ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት

0
126

የሕግ ሥርዓት በመርህ ደረጃ ከክስ ጀምሮ እሰክ ቅጣት ውሳኔ ድረስ ያሉት ሂደቶች ተከሳሹ ባለበት መከናወን አለባቸው::ተከሳሽ ችሎት በመቅረብ የቀረበበትን ክስ የመረዳትና የመከላከል መብት አለው፤ ምክንያቱም ተከሳሽ ጉዳዩ ሲታይ  በችሎት መገኘቱ ክሱን በበቂ ሁኔታ ለመከላከል እጅግ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ነው::ይሁን እንጅ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሀገራት ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ የሚታይበትን ሥርዓት በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጋቸው ተካቶ እንደሚገኝ  የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የመደበኛ ወንጀል አቃቢ ሕግ አቶ አስማማው በላይ አብራርተውልናል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴሬላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንሥግሥት በአንቀጽ 20 በወንጀል ተጠርጥሮ የተከሰሰ ሰው ፍርድ ቤት ሲቀርብ ክሱ ቀድሞ ደርሶት እና ተረድቶት የመስማት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለው ይደነግጋል::በዚህም መሰረት በቂ ዝርዝር ተነግሮት ማስረጃ የመመልከት፣ በመረጠው ጠበቃ መከራከር፣ ጠበቃ መቅጠር ካልቻለ መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምለት እንዲሁም ክሱ በሚገባው ቋንቋ ተተርጉሞ እንዲቀርብለት ሕገ መንግስጡን ጠቅሰው የዐቃቢ ሕግ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ አስማማው ገለጻ ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ የመስማት ሂደትም ይከናወናል:: ይህም ተከሳሹ ፈጽሟል በተባለው ወንጀል በፍርድ ቤት  በሌለበት በመታየት ላይ የሚገኝ ማለት ነው::ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት ተገቢነቱ መታየት ያለበት ከወንጀል ሕጉ ዓላማ፣ ከፍትሕ እና ከሰብዓዊ መብት አንፃር ነው፡፡

አንድ ሰው የወንጀል ክስ በሚቀርብበት ወቅት ክሱን በአካል ቀርቦ የመደመጥ ተፈጥሯዊ የሆነ ሰብዓዊ መብቱ አለው:: ይህም በሕገ መንግሥቱ በቂ ከለላ ተሰጥቶታል::ሆኖም በተወሰኑ የወንጀል ጉዳዮች ላይ ተከሳሾች በሌሉበት ጉዳያቸው ሊታይ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ባለሙያው ጠቁመዋል::

ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት የሚፈቀደው በተወሰኑ ጉዳዮች ብቻ ነው::ይህም የተደረገበት ምክንያት ሰው ፍርድ ቤት ቀርቦ የቀረበበትን ክስ አውቆ እና ተደምጦ ካልተወሰነ የተፈጥሯዊ ፍትሐዊ መርህን የሚጣረስ በመሆኑ ነው፡፡

ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ ለመስማት በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ እና በመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ላይ ተደንግጓል::ባለሙያው አቶ አስማማው እንደሚገልፁት ክስ ሊሰማ የሚችለው በመርህ ደረጃ ተከሳሽ ባለበት እንደሆነ በሕግ ደንግጓል::ነገር ግን የጥፋተኝነት ውሳኔ ለመወሰን ተከሳሹ መጥሪያ በአካባቢው ተልኮ፣ ፓሊስ በአድራሻው ወስዶ ከሰጠው አልያም ተከሳሹን ካጣው በመኖሪያ ቤቱ ወስዶ ከለጠፈ፣ መኖሪያ ቤቱ ተፈልጎ ከታጣ ደግሞ ለሚኖርበት ቀበሌ አስተዳደር አለማግኘቱን በጽሑፍ ካሳወቀ በኋላ የመጨረሻ መጥሪያ በጋዜጣ እንዲጠራ ይደረጋል::

