የክረምቱ አሰልቺ ዝውውር

0
15

በእግር ኳሱ ዓለም ሜዳ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጭ የሚፈጠሩ ክስተቶችም በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ ትልቅ ትኩረት ይሰጣቸዋል። የተጫዋቾች ዝውውር  ጉዳይ እና ከጀርባ የሚነገሩ ሚስጥሮች የጨዋታውን ያህል የደጋፊውን ቀልብ ከሚስቡት መካከል ይጠቀሳሉ። በያዝነው የክረምቱ የዝውውር ወቅት ደግሞ የስዊድናዊው ኮከብ አሌክሳንደር ኢሳቅ  ጉዳይ በአውሮፓ ዝውውር ትልቁ መነጋገሪያ ነበር። በመጨረሻ ግን ዝውውሩ እውን ሆኗል፡፡ ሊቨረፑል 130 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ ከፍሎ አስፈርሞታል፡፡ ይህም የፕሪሚየር ሊጉ ክብረወሰን ሰብሯል፡፡

የኒውካስል ዩናይትድ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ኢሳቅ በክለቡ እንደተከዳ እና ቃል የተገባለት እንደተጣሰ በይፋ መግለጹ የእግር ኳሱን ዓለም አስደንግጦ ነበር።  የዝውውር ገበያውን ከማናወጡም በላይ ተጫዋቹ ከክለቡ እና ከደጋፊዎች ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻክር አድርጎታል። “ለረጅም ጊዜ ሌሎች ሲናገሩ እኔ ዝምታን መርጬ ነበር። ይህ ዝምታዬ ሰዎች የራሳቸውን እውነት ያልሆነ ትርክት እንዲፈጥሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡ “ክለቡ አቋሜን ለረጅም ጊዜ ያውቅ ነበር። ጉዳዩ አዲስ እንደሆነ ማስመሰል ትክክል አይደለም። ቃል የተገባልኝ ሲጣስ ግንኙነታችን እንደቀድሞው ሊቀጥል አይችልም።” ሲል በኒውካስትል ዩናይትድ ያለውን ቅሬታ በግልጽ ተናግሯል።

ኢሳቅ በግልጽ ” ሴንት ጀምስ ፓርክን መልቀቅ ክለቡንም እኔንም የሚጠቅም ነው” ማለቱ በኒውካስትል የመቆየት ፍላጎት እንደሌለው ነበር የሚያመለክተው። የፕሪሚየር ሊጉ የዓመቱ ምርጥ ሽልማት ስነ ስርዓት ላይ አለመገኘቱ ከኒውካስትል ጋር ያለው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ መሻከሩን የሚያሳይ ትልቅ ምልክት እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል። ይህ ክስተት በኢሳቅ እና በኒውካስትል መካከል የነበረው ወርቃማ ዘመን ማብቃቱን እና አዲስ ምናልባትም አወዛጋቢ የሆነ ምዕራፍ መጀመሩን ያበሰረ ነበር።

የአሌክሳንደር ኢሳቅ ቅሬታውን ከተነፈስ  በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ኒውካትል ዩናይትድ  ሲዊድናዊው አጥቂ በዚህ ክረምት ክለቡን መልቀቅ እንደሚችል ከክለቡ ባለስልጣን ምንም አይነት ቃል እንዳልተገባለት በግልጽ በመግለጫው ተናገሯል። “ምርጥ ተጫዋቾቻችንን ማቆየት እንፈልጋለን፤ ነገር ግን የተጫዋቾችን ፍላጎትም እንረዳለን፤ አመለካከታቸውንም እናዳምጣለን።

በዚህ ክረምት ለዝውውር ያስቀመጥናቸው ቅድመ ሁኔታዎች አልተሟሉም ወደፊትም ይሟላሉ ብለን አናምንም።” በማለት አጥቂውን በቀላሉ እንደማይለቁት ፍንጭ ሰጥተው ነበር። ነገር ግን ዝውውሩ በይፋ ሊዘጋ የሰዓታት እድሜ ሲቀረው ሁሉም ነገረ መጠናቀቁን ፋብሪዚዮ ሮማኖ ተናግሯል፡፡

አሰልጣኝ ኤዲ ሃው ከኢሳቅ ጋር በግላቸው ምንም አይነት ችግር እንደሌለባቸው እና ተጫዋቹ ሃሳቡን ቢቀይር  የቡድኑ አባላት በደስታ እንደሚቀበሉት ቢናገሩም ከመሄድ ግን አላስቀሩትም። ኢሳቅ ከቅድመ ውድድር  ዝግጅት ጀምሮ ከቡድኑ ተለይቶ በቀድሞ ክለቡ ሪያል ሶሴዳድ የልምምድ ማዕከል በግሉ ልምምድ ሲያደረግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

በኒውካስትል የተጠየቀው የዝውውሩ የገንዘብ መጠን ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አወሳስቦት ነበር። ሊቨርፑል ያቀረበው 110 ሚሊዮን ፓውንድ መነሻ ዋጋ ውድቅ የተደረገ ሲሆን ኒውካስትል 150 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ለጥፎበት ነበር። በመጨረሻ ግን ሁለቱንም ክለቦች በሚስማማ መንገድ ዝውውሩ አልቃል፡፡

ኢሳቅ ከክለቡ ጋር ለረጅም ዓመታት የሚያቆየው የውል ስምምነት ነበረው፡፡ ተጫዋቹ በቀላሉ እንዲለቅ የሚያስችል “የመልቀቂያ አንቀጽ” (release clause) አለመኖሩ ክለቡ በዝውውሩ ላይ ሙሉ ስልጣን እንዲኖረው አስችሎታል። ይህም የኒውካስትል ዩናይትድን መልካም ፈቃድ ከመጠበቅ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረውም።

ኒውካስል ዩናይትድ  ለኢሳቅ ያላከበረው ቃል ምንድን ነበር?  ከመጋረጃ ጀርባ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የውዝግቡ ዋና መንስኤ ተጫዋቹ ጠይቆት የነበረው የውል ማሻሻያ እና የደሞዝ ጭማሪ ሳይፈጸምለት በመቅረቱ ነው። ባለፉት ዓመታት ተጫዋቹ አስደናቂ ብቃቱን ማሳየቱ አይዘነጋም።

በተለይ በ2023/24 የውድድር ዘመን ኢሳቅ ለኒውካስትል በ40 ጨዋታዎች 25 ግቦችን በማስቆጠር የቡድኑ መሪ ተዋናይ እንደነበር አይዘነጋም። በዚህ ወቅት ታዲያ የክለቡ የቀድሞ ባለድርሻ የነበረችው አማንዳ ስቴቭሊ ለተጫዋቹ የውል ማሻሻያ እንደሚደረግለት ቃል ገብታለት ነበር።

ነገር ግን በክለቡ አስተዳደር መዋቅር ውስጥ የተፈጠረ ለውጥ ሁሉንም ነገር አበላሸው። በስቴቭሊ ምትክ አዲስ የስፖርቲንግ ዳይሬክተር ሆኖ የመጣው  ፖል ሚቼል የኢሳቅ የውል ማሻሻያ ጥያቄን ቆሻሻ ሳጥን ውስጥ ወርውሮታል። ገና የአራት ዓመታት ውል ለሚቀረው ተጫዋች ተጨማሪ የደሞዝ ወጪ ማውጣት አስፈላጊ እንዳልሆነ  አዲሱ አመራር መናገሩን መረጃዎች አመልክተዋል።

ይህ ውሳኔ ለኢሳቅ ትልቅ የክህደት መልዕክት ነበር። እናም ኢሳቅ ልክ እንደ ብሩኖ ጉማሬሽ ካሉ የክለቡ ቁልፍ ተጫዋቾች እኩል ከፍተኛ ተከፋይ አለመሆኑ ልቡ እንዲሸፍት አድርጎታል። ኢሳቅ በሴንት ጀምስ ፓርክ በሳምንት 120 ሺህ ፓውንድ ደሞዝ ነበር የሚያገኘው።

ይህ ደሞዝ በእሱ ደረጃ ላይ ካሉ የፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ አጥቂዎች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ እንደሆነ የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል። እናም ለዚህ ነው ግብ አነፍናፊው “ቃል የተገባልኝን ተክጃለሁ” ያለው፡፡ ይህ ደግሞ ትልቁ መፍትሄ ክለቡን መልቀቅ ነው ብሎ እንዲያምን አድርጎታል።

የክረምቱ የዝውውር ወቅት ሊዘጋ የሰዓታት እድሜ ብቻ ይቀሩታል፡፡ባለቀ ሰዓት ግን ዝውውሩ ዕውን ሆኗል፡፡ኢሳቅ በአንፊልድ ስድስት ዓመታት የሚያቆየውን ውል ፈርሟል።

ሊቨርፑልም አጥቂውን ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ነገር ግን ኒውካስትል የለጠፈው ከፍተኛ የዝውውር ዋጋ አዘግይቶት እንደነበር አይዘነጋም።

የሊቨርፑል ዝውውር ባይሳካ ኖሮ ኢሳቅ በውሉ መሰረት በኒውካስል የመቆየት ግዴታ ነበረበት። ይህ ከሆነ ደግሞ ግንኙነቱ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ተጫዋቹ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ባለመስራቱ  በደጋፊዎች ዘንድ የነበረው ተወዳጅነት እና ተቀባይነት በእጅጉ ቀንሶ ነበር። ያሰበው  ባይሳካ ኖሮ በሴንት ጀምስ ፓርክ እንደበፊቱ  ደስተኛ እና ስኬታማ  ላይሆን ነበር፤ አሁን ግን ዝውውሩ መሳካቱ ከብዙ ምስቅልቅል ድኗል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here