“ተግባራችን ውጤቱ ያማረ የሚሆነው በመልካም ሥነ-ምግባር ላይ ተመርኩዞ ከተሠራ ብቻ ነው”

0
127

ሊቀ መምህራን አዲስ  ጤናው የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ እና ኮኩሐ ሃይማኖት የትምህርት አበ ነፍስ እና የስብከት ዘዴ መምህር ናቸው፡፡ የሕይወት ተሞክሯቸውን፣ በሕይወታችን ወሳኝ በሆነው ሥነ ምግባር እና የሥነ ምግባር ጉድለቶች ያስከተሏቸውቸው ችግሮች እንዲሁም ከችግሩ መውጫ መፍትሔዎች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ፡፡

የልጅነት ጊዜዎት ምን ይመስላል? ወደ አብነት ትምህርት ቤትስ እንዴት ገቡ?

የተወለድኩት በ1960 ዓ.ም በምሥራቅ ጎጃም ጅላን ሚካኤል በሚባል ቦታ ነው፡፡ እናት እና አባቴ የመጀመሪያ ባል እና ሚስት ናቸው፡፡ ሰባተኛ ልጃቸውን እንደወለዱ እናቴ በድንገት አረፈች፡፡ አባቴ ለዓመት ያክል ጎረቤት እያስቸገረ እያስጋገረ እና ወጥ እያሠራ ሰባት ልጆቹን ለማሳደግ ሞከረ፡፡ ከዚያ በኋላ ዘመድ እና ጎረቤት አይሆንም ብለው ሌላ ሴት አጭተው አጋቡት፡፡ የእንጀራ እናታችን ትልቅ ተጽዕኖ ታደርስብን ነበር፡፡ አባታችን ልጆቹን በጣም ይወዳል፤ እሱ ሲመጣ ምንም አትናገረንም፤ ሲወጣ ግን ትጨቁነናለች፡፡ በዚህ የተነሳ የስጋ እናቴን ኩታ ለብሼ የቄስ ትምህርት ገባሁ፤ በየቤቱ እየዞርኩም እለምናለሁ፡፡ በዓመቴ ዳዊት ደገምኩ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር እየተረዳዳሁ ትምህርቱን ቀጠልኩ፡፡

ከዚያስ?

ጾመ ድጓን ግማሽ በላይ እንዳደረስነው ጓደኞቼ ወደ ቅኔ ትምህርት ቤት እንሂድ አሉኝ፡፡ ተስማምቼ ቀኝ አቦ የቅኔ ትምህርት ቤት ገባን፡፡ እዚያ ስንገባ ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር፡፡ የቅኔ ቤቱ አለቃ “እነዚህን ምስኪን የገበሬ ልጆች ልታስፈጇቸው ነው ያመጣችኋቸው?” ብለው ተቆጡ፡፡ ራሳቸው ፈልገው ነው የመጡት ተብሎ ተነገራቸው፤ ከሸዋ ለመጣ አንድ ጎበዝ ተማሪ እንዲያስተምረን ሰጡን፡፡

አዲሱ መምህራችን የሚረጨውን እየረጨ የሚደገመውን እየደገመ በወረርሽኙ ሳንጠቃ ተረፍን፡፡ እሱ በሌለ ጊዜ በሚያሳየኝ መሠረት እኔ የሚረጨውን እረጫለሁ የሚደገመውን እደግማለሁ፡፡ ተማሪው ሁሉ ወቀድቆ እኛ ብቻ ብንድን ምን ትርጉም አለው? ብየ እሱ በሌለበት ትምህርት ቤቱን ሁሉ ረጨሁት በሙሉ የታመመው ዳነ፤ በሽታው ጠፋ፡፡ በሳይንሱ እንዳለው የተስቦ መድሃኒት ነበር የሚረጨው፡፡ መድሃኒቱ የሚጠጣም የሚረጭም ነው፤ ይሄን በኋላ በራሴ ተመራምሬ ያገኘሁት ነው፡፡

