ተወዶ የተዘነጋዉ ስፖርት

0
162

ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

በአማራ ክልል በሁሉም ቦታዎች እኩል ከሚወደዱ ስፖርቶች መካከል የቮሊቦል ስፖርት አንዱ ነው። ከገጠር እስከ ከተማ በስፋት ይዘወተራል። በትምህት ቤቶች እና በመኖሪያ አካባቢዎች ሳይቀር የሚዘወተር ስፖርት ነው የቮሊቦል ስፖርት። ስፖርቱ አነስተኛ በጀት እና ትንሽ የማዘውተሪያ ሥፍራ የሚጠይቅ በመሆኑ  በክልሉ ማኅበረሰብ ዘንድ እንዲወደድ አድርጎታል።

እኔም ለሥራ በተለያዩ የአማራ ክልል ቦታዎች በተዘዋወርኩበት ወቅት በከተማ እና በገጠር ቀበሌዎች በርካታ የጤና የቮሊቦል ቡድኖችን በስፋት መመልከቴን አስታወሳለሁ። ልክ እንደ አትሌቲክስ እና ሌሎችም ስፖርቶች ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ ቢሠራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አቅም ያለባቸውን ቦታዎች ዐይቶ መናገር ይቻላል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ  በአማራ ክልል የቮሊቦል ስፖርት በእጅጉ መዳከሙን ብዙዎች የሚስማሙበት ሀቅ ነው። በአማራ ክልል በርካታ የቮሊቦል ክለቦች እና ቡድኖች ባለመኖራቸው ስፖርቱ በተደራጀ መልኩ እንዳይቀጥል አድርጓል።

አማራ ክልልን ወክሎ በኢትዮጵያ ደርባ ሜድሮክ  ስሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፍ ክለብ አንድ ብቻ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ክለብ የባሕር ዳር ከተማው “ጣና ባሕር ዳር” ነው።

በክልሉ ተጨማሪ ተፎካካሪ ክለብ ባለመኖሩ እና እርሱን የሚመግቡ የታዳጊ ፕሮጀክቶች ባለመኖራቸው መሻሻል ሳያሳይ ዓመታት እየነጎዱ ነው፡፡በሴቶች ቮሊቦልም በክልሉ ትልቅ አቅም እንዳለ ቢታወቅም በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፍ   አንድም ክለብ ግን የለም።

ይህም በዘርፉ ክልሉ እየሠራ አለመሆኑን ያመለክታል። በቀደሙት ጊዜያት በአማራ ክልል የቮሊቦል ስፖርት ጠንካራ ክለቦች እንደነበሩ እና  ውድድሮችም ሳይቆራረጡ ይደረጉ እንደ ነበር ከአሚኮ ስፖርት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረገው የቀድሞው ተጫዋች አቶ ሰፊ ገበየሁ ይናገራል።

በተለይ ደግሞ ከ1970ዎች ጀምሮ እስከ 1990ዎች ድረስ የቮሊቦል ስፖርት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት እንደ ነበር ያስረዳል። በወቅቱ ጨዋታዎች በፍላጎት እና በፍቅር ብቻ መደረጋቸው ቮሊቦል በደንብ ሊስፋፋ እንደቻለ የቀድሞው ተጫዋች ያስታውሳል።

አሁን ላይ ምንም እንኳ እንደ ሌሎች ስፖርቶች ብዙ ገንዘብ ፈሰስ ባይደረግበትም ከቀደሙት ጊዜያት አንፃር ግን የቮሊቦል ስፖርት አነሰም በዛም ገንዘብ ተበጅቶለት ቢሠራም በተፈለገው ልክ ግን አላደገም። ቋሚ የሆነ የውድድር ስርዓት አለመኖር፣ በክልሉ በርካታ የቮሊቦል ክለቦች እና ቡድኖች አለመኖራቸው እና የታዳጊ ፕሮጀክቶች በስፋት አለመከፈታቸው በዘርፉ ተተኪዎች እንዳይወጡ እና ስፖርቱ እንዲደከም ምክንያት እንደሆነ የቀድሞው ተጫዋች ያብራራል።

ለቮሊቦል ስፖርት የሚበጀተው ገንዘብ አነስተኛ መሆን፣ ከቀድሞ ተጫዋቾች፣ ባለሙያዎች እና ዳኞች ጋር በቅርበት አለመሥራታቸው ስፖርቱ እንዲቀዛቀዝ መንሰኤ ሆኗል ይላሉ አቶ ሰፊ ገበየሁ። ዘርፉ በባለሙያ አለመመራቱም ለመዳከሙ አንደኛው ምክንያት ነው ተብሏል። በተጨማሪም የስፖርት ቁሳቁስ ችግርም ዘርፉ አደጋ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የጤና እና የሠውነት ማጎልመሻ መምህራን በትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ማድረግ ይገባል ባይ ናቸው የቀድሞ ተጫዋቹ። የአማራ ክልል ቮሊቦል ስፖርት ወደ ቀደመ ስሙ እንዲመለስ ፕሮጀክቶች ላይ ይበልጥ መሥራት እና ባለሙያዎችን በብዛት ማፍራት ለነገ የማይባል ተግባር ነው።

