ተጠባቂው የኢኮኖሚ ዋልታ

0
60

ሀገራት ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሰራሽ እና ሌሎችንም ጎብኚዎችን ሊስቡ የሚችሉ የቱሪዝም ሃብቶቻቸውን ያስተዋውቃሉ:: የመስህብ ሀብቶቻቸውን ሲያስተዋውቁ ለምጣኔ ሐብታዊ ዕድገታቸው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተረድተው ነው:: እንደ ዓለም ባንክ መረጃ (https://www.worldbank.org) ቱሪዝም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የ10 ትሪሊዮን ዶላር አስተዋጽኦ አለው::

በቱሪዝም ገጽታቸውን ይገነቡበታል:: ባህላቸውን ያስተዋውቁበታል:: አብሮነታቸውን ያጎለብቱበታል:: የሥራ ዕድል ይፈጥሩበታል:: ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (https://ilostat.ilo.org) ቱሪዝም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጸው፣ በ2024 እ.አ.አ 270 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አብነት በመጥቀስ ነው::

በአጠቃላይ ቱሪዝም ገጽታን ከመገንባት እስከ ገቢ ማሳደግ ያለውን አበርክቶ ለማሳደግ የቅርስ ልየታ፣ ጥበቃ እና ልማት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት በዓለም ላይ እስካሁን አንድ ሺህ 248 ቅርሶችን መዝግቧል:: ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አንድን ሀገር ለጉብኝት መዳረሻው ሲያደርግ ቀዳሚው የጉብኝት ቦታ ማስረጃ ሆኖ የሚያገለግለውም ይኸው ድርጅት ነው::

ኢትዮጵያም የበርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ እንዲሁም ሃይማኖታዊ በዓላት እና የባህላዊ ክዋኔዎች መነኻሪያ ሆና የዓለም ሕዝብ መክተሚያ ሆናለች:: በዩኔስኮም 15 የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችን አስመዝግባለች::

ከኮቪድ19 ወረርሽኝ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ለጠቅላላው የሀገር ውስጥ ምርት የአራት ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ እንደነበረው የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (https://www.uneca.org) መረጃ ያሳያል::

በእርግጥ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የቱሪዝም የመስህብ ሀብት አንጻር ሲታይ በጎብኝ ቁጥርም ሆነ በገቢ የተመዘገበው መጠን ዝቅተኛ ነው:: 54 የሚደርሱ ቅርሶችን በዩኔስኮ ያስመዘገበችው ፈረንሳይ በ2024 100 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ጎብኝተዋታል:: ይህም 71 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ እንድታገኝ ረድቷታል::

የፈረንሳይ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ለሰጠችው ኢትዮጵያም ሆነ ለሌላው ሀገር በተሞክሮነት የሚታይ ነው:: ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብትነት የምትጠቀማቸው በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ጥብቅ የማኅበረሰብ ሥፍራዎች፣ ብርቅየ የዱር እንስሳት እና የማይዳሰሱ ደማቅ የማኅበረሰብ በዓላት ያሏት ሀገር ናት።

የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ46ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያም ለ38ኛ ጊዜ “ቱሪዝምና ዘላቂ ለውጥ” በሚል መሪ ቃል መከበሩን ከቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል:: ይህም መሪ ቃል ቱሪዝም  ለሀገር ዕድገት ያለውን ፈርጀ ብዙ ፋይዳ የሚጠቁም ነው:: ለግቡም ማህበረሰቡን  ማስገንዘብ፣ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲጎለብት ማስቻል፣ በጎብኚዎችም ዘንድ መነሳሳት መፍጠር ተገቢ ነው::

የአማራ ክልልም ሃይማኖታዊ በዓላትን እና ባሕላዊ ክዋኔዎችን እንደ ስበት ማዕከል ተጠቅሞ የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት እየሠራ ይገኛል:: የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ የእንግጫ ነቀላ እና የቡሄ  በዓላትን ጨምሮ የመስቀል ደመራ፣ የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ በዓል፣ የገና፣ የጥምቀት፣ የመርቆርዮስ፣ የአገው ፈረሰኞች በዓላት የቱሪዝም ዘርፉ ሞተሮች ናቸው:: እነዚህም ክልሉ ያለውን ጸጋ በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው:: እነዚህን በዓላት ለማክበር የሚመጡ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ የመስህብ ሐብቶችን እንዲጎበኙ ዕድል ይፈጥራል::

ክልሉ ሰፊ የመስህብ ሀብቶች መገኛ ቢሆንም የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ደግሞ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በዘርፉ ይበልጥ ጎልቶ እንዳይወጣ አድርጎት ቆይቷል:: በሚዳሰሱ እና በማይዳሰሱ ቅርሶች ዕምቅ ሀብት ያለው ክልሉ በ2017 ዓ.ም ከ12 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ እና ከ27 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች መዳረሻ ሆኖ ማለፉን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያለፈውን ዓመት አፈጻጸሙን ነሐሴ 29 ቀን በገመገመበት ወቅት አስታውቋል:: በዚህ ወቅት ክልሉን ከጎበኙ ቱሪስቶች አምስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱም ተጠቁሟል:: ይህም ክልሉ ምን ያህል እምቅ የመስህብ ሀብት እንዳለው ማረጋገጫ ነው:: የሰላም እጦቱ እንደ ትልቅ ተግዳሮት የሚታይ ቢሆንም ክልሉ ካለው ሰፊ የመስህብ ሀብት አኳያ ግን እስካሁን የተገኘው ውጤት አመርቂ ሆኖ አይታይም::

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) ክልሉ ለቱሪዝም ግብዓት የሚሆኑ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ.. ጸጋዎች ያሉት ቢሆንም ከኮቪድ ወረርሽኝ ጀምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት ያጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች ግን የቱሪዝም ዘርፉ ጎድተውት መቆየታቸውን አረጋግጠዋል::

እንደ ዶ/ር አየለ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ በክልሉ ያሉ የመስህብ ሀብቶችን ከማስጎብኘት ጎን ለጎን ለመጪው ጊዜ የተሟላ የቱሪዝም እንቅስቃሴ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠራ ነው:: ነባር ቅርሶችን መጠገን፣ ማደስ፣ አዳዲስ መዳረሻዎችን ማልማት፣ ሃይማኖታዊ በዓላት እና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችን ማክበር ተፋዞ የቆየውን ቱሪዝም ለማነቃቃት እየተሠራ ነው ብለዋል::

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገኘ ያለውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀምም የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ክልሉን እንዲጎበኙ እየተደረገ ነውም ብለዋል:: ክልሉ ወደተሟላ ሰላም ሲመለስ ክልሉ ወደ ዓለም የቱሪዝም ገበያ ይዞት የሚወጣው ሀብት ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ እንዲሆን ታሳቢ ያደረጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም እየተሠሩ ነው ብለዋል:: አዳዲስ የቱሪዝም የመስህብ ሀብቶችን ከማልማት እና ከማስፋት በተጨማሪ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በአቅም ግንባታ ሥልጠና ማብቃት ለውጭ ሀገር ጎብኝዎች እንደ ምቹ ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል:: አሁንም  ሰላማዊ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች የመስህብ ሀብቶችን የማስጎብኘት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል::

የአማራ ክልል መንግሥት ከ2018 በጀት ዓመት ጀምሮ የሚጀምር የ25 ዓመት የአሻጋሪ የልማት ዕቅድ ተግባራዊ እያደረገ ነው::

ዕቅዱ ለትልልቅ የብዝኃ ኢኮኖሚ ዘርፎች ትኩረት ሰጥቷል ነው ያሉት:: ቢሮዉ  ዕቅዱን ካቀደ በኋላ ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከሚሰሩ ትልልቅ ድርጅቶች፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከዘርፉ ምሁራን፣ ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከቅርስ ባለስልጣን እና ከሌሎችም የካበት ልምድ ካላቸው አካላት ጋር ምክክር በማድረግ በተጨማሪ ግብዓት ማዳበር መቻሉን ተናግረዋል::

ክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ጸጋ በመጠበቅ እና በማደስ ለዓለም የቱሪዝም ገበያ ማቅረብ እንደተጠበቀ ሆኖ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲፈጠሩ የሚያደርግ ዕቅድ ነው ብለዋል:: ጣና ሃቅን እና የሾንኬ መንደርን በዓለም የቅርስ መዝገብ ለማስመዝገብ እየተሠራ ያለውን ሥራ ማሳያ አድርገው አንስተዋል::

ክልሉ በተፈጥሯዊ የቦታ አቀማመጥ፣ በባህላዊ እና በተፈጥዊ ሀብት የታደለ ነው ብለዋል:: ይህም በትንሽ ነገር ተጨማሪ የመስህብ ሀብት ፈጥሮ የቱሪዝም ዘርፉን ለማስፋት አቅም እንደሚሆን ነው የተናገሩት::

ዕቅዱ የት አካባቢ ምን አይነት የቱሪዝም መዳረሻ ማልማት ይገባል የሚለውን የመለሰ መሆኑን አስታውቀዋል:: የዘመኑ አዳዲስ የቱሪዝም ፍላጎቶችን የለየ እንደሆነም አስታውቀዋል:: የተራራ እና የውኃ ላይ ቱሪዝም፤ ታሪካዊ  ትስስር ያላቸው ሁነቶች በተለይም እንደ ጉዞ አድዋ ያሉ አይነት ሁነቶችን እንዲሠሩ ዕቅዱ ትኩረት የሰጠ ነውም ብለዋል:: የበጀት ምንጩ ሁሉ ተለይቶ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑ ለእቅዱ ተግባራዊነት አቅም አድርገው አንስተዋል::

የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን ድርሻ ለማሳደግ የአማራ ክልል የ25 ዓመት የልማት አሻጋሪ ዕቅድን ቀርጾ ወደ ሥራ ሲገባ የቱሪዝም ዘርፉን ማሻሻል ላይ ትኩረት እንደሚሰጠው የገለጹት የክልሉ ፕላን እና ልማት ቢሮ ኃላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር) ከሰሞኑ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው:: ዶ/ር ደመቀ እንደሚሉት እስካሁን የነበረው የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ጥንታዊ ቅርሶች እና አንዳንድ በቅርስነት የተመዘገቡ የመስህብ ሀብቶችን በማስጎብኘት ብቻ የሚገኝ ገቢን ታሳቢ ያደረገ ነው:: “ያለፈው ትውልድ የሠራልንን እና ትቶልን ያለፈውን በአግባቡ አልምተን አልተጠቀምንበትም፤ እንክብካቤም አላደረግንለትም:: መንከባከብ ካለመቻላችንም ባለፈ ለቱሪዝም የሚሆኑ ጸጋዎች በአግባቡ አልተለዩም” ሲሉ የእስካሁን ሂደቱ በዘርፉ ላይ ያሳደረውን ዘርፈ ብዙ ተጽእኖ አስረድተዋል::

የቱሪዝም ዋና አላማው የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ማስረዘም ነው ያሉት ዶ/ር ደመቀ፤ ለዚህም መፍትሄው በክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪ ዕቅድ ላይ መመላከቱን አስታውቀዋል:: የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ለማስረዘም የጉብኝት ቦታዎችን ማስፋት፣ ፍላጎት እና አቅርቦትን ማጣጣም ዋነኞቹ መፍትሄዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል::

በእስካሁን ተሞክሮ ወደ ክልሉ የሚመጡ ጎብኝዎች አማካኝ የቆይታ ጊዜ ሁለት ቀን፤ በገቢ ደረጃም ከአንድ ሺህ 300 ዶላር በታች መሆኑን ዶ/ር ደመቀ አስታውቀዋል:: በመሆኑም የጎብኝውን የቆይታ ጊዜ ለማርዘም የመስህብ ሀብቶች ፍላጎት እና አቅርቦትን ማጣጣም ይገባል ባይ ናቸው::

ጎብኝዎች በስፋት የሚፈልጓቸው ምን እንደሆኑ፣ አብዛኛዎቹ ጎብኝዎች በየትኞቹ የዕድሜ ክልል ላይ እንደሚገኙ፣ ወደ ክልሉ በብዛት የሚገባው ማን (የሀገር ውስጥ ወይስ የውጭ) እንደሆነ ለይቶ መሥራት ለዘርፉ መነቃቃት ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል:: ጎብኝዎችም ወደ ክልሉ ገብተው በአንደኛው አካባቢ የነበራቸውን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ መውጫቸው የገቡበት ሳይሆን በሌላ አቅጣጫ እንዲሆን የሚያደርጉ ሥራዎች በትኩረት ይሠራባቸዋል ብለዋል:: ይህም የቆይታ ጊዜን በማራዘም በገቢ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል::

በአጠቃላይ ክልሉ በ25 ዓመት ዕቅዱ ትኩረት የሰጠው ቱሪዝም ግቡን እንዲያሳካ ግን አስተማማኝ ሰላም እና ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል:: ለዚህም የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here