ከዛ ሸዋ ሰው ጋር እሱ አስተማሪ ሆኖ እያስቀጸለ፣ እኛ ለምነን እያበላነው መኖር ቀጠልን፡፡ እሱም ልመና አይሄድም፤ እኛም በጥበቡ እንፈራው ነበር፡፡ አንድ ለእኛ ከጠጣን ለእሱ አንድ እንይዛለን፤ ከተሰጠን መብል ግማሹን እናመጣለታለን፡፡ እንደ አባት እየተንከባከብነው ቆየን፡፡ በኋላ በቅጸላው እኛ እየጎለበትን መጣን፡፡ በድብቅ ከሌላ አስነጋሪ እና አስዘራፊ እንሄዳለን፡፡ እሱ ሲመጣ እንዳንበላ (እንዳያውቅብን) ከእሱ ጋር እንቀጽላለን፡፡ ሲያቅተው እኛን መጠየቅ ጀመረ፤ አያ እገሌ እንዲህ ነው የፈታው እያልን አስመስለን እንነግረዋለን፡፡ በለጥነው ማለት ነው፡፡

በዓመታችን በሚካኤል ዋዜማ ተቀኘን፤ ጣና ሞገዱ ለእኔ ተሰጠኝ፤ ቀጥሎ ወደ ዲማ ጊዮርጊስ ሄድን፤ አገባቡን ስንቀጽል ቆየን እና ወደ አቋቋም ትምህርት ልንቀጥል ስንል አንድ አባት “አንተ አምሮህ ብሩህ ነው፤ መጽሐፍ ነው መቀጠል ያለብህ” አሉኝ፡፡ ተመርቄ ልሄድ የነበረው መጽሐፍ ቤት ገባሁ፡፡

ቀን እና ማታ በኩራዝ ሳይቀር እያነበብኩ ጓደኞቼን አለፍኳቸው (በለጥኳቸው)፡፡ እነሱ ቀን ቀን ብቻ በጉባኤው ይማራሉ፡፡ ስበልጣቸው ጊዜ ተጣሉኝ፡፡ ቤተሰቦቼንም ማጣራት ጀመሩ፤ እኔ ከቤቴ መርሬ ነው የወጣሁት፤ አምስት ዓመት ሙሉ ቤተሰቦቼን አልጠየኳቸውም፡፡ ሀሳቤን አንድ አድርጌ ነበር የምማረው፡፡ ውጤታማ የሆንኩትም ለዚህ ነው፡፡ በእናቴ ወገን በእግራቸው የሚጽፉ ምሁራን ናቸው አልኳቸው፡፡ የተወሰነ ተጋጨን፤ ከዱላም ደረስን፡፡ እንዴት መጽሐፍ እየተማርኩ እደባደባለሁ ብየ አዘንኩ፤ ከመምህሬ ፊት ወድቄ አለቀስኩ፡፡ አስታርቁን ብየም ታረቅኩ፡፡ ተመርቀንም ወጣን፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከትን የሚያስተዳድሩት አቡነ መቃርዮስ ወደ ማርቆስ ለስብሰባ መጡ፡፡ እሳቸው ባሉበት ሦስት ሙሉ ቤት አበረከትኩኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ከየት ነው የመጣኸው? አሉኝ፤ ከዲማ አልኳቸው፤ የአለቃ ማርቆስ ተማሪ ነህ? አሉኝ፤ አዎ አልኳቸው፤ ምን ምን ታውቃለህ? አሉኝ፤ የመጽሐፍ እና ቅኔ መምህር ነኝ አልኳቸው፡፡ “በሕር ዳር ማሰልጠኛ ስላለ እዛ ና” አሉኝ እና 10 ብር ሰጡኝ፡፡ በስምንቷ ብር ባሕር ዳር ተጓጉዤ ደረስኩባት፡፡ በሁለቷ ብር ምሳየን በላሁባት፡፡

ለስልጠና ተቋሙ መምህር መጥቷል ተቀበሉት ተብሎ ተደውሎላቸዋል፡፡ ነገር ግን ልጅ እግር ስለነበርኩ የቆሎ ተማሪ እየመሰልኳቸው እያለፉኝ ይሄዳሉ፡፡ ጠጋ ብየ አቡነ መቃሪዮስ ወደ እዚህ እንደመጣ ነግረውኝ ነበር እኔ የቅኔ መምህር ነኝ አልኳቸው፡፡  ደነገጡ! በወቅቱ 17 ወይም 18 ዓመቴ ነበር፡፡ ቤት ተነጥፎ ምግብ ተዘጋጅቶ ጠበቁኝ፡፡

ስልጠናው ምን ምንን ያካተተ ነበር?

ስልጠናው አምስት ወር የሚሸፍን ነው፡፡ በውስጡም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ዶግማ፣ ትምህርተ አበ ነብስ፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ግዕዝ፣ ስነምግባር፣ ቅርሳ ቅርስ፣ የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ፣ ቅኔ እና ሌሎች 11 ትምህርቶች አሉት፡፡ በደንብ ሥርዓተ ትምህርት የተቀረጸለት ነው፡፡ ቀን ቀን እያስተማርኩ ማታ ማታ ስልጠና እከታተላለሁ፡፡ ስመረቅ መደበኛ መምህር ሆኜ ተመደብኩ፡፡

ዘመናዊ ትምህርትም ተከታትለዋል፤ እንዴት እንደገቡ እና የደረሱበትን ደረጃ ቢነግሩን?

ወደ ባሕር ዳር ከተማ የመጣሁት  በ1978 ዓ.ም ነው፡፡ ሦስት ዓመት በማሠልጠኛ ተቋሙ ካገለገልኩ በኋላ ዘመናዊ ትምህርት መማር ጥልቅ ፍላጎት ስለነበረኝ ዐፄ ሠርጸ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ የተማሪዎችን ደብተር በደንብ አነበብኩ፤ ወዲያው ወደ ሦስተኛ ክፍል እንድገባ ተደረገ፡፡ ቀጥሎም በደንብ እንብቤ በዛው ዓመት ወደ አራተኛ ክፍል ተሸጋገርኩ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት አምስት እና ስድስተኛ ክፍሎችን በእጥፍ አለፍኩ፡፡ ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍሎችንም እንዲሁ በእጥፍ አለፍኩ፡፡ በሦስት ዓመት ዘጠነኛ ክፍል ደርስኩ፡፡ ከዘጠኝ በኋላ በእጥፍ ማለፍ የለም ተባለ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ከተማሪው በላይ ነበር ውጤት የማመጣው፡፡ አስረኛ ክፍል እንዳጠናቀቅኩ ኮሎጅ ገብቼ በሂሳብ አያያዝ ዲግሪ ይዣለሁ፡፡ በነገረ መለኮት አራት ዓመት ዲግሪ እና ማስተርስ ዲግሪ አለኝ፡፡

ከሚያስተምሯቸው ትምህርቶች አንዱ ሥነ ምግባር ነው፤ ሥነ-ምግባር ምንድን ነው?

ሥነ-ምግባር ማለት የሁለት ቃላት ጥምር ውጤት ነው፡፡ “ሥነ” የሚለው ቃል “ሠነየ” ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ሲሆን፤ ያማረ፣ መልካም የሆነ፣ ደስ የሚያሰኝ፣ በለጠ፣ ተሻለ ማለት ነው፡፡ ምግባር የሚለው ደግሞ “ገብረ” ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሥራ፣ ፈጠራ፣ ድርጊት፣ ክንውን ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሥነ-ምግባር ማለት መልካም፣ የተገነባ፣ የተፈቀደ፣ የተወደደ፣ ያማረ ሥራ ወይም ድርጊትን የሚያጠና የፍልስፍና ዘርፍ ሲሆን አንድን ነገር ትክክል ነው ወይም አይደለም ብለን እንድንጠራ የሚያደርገን እሴት ነው፡፡ በእንደዚህ መልኩ ጠለቅ ብሎ የተነተነው ሥነ-ምግባርም በህይወታችን ዋጋ ልንሰጣቸው ከሚገቡን ነገሮች አንዱ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

እያንዳንዳችን የምንፈፅመው ተግባር ደግ ወይም መጥፎ መሆኑ የሚታወቀው በውጤቱ ነው፡፡ ውጤቱም ያማረ እና የተዋበ የሚሆነው በመልካም ሥነ-ምግባር ላይ ተመርኩዞ ከተሠራ ብቻ ነው፡፡ ይሄንን ውጤቱ ያማረ ተግባር ለመፈፀም ደግሞ መልካም የሆነ ሥነ-ምግባር ያስፈልጋል፡፡

ሆኖም ሁሉም ዜጋ ለሚሰራው ስራ የስነ-ምግባር መርሆችንና እሴቶችን በመከተል ሀገራዊ፣ ቤተሰባዊና ግላዊ ግዴታዎቹን በመልካም ሥነ-ምግባር ለሀገር ልማትና ዕድገት አስተዋፆውን ማበርከት ይገባል፡፡ ይሄንን ውጤቱ ያማረ ተግባር ለመፈፀም ደግሞ መልካም የሆነ ሥነ-ምግባር ያስፈልጋል፡፡

እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

ይቀጥላል

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here