ተጓዥ ሙዚቃዎች

0
196

ካለፈው ሳምንት የቀጠለ

ባለፈው ሳምንት ባስነበብነው የመጀመሪያ ክፍል፤ ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ በሙዚቃዎቻችን ሲተላለፉ የቆዩ መልዕክቶችን ከብዙው ጥቂቱን ጠቅሰናል። ከአካባቢዎች ጋር ያላቸውን ቁርኝትም እንዲሁ። ቀጣዩ እና የመጨረሻው ክፍልም እንደሚከተለው ቀርቧል።

የጎንደር አካባቢዎች

ጎንደር በርከት ያሉ አዝማሪዎች የፈለቁበት አካባቢ ነው። ቡርባክስን የመሰለ የአዝማሪ መንደር አለው። እብናትን እና ወረታን የመሰሉ የብዙ አዝማሪዎች መገኛም ነው። በመላው ጎንደር ከአለፋ ጣቁሳ  እስከ መተማ፤ ከወልቃይት እስከ አርማጭሆ፤ ከጋይንት እስከ ጃን አሞራ፤ ከአድርቃይ እስከ ወገራ፤ ከፎገራ እስከ በለሳ፤ ከደብረ ታቦር እስከ እብናት ድረስ በብዙ ድምጻዊያን አንደበት ተዘፍኗል። “መተማ ዮሐንስ ገንዳ ውሃ ማማሩ፤ እንኳንስ ሰዎቹ ፍቅር ያውቃል ሃገሩ” ስትል በአምሳል ምትኬ የምትቀኝለት ጎንደር ዙሪያውን የሚጠቃቀሱ ቦታዎች አሉት። ጎንደር አርማጭሆ፣ ደባርቅ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ወገራ፣ ጃናሞራ፣ ደብረታቦር፣ ጋይንት፣ ሊማልሞ፣ ጠለምት፣ በየዳ እና ሌሎችም በአምሳል ሙዚቃዎች ውስጥ ተጠቃቅሰዋል። ፋሲል ደሞዝም እንዲሁ የጎንደር አካባቢዎችን ያነሳሳል። ፋርጣ፣ ነፋስ መውጫ፣ አርባያ በለሳ፣ ደንቢያ፣ ፎገራ፣ ስማዳ፣ ዳባት፣ እስቴ፣ አሞራ ገደል፣ አፈርዋናት፣ አዲስ ዘመን፣ ወረታ፣ እብናት፣ እስቴ በሙዚቃዎች አማካይነት ተዋውቀዋል። ወርቁ ሞላም እንዲሁ ጭልጋ፣ ጉና፣ ሳንጃ፣ ማሰሮ፣ ትክል ድንጋይ፣ ዳንሻ፣ ሁመራ፣ አለፋ እና ቋራን በሙዚቃ አዋዝቶ አስተዋውቋል።

የጎጃም አካባቢዎች

“ወይ አልተቆጣሁት አልተናገርሁት

ልቤ ጎጃም ሲሄድ ሰላሌ ያዝሁት

ጎሀጽዮን ማዶ ደጀን ላይ ስደርስ

የሠራ አከላቴ ይለዋል ደስደስ” ብሎ ቻላቸው አሸናፊ በሚያዜምበት ዘፈን በርከት ያሉ የጎጃም አካባቢዎችን አስተዋውቋል። ደጀን፣ ዓባይ በረሃ፣ ሸበል በረንታ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሞጣ፣ ጎንቻ ፣ እነብሴ አካባቢዎች ተጠቅሰዋል። አሰፉ ደባልቄ ከመሸንቲ ትጀምራለች። ዳንግላ፣ እንጅባራ፣ፍኖተ ሰላም፣ ደንበጫ፣  ሉማሜ እና ደጀንን ትጠቃቅስና ወደ ቢቸና ትመለሳለች። እናም ደብረ ወርቅ፣  እናርጅ እናውጋ፣ ሀሙሲት፣ የጁቤ፣ በሞጣ አድርጋ አዴት ትደርሳለች። ከዚያም ወደ ባህርዳር ገብታ ዘጌን ትጎበኛለች። ጅጋ፣ቡሬ፣ እነማይ፣ ደባይ ጥላት፣ ፓዌ፣  ቻግኒ፣ ዘንገና፣ ግምጃ ቤት፣ ቲሊሊ፣ መተከል በይሁኔ በላይ እና አምሳል ምትኬ ዘፈኖች ውስጥ ተነስተዋል።

እንደልቤ ማንደፍሮን “ገዳዎ” በሚለው ሙዚቃዋ ጎጃም ጎንደር የሚሉ አካባቢዎችን ስትጠቅስ እንሰማለን። ሁለቱም አካባቢዎች ያሉ ቦታዎች ያላቸውን ጸጋ እና የህዝቦችን መስተጋብር እና አብሮነት በግጥሞቿ ታነሳለች።

“እስቲ ጎጃም ልሂድ ከደረሰ አዝመራው

እስቲ ጎንደር ልሂድ አብቦ ካፈራው

ከደረሰው እሸት ስንዴና ባቄላ

ለዓይኔ ያማረኝን ቆርጬ እንድበላ

ጎንደር እና ጎጃም እልፍኝ እና አዳራሽ

በዓለም በመከራ አንዱ ለአንዱ ደራሽ

ጎንደር አገሬ ነው ጎጃም ጎረቤት

መስሎ የሚታየኝ እናትና አባቴ”

እንደልቤ በሙዚቃዋ ከአዲስ አበባ ወደ ትውልድ አካባቢዋ ጎንደር እየተጓዘች ነው። ጎንደርን ደርሳ ለማየት ከፍተኛ ጉጉት አድሮባታል። ልቤ እንደፈረስ ጋለበብኝ ትላለች። ከደጀን ጀምራ እስከ ጎንደር አካባቢዎችን ስትጠራቸው መስመሩን በስዕል እንድናየው ታደርገናለች።

ደጀንን አልፌ ፣አልፌ ማርቆስ

ጉዞዬን ጀምሬ ዳንግላል ስደርስ

ሽምጥ ይጋልባል ልቤ እንደ ፈረስ

ከአባጃሌው ሀገር ጎንደር ለመድረስ።

የባህላዊ ሙዚቃዎች መገለጫ የሆነው አካባቢን ማስተዋወቅ “ከጎንደር ባህርዳር ስትመላለሱ፤ እስኪ ሁላችሁም ወረታን አስታውሱ” ብሎ ወረታ ከተማ የምትገኝበትን አማካይ  መገኛ ስፍራ ይነግረናል። ወረታ ከተማ በጎንደር እና ባህርዳር መካከል ላይ እንደምትገኝ ከሩቅ ሀገር ያለ ሰው ለማወቅ እድል ያገኛል። ባህርዳር ከተማ ያላትን የመዝናኛ አማራጭነት እንደልቤ እንዲህ በማለት ትገልጻለች “መንፈስን ለማደስ ፍቱን አብነት፤ ውቢቱ ባህርዳር የጣና ገነት”። በእንደልቤ ጉዞ ውስጥ ሀሙሲት፣ እብናት፣ አዘዞ ፣ ስማዳ፣ ደብረ ታቦር፣ አዲስ ዘመን አካባቢዎችን ትጠቃቅሳለች።

“ልሂድ ደብረታቦር አዘዞ ስማዳ

ፍየል በጉ ታርዶ ተጥሎ ፍሪዳ

ወተት ማሩ ቅቤውን ከማጀት ሲቀዳ

ዐይቸው ልመለስ የእማምዬን ጓዳ”

 

የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች

“ተጉለት እና ቡልጋ ኩታ ገጡሙን

ሸነሸኑት አሉ  ሊያውሉት ጾሙን

ያርሳል በማረሻ ይተኩሳል በአልቤን

አልዩአምባ ሄጄ አስረከብሁት ልቤን” በሚል ማናልሞሽ ዲቦ የሸዋ አካባቢዎችን በሙዚቃ ስራዋ ታነሳሳለች። ማናልሞሽ ከቡልጋ ጀምራ ተጉለት፣ ምንጃር፣ አንኮበር፣ መንዝ፣ ሸንኮራ፣ይፋት፣ መሬ፣ ጀማ፣ ደራ፣ ሚዳ፣ መራኛ፣ ሞፈር ውሃ፣ ጅረት፣ ሰላሌ፣ እንሳሮ፣ ማጀቴ እና ጅሩ አካባቢዎችን ካላቸው ታሪክ እና ጸጋ ጋር ትጠራቸዋለች። ሰላ ድንጋይ ሳሲት፣ አዳባይ፣ ሞጃ በሌሌችም ድምጻዊያን ተደጋግመው ተጠቅሰዋል። መብሬ መንግሥቱ “ደራ ነው” በሚለው ዜማው ደራ እና አካባቢውን ይጥቅሳል።

“አመጸኛው ደራ ይባል ነበር ድሮ

እምቢተኛው መሬ ይባል ነበር ድሮ

አለ ወዲያ ወዲህ ምን ነካው ዘንድሮ” በማለት አካባቢውን ያስተዋውቃል። ድምጻዊ አሸብር በላይ ይፋት፣ ሀገረ ማርያም፣ ማጀቴ፣ አንጾኪያ፣ ገምዛ፣ አጣዬ፣ ካራቆሬ፣ ጣርማበር እና ሸዋ ሮቢትን ያነሳል።

ተስፋዬ ውቤ እና መሠረት በለጠ ቀደም ባለው ዘመን “ባዬሃት፣ ባየሻት” እየተባባሉ የኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ፣ የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ ቦታዎችን ለማስተዋወቅ ዘፍነዋል።

“ባየሻት ሃገሬን ተዘዋውረሽ

ባየሻት ኢትዮጵያን ተዘዋውረሽ

ስንት ነገር አላት የሚያኮራሽ” ይላታል መሠረትን። እሷም ትቀጥላለች።

“ባየሃት ሃገሬን እመዋን

ባየሃት ኢትዮጵያን ሸጋዋን

የተፈጥሮ ውበት ጸጋዋን” ስትል ትመልስለታለች። ተመልከች ይላትና አክሱም ጽዮን፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ ግሸን ማርያምን ፋሲለደስ ቤት መንግሥትን ያስጎበኛታል። እሷም አንተም እስኪ ተመልከት ትለዋለች። መስጊዱን፣ የታሪክ፣ የባህል፣ ቅርስ እና ሌሎች የሀገር ኩራት የሆኑ አሻራዎችን ታሳየዋለች። የጭስ ዓባይ ፏፏቴ መንፈስን ሲያድስ ባየሽው ምነ! ሲላት “የወለጋ ቡና ወርቅ ማዕድኑ፣ “የጅማ የአርባ ምንጭ አረንጓዴ ደኑ” በማለት ትነግረዋለች። የወሎ ፣የጎጃም እና ጎንደር እሸት እና ወተት በረከትን ትጠቅሳለች።

“የሐረር ብርቱካን የአሩሲ ገብስ እሸት

የባሌ ማር ቅቤው የሲዳሞ ወተት

የሸዋ ነጭ ጤፍ የትግራይ አምባሻ

ደስታ ነው ጥጋብ ነው መወለድ ከሐበሻ” በማለት ተስፋዬ ጸጋዎችን ይዘረዝራል። የውኃ አካላት፣ የዱር አራዊት፣ የቤት እንስሳት፣እጽዋት፣ ጠላ እና ጠጅ ፣ ማር እና ወተቱ፣ አዝመራው እሸቱ የኢትዮጵያ ሲሳይ ነው ይላሉ።

አዳነ ተካ አቢሲኒያ በሚል ርዕስ ባቀረበው ሙዚቃው  ኢትዮጵያዊያን ምን አላቸው የሚለውን ለማሳየት ሞክሯል። በጎንደር፣ በወሎ፣ በሸዋ፣ በጎጃም፣ በአርሲ፣ በጅማ፣ በአርባ ምንጭ፣ ትግራይ ወለጋ፣ ጋምቤላ እና ሌሎችም አካባቢዎች ኢትዮጵያዊያን ባላቸው ሀብት እና ጸጋ ተጠቅሰዋል።

ማጠቃለያ

ባህላዊ ሙዚቃዎች ዘመንን ተከትለው ተጉዘዋል። አብዮት ሲሆን እሱን ተከትለዋል። ልማትዊ መንግሥት ሲሆን እንዲሁ፣ ብሔረሰብ ሲሆን እሱን ተከትለው፣ በለውጥ ዘመን ለውጥን ተከትለው ተስተጋብተዋል። ሙዚቃዎች የንግድ ሥራዎች ናቸው። አንድ ጋዜጠኛ በዘር ወቅት ስለ አረም እንደማይዘግበው ሁሉ የሙዚቃ ሥራው ዘመንን እና ወቅትን ለመከተል ሲገደድ አይተናል። የሚሠሩት ለሰዎች ነውና መደመጥ አለባቸው። ለዚህም የአድማጩን ጆሮ እና ዓይን ለማግኘት የሚችሉበትን ወቅት እና ጊዜ ማጤን ግድ ይላቸዋል። ባለፉት 30 ዓመታት የተዘራው የብሔረሰብ እሳቤ ዘር አሁን ፍሬ እያፈራ ነው።

ብሔረሰብ ውስጥ ገብተው እንደ ቀድሞው ዘመን ኢትዮጵያ ሲሉ ልንሰማቸው ያልቻልነው። ብሔር ሃገር ለማከል ሲሞክር እናያለን። ያም ሆኖ ባህላዊ ዘፈኖች ምናልባትም ባህልና ቱሪዝም አካባቢን ለማስተዋወቅ ከሚሠራው በላይ፤ የማስጎብኘት ሥራን ሠርተዋል። ቤታችን ቁጭ ብለን በዓይነ ሕሊናችን ብዙ አካባቢዎችን ጎብኝተናል።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ጥቅምት 11  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here