እንደ አማራ ቮሊቦል ሊግ ዓይነት ቋሚ የውድድር ስርዓት መዘርጋት ስፖርቱን ለማነቃቃት ያግዛል። ከዚህ በፊት በነበሩ ጊዜያት የነበረውን የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር በማስጀመር እና ከትምህርት ቤቶች ጋር በቅርበት መሥራት ለቮሊቦል ስፖርት እድገት ወሳኝ መሆኑን የቀድሞ ተጫዋቹ አቶ ሰፊ ገበየሁ ተናግሯል።

የንግድ ተቋማት እና ሌሎች ድርጅቶች የቮሊቦል ክለቦችን እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል። በአማራ ክልል ተጨማሪ ክለቦችን በማቋቋም  ከፕሮጀክት እና ከታዳጊ ማሰልጠኛ የሚወጡ የቮሊቦል ስፖርተኞችን ከክለቦች ጋር ማገናኘትም ሌላኛው መሠራት ያለበት ተግባር ነው።

በክልሉ የሴቶች የቮሊቦል ስፖርት አሁን ላይ የለም በሚባል ደረጃ ተቀዛቅዟል። የተዳከመውን የሴቶችን የቮሊቦል ስፖርት ለማነቃቃት የሚመለከታቸው አካላት ከወሬ ባለፈ መሬት ላይ የሚወርድ ሥራ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው አቶ ሰፊ ይናገራሉ።

ፌዴሬሽኑ  ሀብት በማሰባሰብ በቂ በጀት መመደብ ከቻለ ስፖርቱን መለወጥ ይቻላል፤ የቀድሞ ስፖርተኛው ሀሳብ ነው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ከፌዴሬሽኑ እና ከማስልጠኛ ጣቢያዎች ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

ምንም እንኳ የቮሊቦል ስፖርት አነስተኛ የማዘውተሪያ ስፍራ ቢጠይቅም የቀድሞ የቮሊቦል ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሳይቀሩ ለሌላ አላማ በመዋላቸው ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል። ይህም መፍትሄ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ተሰጥቶታል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ ሜድሮክ ሲሚንቶ ወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በባሕር ዳር ከተማ ሲደረግ እንደነበረ አይዘነጋም። ታዲያ በክልሉ መዲና በሚደረግበት ወቅት በተደጋጋሚ ጨዋታዎችን የመመልከት ዕድሉን አግኝቼ የነበረ ሲሆን አሰልጣኞችን እና ተጫዋቾችንም ለማነጋገር ሞክሬ ነበር። እኔም ለመታዘብ እንደ ሞከርኩት ተተኪዎች እና አዳዲስ ፊቶች እየታዩ አለመሆኑን አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች አረጋግጠውልኛል።

የመተካካቱ ሂደት ደካማ በመሆኑ ታዳጊዎች ህልም እንዳይኖራቸው እና ነገን አስበው በቁርጠኘነት እንዳይተጉ አድርጓቸዋል።

የአማራ ክልል ቮሊቦል ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ በላይ አበጀ ስፖርቱን ለማነቃቃት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአማራ ክልል ቮሊቦል ሊግ መጀመሩን ገልጸው ስፖርቱ መዳከሙን ግን አልሸሸጉም። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ክልል ቮሊቦል ፌዴሬሽን በክልሉ የቮሊቦል ስፖርት የቀደመ ስም እና ዝናውን ለመመለስ ለረጅም ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የአማራ የቮሊቦል ሊግ አስጀምሯል። በዚህ መድረክም ከ17 ክለቦች በላይ መሳተፋቸው የሚታወስ ነው።

ፌዴሬሽኑ በሁሉም የአማራ ክልል ቦታዎች አቅም እንዳለ ቢረዳም እስካሁን ግን በተገቢው ልክ አለመሥራቱን ያምናል። የስልጠና ቦታዎችን በመለየት እና በማጠናከር አሰልጣኞችን በማብቃት እና ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ መሥራት የሚታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን የጽ/ ቤት ኅላፊው ተናግረዋል። በክልሉ አንድ አንድ ዞኖች በምዕራብ ጎጃም እና ደቡብ ወሎ በመሳሰሉት ዞኖች የቮሊቦል የስልጠና ጣቢያዎች እንዳሉ ቢታወቅም በፌዴሬሽኑ አነስተኛ ድጋፍ እና ክትትል በሥራ ላይ አለመሆናቸው ተረጋግጧል። በቀጣይ ግን ፌዴሬሽኑ የተሻለ ሥራ እንደሚሠራ አቶ በላይ አበጀ ነግረውናል። በአማራ ክልል የቮሊቦል ክለቦች ወይም ቡድኖች ሲመሰረቱ ሴቶችንም ታሳቢ ተደረጎ አለመሠራቱ የሴት የቮሊቦል ክለቦች አለመኖራቸውን ያረጋግጣል። ታዲያ ይህን ችግር ለመቅረፍ የወንዶች ቮሊቦል ክለብ ሲቋቋም የሴቶችንም አብረው እንዲይዙ አስገዳጅ ሕግ እናስቀምጣለን ብለዋል የጽ/ቤት  ኅላፊው።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here