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሰረት ተከሳሽ ይህ ሁሉ ጥረት ተደርጎ ያለ በቂ ምክንያት የተከሰሰበትን ጉዳይ ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ሳይቀርብ ከቀረ  ፍርድ ቤቱ አለመቅረቡን በመዝገቡ ከጻፈ በኋላ በሌለበት እንዲሰማ ያዝዛል::

በልዩ ሁኔታ ግን ከአስራ ሁለት ዓመት በታች በማያንስ ፅኑ እስራት የሚያሳስር ወንጀል የሠራ ወይም በቀድሞው በ1949 ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ  ከቁጥር 354 እሰክ 365 ድረስ ያሉትን ከባድ ውንብድና ፣ የባህር ላይ ውንብድና፣ ዘረፋ  እንዲሁም በመንግሥት እና በሀገር ደህንነት ላይ ወንጀል የፈጸመ   ወይም በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በላይ  በሚያስቀጣ ወንጀል የተከሰሰ ሰው  ለፈጸማቸው እነዚህ ወንጀሎች እንዲከላከል  ተጠይቆ   ለፍርድ በተቀጠረ ቀን ሳይቀርብ ቢቀር እና ቢጠፋ  የፍርድ ሂደቱ በሌለበት ሊሰማ ይችላል፡፡

እንደ ዐቃቢ ሕግ ባለሙያው ገለጻ ተከሳሽ የተመሰረተበትን ክስ  እንዲከላክል ዐቃቤ ሕግ  እድል ሰጥቶት  ፍቃደኛ ካልሆነ ጉዳዩ በሌለበት የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲሰጥ በማንኛውም አይነት ክስ ላይ ይጠይቃል::በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ በመስጠት ቅጣት እንዲተላለፍ ይደረጋል፡፡

ባለሙያው አጽንኦት የሰጡት ጉዳይ  ተከሳሽ ከሌለ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ወንጀሎች በቂ ክርክር ስለማይኖር ጥፋተኛ ተብሎ የመወሰን አጋጣሚው  ከፍተኛ ስለሆነ እና የተከሳሽን መብትም ስለሚጋፋ ሁሉም ወንጀሎች ተከሳሹ በሌሉበት አይታይም::ለአብነት የመግደል ሙከራ ወንጀል ከአምስት ዓመት ጀምሮ እስከ 20 ዓመት ያስቀጣል::ነገር ግን የተከሳሹን የመከራከር መብት ላለመጋፋት  በሌለበት የሚታይ ወንጀል እንዳልሆነ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት መወሰኑን ይገልፃሉ፡፡

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ  መሠረት በሌሉበት ውሳኔ ለመወሰን በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ከ160 ጀምሮ  ሰፍሯል::161 ንኡስ አንቀጽ ሁለት “ሀ” እና “ለ” ላይ በዕድሜ ልክ እና በሞት የሚያስቀጣ ፣ ከ12 ዓመት እና ከዛ በላይ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል አልያም ደግሞ ከአምስት ሺህ ብር በላይ በመንግሥት ኢኮኖሚላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች እንደ ቀረጥ፣ ታክስ ፣ ማዕድን… ወንጀሎች አንደሆኑ ተቀምጧል::ይሁን እንግ ተከሳሹ በሌለበት ከተወሰነ በኋላ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ውሳኔውን በሰጠው ፍርድ ቤት በመቅረብ መጥሪያ ያልደረሰበትን እና ያልቀረበበትን ምክንያት በበቂ ማስረጃ ካቀረበ ጉዳዩ በዛው ሳይሆን በሌላ ተመሳሳይ ደረጃ ባለው ፍርድ ቤት እንደገና ቀርቦ ክርክር ማድረግ እና የቀድሞው ውሳኔ ሊሰረዝ የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖር ነው ባለሙያው የገለፁት፡፡

ተከሳሹ በሌለበት የተሰጠ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተከሳሹ በተገኘ ጊዜ ይርጋ እስካላገደው ድረስ እንደ ክሱ ሁኔታ ተፈፃሚ የሚሆን እንደሆነም ነው ባለሙያው ያብራሩት፡፡

( ማራኪ ሰውነት)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here