰባሰባችን ቀድሞውንም ብክነቶች የሚያጡት አይደለም:: ግጭቶች ሲታከሉበት ደግሞ የበለጠ ለጉዳት ይዳረጋል:: አርሶ አደሩ በግጭት ውስጥ ሲሆን ምርቱን ለመሰብሰብ ይቅርና ውሎ ለማደር መቸገሩ አይቀርም:: “ተንጋለው ቢተፉ ተመልሶ በአፉ እንዳይሆን” የትኛውም አካል ለምርት በሰላም መሰብሰብ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ሀገርን ከከፋ የምርት እጥረት እና ተያያዥ ጉዳት መከላከል አለበት::
በየትኛውም ሀገር የሚደረጉ ግጭቶች የግብርና ሥራዎችን ከግጭት ነጻ የሚያደርጉት የግብርና ጉዳይ የሕልውና በመሆኑ ነው:: እንኳንስ አቅማዳውን ይዞ ምርት ለመሰብሰብ የሚጠብቅን አርሶ አደር ይቅርና እርሻ ያለን ገበሬም ቢሆን በግጭቱ መጉዳት ተንጋሎ እንደመትፋት ነው:: የደረሰው ሰብል የማሳ ሲሳይ ሆኖ እንዳይቀር አርሶ አደሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላም የሚሻበት ወቅት አሁን ነው፤ ሁላችንም ለሰላም መስፈን ልንረባረብ ይገባል::
በኲር ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም