ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ የሚቀርቡ ዘፈኖች ውስጥ ጀግንነት፣ ውበት፣ ቁንጅና፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ጥበብ፣ ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ አብሮነት፣ መቻቻል፣ አመጋገብ፣ ስነ ጥበብ፣ ኪነ ሕንጻ፣ ቋንቋ፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ አነጋገር፣ ኀዘን እና ደስታ በመልእክትነት ሲተላለፉ ቀጥለዋል::
በኤፍሬም ታምሩ “ኧረ ነይ’ማ” ዘፈን ውስጥ የፍቅር ስሜት ብንመለከትም እንኳን ገጸ ባህሪው የወደዳትን ልጅ፤ ወክላ የቀረበችው ሴት የማህበረሰቡን የወል መረዳት እና አመለካከት እንድንገነዘብ ትረዳናለች:: ርግጥ ነው ሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ ጀግንነት፣ ደግነት፣ ባህል፣ ታሪክ እና ጥበብ መኖሩ ሳይካድ አንዱ ከሌላው የሚለይበትን ነገር ለማሳየት ይሞከራል::
“አገሩን ዳር ከዳር አርሰነዋል ሲሉ
አንቺን አበቀለ ከተዘራው ሁሉ
ሽወዬ ነሽ ሲሉኝ ተከተልሁ እግርሽን
ሐረርጌ ነሽ ሲሉኝ ተከተልኩ ውበትሽን
ወሎዬ ነሽ ሲሉኝ ወደድሁት ፍቅርሽን
ጎንደሬነሽ ሲሉኝ አሰርሁት ማተብሽን
ጎጃሜ ነሽ ሲሉኝ ፈራሁት ፍቅርሽን::
በወሎ በጎጃም እንዲያ ስበረታ
ሸዋን አልፎ ልቤ ጎጃም ላይ ተረታ”
ኤፍሬም በግጥሙ ውስጥ የሚነግረን በጎንደር፣ በወሎ፣ በሸዋ፣ እና በጎጃም ማህበረሰቦች ውስጥ ማህበረሰቡ የሚስማማባቸውን የወል ማንነቶች በማጉላት ነው:: ጎንደር በታማኝነት፣ ወሎ በፍቅሩ፣ ሸዋን …፣ ጎጃም ደግሞ በቀላሉ ማግኘት አለመቻሉ::
የሴቷን ልብ ለማግኘት ደጅ መጽናት እንዳለበት አውቆ “ፈራሁት ፍቅርሽን” ሲል እንሰማዋለን::
ሙዚቃዎች ዘመንን ተከትለው እንደሚጓዙ ማሳያው ሙዚቃዎችን ማድመጥ ነው:: በደርግ ዘመን ሀገሬ የሚሉ በርካታ መዝሙር መሳይ ዘፈኖች ተሠርተዋል:: ይህ የመንግሥት አቅጣጫ እና ፖለቲካዊ ጉዞን መከተል በኢህአዴግ ዘመንም ተስተውሏል:: ደርግ የገነባው መስመር በኢህአዴግ ዘመን ተለውጧል:: ደርግ ሀገራዊ አንድነትን ማምጣት የሚቻለው የጋራ መብቶችን በማክበር ነው ይል ነበር::
እድገት የጋራ መብቶች መከበር ላይ ነው ብሎ ያምናል:: ሁሉንም ሕዝብ በአንዲት ኢትዮጵያ ስም እንዲጠራ ይፈልግ ነበር:: ኢህአዴግ ደግሞ የግለሰቦች መብት መከበር አለበት ብሎ ያምናል:: ከኢትዮጵያ ይልቅ ብሔሮች ገዝፈው ታይተዋል:: አሁንም በሀገር ፋንታ ብሔር ከፍ ከፍ ሲል እናያለን:: በዚህም ብሔር ብሔረሰቦች የበለጠ እውቅና ያገኙ ጀመር:: ብዙዎች ከሀገር ወርደው ብሔረሰብ ዘፈን ውስጥ ገብተው ተስተውለዋል:: በተለይ በቅርቡ የሚሠሩ ዘፈኖች ደግሞ ወደ ጥላቻ የሚያመሩ መሆን ጀምረዋል:: አንዱ ብሔር ሌላውን የሚበልጥበትን ፍለጋ እና ፉክክር ይስተዋላል ሙዚቃዎች ውስጥ::
የደርግን ዘመን የሚያስታውሱን ጥላሁን ገሰሰ እና ብዙነሽ በቀለን “በሀገር ጉብኝት” በሚለው ዘፈናቸው ምን እንዳሉ እንመልከት:: ሁለቱ አንጋፋ ድምጻዊያን ጉዞ ይጀምራሉ:: ተወዳጅ ቦታዎችን ለማስተዋወቅ የተዘፈነ ይመስላል:: ወለጋ ሄደው የወርቅ ሀብትን ይጎበኛሉ:: ለጌጥ የሚሆንም እንግዛ ይላሉ:: በዚያውም በኢሉባቦር አልፈው ከፋን ይቃኛሉ:: አሁንም ከአዲስ አበባ ይነሱና በሸዋ በኩል ዘልቀው ወሎን ይጎበኛሉ:: በወሎ ቆይታቸውም የላሊበላ ገዳምን ይጎበኛሉ:: ጉዞው ወደ አፋር ቀጥሎ ገዋኔን አይተው ወደ አዋሽ ያቀናሉ:: አዋሽ እንደደረሱም በባቡር ተሳፍረው ሐረር ገብተው ያድራሉ:: በሐረር ቆይታቸውም የጀጎል ግንብን እና ሕዝቡን ይጎበኛሉ:: አብረው መጓዛቸው ፍቅር እና አንድነታቸውን እንደሚያጠናክረው በማመን ጉብኝታቸውን ይቀጥላሉ:: ወደ ባሌ ተጉዘው ሶፍ ኡመር ዋሻን ከተመለከቱ በኋላ ወደ ሲዳማ ተጉዘው ጋሞንም ይቃኛሉ:: አርሲን ጎብኝተው ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ::
ጉብኝቱ እንደቀጠለ ነው:: በአውሮፕላን ተሳፍረው ወደ አስመራ ያቀናሉ:: አስመራ አምሽተው አሰብ እና ምጽዋ ወደቦችን ይጎበኛሉ:: በመርከብ ተሳፍረው በቀይ ባህር ሽርሽር ያደርጋሉ:: ዳህላክ ደሴትንም እረፍት ያደርጉባታል:: ወደ ትግራይ ተጉዘው መቀሌን ይዝናኑባታል:: ወደ ጎንደር ይጓዛሉ፤ ፋሲል ግንብን ይጎበኙና ወደ ሰሜን ተራራዎች አቅንተው ብርቅዬዎችን ዋልያዎች ይጎበኛሉ:: ወደ ጎጃም ይመጡና ደግሞ ማር እና ጤፉን አይተው ይደነቃሉ:: በባህርዳር ቆይታቸው ዓባይ እና ጣናን ይጎበኛሉ::
የጉዟቸው መጨረሻም ሸገር አዲስ አበባ ያበቃል:: ሁለቱም ዘፋኞች በወቅቱ ኢትዮጵያ የነበሯትን ጸጋዎች ለማስተዋወቅ ሞክረዋል:: በሙዚቃው የተጠቀሱት አካባቢዎች ዛሬም ድረስ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው:: አሰብ፣ ምጽዋ፣ ዳህላክ፣ አስመራ እና ቀይ ባህር ዛሬ የኤርትራ ይዞታዎች ሆነዋል:: አንዳንዶቹ ደግሞ የስም ለውጥ አድርገዋል:: ሙዚቃዎች እንዴት የታሪክ ማስረጃዎች እንደሆኑ ከዚሁ መመልከት ይቻላል::
በህላዊ ሙዚቃዎች ብዙ ይዘቶችን ይዘው ቢቀርቡም ቦታዎችን እና አካባቢዎችን በማስተዋወቅ በኩል ትልቅ ሚና እንዳላቸው አድማጭ ተመልካች ይገነዘበዋል:: ባህላዊም ይሁኑ ዘመናዊ ዘፈኖች በብዛት ትኩረት የሚያደርጉበት ጉዳይ ፍቅር ነው:: ሀገረሰባዊው ዘፈን አካባቢውን በመጥራት፣ የሀገሬ ፣ የመንደሬ፣ የንጉሥ ልጅ፣ የጀግኖች፣ የደጋጎች፣የጠቢባን ልጅ፣ የአርበኞች ልጅ እና መሰል የጋራ እውነታዎች ላይ በመመስረት የአካባቢውን ስም ይነግሩናል:: የወደዷ/ዳትን ልጅ ከሚታወቅ አካባቢ መገኘቷ ለፍቅር ምርጫ፣ ለመተጫጨት ትልቅ ቦታ አለው:: ማህበረሰቡም የማን ልጅ ናት፤ የት አካባቢ ናት፤ የእነ ማን ወገን ነው? በማለት በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት ያጠናል:: “እሱማ የእነ አያ እገሌ ወገን ነው:: የታወቁ ከበርቴ፣ ከሰው ጋር በፍቅር የሚኖሩ፣ የተጣላ የሚያስታርቁ፣ ደግሰው አገር የሚያበሉ፣ እንግዳ የሚቀበሉ” የሚሉ ሐሳቦችን የሚሰማ ሰው የተጠየቀውን ጋብቻ ይቀበላል:: በአንጻሩ ለጋብቻ የሚጠይቅ ሰው በማህበረሰቡ ዘንድ መልካም ስም ከሌለው፣ ማህበረሰቡ የሚሰጠው ደረጃ አናሳ ከሆነ “እንዴት ቢንቀኝ ነው ልጅህን ላግባት ያለኝ?” የሚል ቁጣን ይቀሰቅሳል:: ባህላዊ ሙዚቃዎች ይህንን ሀገረሰባዊ ትውፊት ይዘው ይዘፈናሉ:: በሀገረሰባዊ ሙዚቃ ውስጥ ማንነትን ማስተዋወቅ የተለመደ ነው:: ግጥሞችን መስማት ለዚህ አብነት ይሆናል:: በፍቅር ሙዚቃ ውስጥ ብዙ ማንነቶች ይተዋወቃሉ:: ቦታዎች እና አካባቢዎች በስፋት ይተዋወቃሉ::
አንዳንድ አካባቢዎችማ ቀበሌዎች ሁሉ በስም ተጠቅሰዋል:: ለዚያውም በተደጋጋሚ:: ለዚህ ደግሞ ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል:: ሰኞ ገበያ የትም ሀገር ፣ የትም አካባቢ ይውላል:: የደሴው ሰኞ ገበያ ግን በተደጋጋሚ ይገለጻል:: ብዙም ይታወቃል::
በሙዚቃዎች አማካይነት ብዙ ቦታዎችን በአካል ከምናውቃቸው በላይ ሰምተናቸዋል:: የሰቆጣውን ዋርካ በአካል ሄጄ አይቸዋለሁ:: በብዙ ሙዚቃዎች ውስጥ ሰምቸዋለሁ:: የጎንደሩን ጃንተከል ዋርካም አይቸዋለሁ:: የሶማ በረሃ ብዙ ሙዚቃዎች ውስጥ ተጠቅሷል::
ባህላዊ ዘፈኖች የማህበረሰቡን አመለካከት ይዘው ነው የሚነሱት:: ማህበረሰቡ ውስጥ እውቅና በነሲብ አይገኝም:: አንዳች መታወቂያ ያስፈልጋል:: “ለካንስ ዝም ብዬ አልወደድሁሽም የቴዎድሮስ ዘር ሆነሽ ነው፤ የበላይ ዘር ነሽና ነው:: የንጉሥ ሚካኤል ስለሆንሽ ነው እንጂ፤ የምኒልክ ልጅ ስለሆንሽ ነው:: የዋግሹሞች ሆነሽ ነው” የሚሉ ገለጻዎች ሙዚቃዎቻችን ውስጥ ተደጋግመው መምጣታቸው አንዳች የጋራ መታወቂያ፣ መሰባሰቢያ ዋርካ ጥላ መሳይ ጥግ የሚያስፈልግ በመሆኑ ነው:: “የበላይ ዘር ሆነሽ የዚያ የጀግናው፤ እንዳይሞት እንዳይድን ልቤን አረግሽው” በሚል መስፍን በቀለ ይዘፍናል::
በማህበረሰቡ ጥሩ ተግባር የሠሩ ሲወደሱ፣ ሲፈለጉ እናም ጀግኖች ሲባሉ እናያለን:: የጀግናን ልጅ ሁሉም ይፈልጋታል:: በቴዲ አፍሮ “ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ ሀገር፤ የአንዲት ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር” ሙዚቃ ውስጥ ከአጼ ቴዎድሮስ ታላቅ ኢትዮጵያዊ መንፈስ በመነሳት ሕዝብን ወደ አንድ ከፍታ የመምራት እሳቤን እናያለን:: የማጀገን፣ የማበረታታት እና አንድነትን የማጠንከር ሙከራ ባህላዊ ሙዚቃዎች ውስጥ አለ:: ሕዝቡ አንድ የጋራ ታሪክ ላይ ተመስርቶ በአንድነት እንዲቆም የማድረግ ኀይል አላቸው:: የአንድ ማህበረሰብ ደስታ እና ኀዘን የጋራ ነው:: ጀግንነቱም እንዲሁ::
በአንጻሩ ዘመናዊ ሙዚቃዎች ውስጥ የጎንደር ልጅ ሆነሽ ወደድሁሽ አይሉም:: ከጋራ ታሪክ እና ማንነት ይልቅ ስሜት ላይ ያተኩራሉ:: እንዳየሁሽ ልቤ ደነገጠ፣ በፍቅርሽ ተሸነፍሁ ነው የሚሉት:: “አይቼሽ ብጠጋ ፍቅር ያዘኝ ለምጄ” እንደሚለው ጥላሁን ገሠሠ:: ዘመናዊ ሙዚቃዎች አንድ ቤት ውስጥ እንዲት ልጅ ላይ ትኩረት አድርገው ስሜትን በመግለጽ ያልፋሉ:: ባህላዊ ሙዚቃዎች ሀገርን ጠቅሰው አዲትን ልጅ አንስተው፤ ብዙ ቦታዎችን ተንከራተው፤ አስጎብኝተው ያልቃሉ::
የቀደመውን የሀገረሰባዊ ሙዚቃ አሠራር የተከተሉ ዘመናዊ ሙዚቃዎችም አሉን ርግጥ ነው:: አክሊሉ ስዩም ሳልሰናበትሽ በሚለው ሙዚቃው ከአስመራ እስከ ደብረ ወርቅ ድረስ አንዲት ልጅ ጠፍታው ይዞራል:: ጸጋዬ እሸቱም እሄዳለሁ ሐረር በሚለው ሙዚቃው ከአዲስ አበባ ለሥራ በሄደበት የተመለከታት ማሽላ ጠባቂ ጉብል ማርካው ይብሰለሰላል::ነዋይ ደበበም እንዲሁ ጅማ በሄደበት ከአንዲት ጉብል ፍቅር ይዞታል:: ቴዲ አፍሮም ቢሆን ባሮ ወንዝ አሳ በምታጠምድ የጋምቤላ ቆንጆ ልጅ ፍቅር ይዋትታል::
የወሎ አካባቢዎች
በባህላዊ ዘፈኖች ውስጥ የወሎ አካባቢዎች በስፋት ተጠቅሰው እንሰማለን:: የወሎ አካባቢዎች ከሰሜን እስከ ደቡብ በሙዚቃዎቹ ተስተጋብተዋል:: በውል የማናውቃቸውን ቀበሌዎች ሳይቀር በዘፈኖች አማካይነት ሰምተናል:: በርከት ያለ የአዝማሪ ቁጥር መኖሩ ምናልባት ለዚህ አግዞት ይሆን? ወሎ በባቲ፣ በአምባሰል፣ በአንቺ ሆዬ ቅኝቶች ምንጭነትም ትታወቃለች:: እንደልቤ ማንደፍሮ ዘወርዋራ በሚለው ሙዚቃዋ “አንገናኝም ወይ ውጫሌና የጁ፤ እንዴት ይለያያል ሸጋ ከወዳጁ” ስትል በወሎዬው ፍቅር ትባዝናለች::
በደረጀ ደገፋው ዘፈን ውስጥ ዋድላ እና ደላንታ፣ ወልዲያ፣ አምባሳል ተደጋግመው ተጠቅሰዋል:: እንዲሁ በመሰረት በለጠ ዘፈን ውስጥ ደሴ፣ ሐይቅ፣ ጎብዬ፣ ማርዬ፣ መርጦ፣ መርሳ፣ ውርጌሳ፣ ቆቦ፣ ሸድሆ፣ መቄት፣ ጦሳ ተራራ፣ ቦርከና ወንዞ፣ እንቻሮ፣ ኮምቦልቻ፣ ባቲ፣ ላስታ እና ሰቆጣ አካባቢዎች በፍቅር ዘፈን ውስጥ አጃቢ ሆነው ቀርበዋል:: ዱባለ መላክ ደግሞ ሮቢት፣ ዋጃ፣ ጥሙጋ፣ መሆኒ፣ ራያ፣ ይጠራል አላማጣ አካባቢዎችን እንሰማለን:: ሀብተ ሚካኤል ደምሴ ሂመኖ፣ ሳይንት፣ ተንታ፣ ቦረና፣ ጃማ፣ ወርኢሉ፣ ደረባ፣ የጁ አካባቢዎች ካላቸው ጸጋዎች ጋር ቀርበዋል:: በኑር አዲስ ሰይድ በኩል ደግሞ አላማጣ፣ ጨርጨር፣ ኮረም፣ ዶሮ ግብር፣ ውጫሌ ሙዚቃውን አድምቀዋል፤ ተዋውቀዋል:: ለማሳያነት አነሳሁ እንጂ ሌሎች የወሎ አካባቢዎችም በብዙ ዘፋኞች ስማቸው ተነስቶ ታውቀዋል:: የወሎ አካባቢዎችን ሙዚቃ ስናነሳ የካሳሁን ታዬ “ሶራ” ን መርሳት አይቻልም ላስታ እና አካባቢውን በስፋት ያስተዋወቀ ዘፈን ነው:: የቅዱስ ላሊበላ ገዳምን ታሪክ በሚገባ አሳይቷል::
ብዙዎች ላሊበላ የቀደምት አባቶች የኪነ ሕንጻ ጥበብ እንዴት እንደነበር በሚገርም ሁኔታ ከዚህ ዘፈን በኋላ አውቀዋል ብል ማጋነን አይሆንብኝም:: በዚሁ ወደ ሰቆጣ እና አካባቢው ሙዚቃዎች ስናመራ ድምጻዊ ታፈረ ሰለፈን እናገኛለን:: ከጋዝጊብላ እስከ ድሀና፣ ዝቋላ፣ አበርገሌ፣ ጻግብጂ፣ ሰቆጣ፣ አምደወርቅ፣ ሰሀላ፣ ተከዜ፣ወለህ፣ … ብዙ አካባቢዎችን በሙዚቃዎች ውስጥ እንሰማለን:: ሰቆጣ፣ ብርብር፣ መከንዝባ፣ ቀውዝባ፣ ጻታ እና ሌሎችንም አካባቢዎች በሙዚቃ እንድናውቃቸው ድምጻዊያን ዘፍነዋል::
“ሲቀላ እና ሊሞ ማዶ ለማዶ ነውና አይሸመገልም ፍቅር ባለጌ ነው” በሚል ዘፈን ሁለቱን ወንዞች እንድናውቅ ያደርጉናል:: “ሰቆጣ ጥሩ ነው ስጋ በልቶ ጠጅ፤ ትንሽ የሚያስፈራው አትንኩኝ ነው እንጂ” እየተባለም ይዘፈናል::
እንደ ጎንደር ጃንተከል ሁሉ ሰቆጣም ትልቅ ዋርካ አለው:: “ሰቆጣ ዋርካው ከጥላው አርፌ፤ ልቤን ትቼ መጣሁ ሳንባዬን ታቅፌ” በሚል ይዘፈናል:: የፍቅር አጋጣሚ አይድረስ ነው መቼም:: እዚህ ዋርካ ስር ሰዎች ለመገበያየት ይቀመጡበታል::
… ይቀጥላል
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም