ተጫዋቾች በረፍት ወቅት

0
153

በዓለማችን ተወዳጅ ከሆኑ ስፖርቶች መካከል እግር ኳስ በቀዳሚነት እንደሚቀመጥ የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል። ይህ ተወዳጅ ስፖርት ከዘጠና ደቂቃም አልፎ የ120 ደቂቃ ስፖርት ነው። ታዲያ በዚህ ዝነኛ ስፖርት ተጫዋቾች በረፍት ጊዜያቸው በቅድመ ውድድር ዝግጅት አልፈው ለውድድር የሚመጥን አቅም እንዴት መፍጠር አለባቸው? የዘርፉ ባለሙያዎች ጥያቄ ነው።

የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ የ2016 የውድድር ዓመት ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም መጠናቀቁ አይዘነጋም። የአዲሱ የውድድር ዓመት ደግሞ መስከረም 10 እንደሚጀመር አወዳዳሪዉ አካል አሳውቋል። የ2016 ዓ.ም የሴቶች ፕሪሚየር ሊግም በተመሳሳይ ሀምሌ 7 ቀን 2016 የተጠናቀቀ ሲሆን አሁን የሁለቱ የሊግ እርከን ተጫዋቾች ረፍት ላይ ናቸው::

በያመቱ የክረምት ወራት ሲቃረብ ብዙ የስፖርት ውድድሮች ተጠናቀው የረፍት ጊዜ ይሆናል።  ይህ የረፍት ጊዜ ተጫዋቾች ከደረሰባቸው የአጥንት ስብራት፣ ከጡንቻ እና ከጅማት ጉዳቶች የሚያገግሙበት፣ የደከመ ሰውነታቸውን እና አዕምሯቸውን የሚያድሱበት ወቅት መሆኑን የፊፋ መረጃ ያመለክታል።

የረፍት ወቅት ተጫዋቾች ከውድድር ነፃ የሚሆኑበት፣ ለመዝናናት ካልሆነ በቀር መደበኛ ውድድር ውስጥ የማይገቡበት ወቅት ነው። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ አካዳሚ መምህር፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የስነ ምግብ ባለሙያ እና የመቻል ስፖርት ክለብ የስነ ምግብ አማካሪ አቶ ዳንኤል ክብረት በጉዳዩ ላይ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የእግር ኳስ አመጋገብ በሀገራችን ገና ተግባራዊ እየሆነ ያለ ሳይንስ ነው። የእግር ኳስ አመጋገብ የተጫዋቾችን አቅም የሚጨምር እንደሆነ የተናገሩት አቶ ዳንኤል ውጤታማ የሚሆነው ግን አመጋገብ፣ ፈሳሽ አወሳሰድ እና የማገገሚያ ስልቶች ተቀናጅተው በአግባቡ ተግባራዊ ሲደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህን ወቅት በተወሰነ መልኩም ቢሆን የቴክኒክ ክህሎታቸውን ለማዳበር ሊጠቀሙበት ይገባል። ከዚህ በተረፈ ግን ተጫዋቾች የረፍት ጊዜያቸውን ለማገገሚያነት ብቻ እንዲጠቀሙበት ይመክራል።

ለእግር ኳስ አመጋገብ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሠራ በአሠልጣኞች የሚፈለገውን የልምምድ ጫና ተጫዋቾች እንዲቀበሉ ያስችላል። ይህ ደግሞ ተጫዋቾች በብቃት ረጅም ጊዜ እንዲጫወቱ ያስችላቸዋል። በተጫዋችነት ዘመናቸው መድረስ ከሚገባቸው ቦታም እንዲደርሱ ያግዛቸዋል። እግር ኳስ ባደገባቸው እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና እና ስፔን በመሳሰሉ የዓለም ሀገራት ይህንን ሳይንስ በሚገባ ተግባራዊ በማድረጋቸው ተጫዋቾቻቸው ያላቸውን አቅም አውጥተው እየተጠቀሙ መሆኑን ያብራራሉ።

የወንዶችም ሆነ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች ረዥም ጊዜ ውድድር ላይ በመቆየታቸው የተጠራቀመ ድካም እና ጉዳት ሊኖርባቸው  እንደሚችል ይጠበቃል። ታዲያ ከዚህ ድካም እና ጉዳታቸው  የሚያገግሙት የረፍት ጊዜያቸውን በአግባቡ ሲጠቀሙበት መሆኑን ባለሙያው አቶ ዳንኤል ያስረዳሉ። የረፍት ወቅቱን በተገቢው መልኩ ከተጠቀሙ አካላቸው ብቻ ሳይሆን አዕምሯቸውም እንደሚታደስ  አቶ ዳንኤል ያስረዳሉ።

ተጫዋቾች ድካም እና ጉዳት ብቻ ሳይሆን በደስታም  ዓመቱን ሊያሳልፉ ስለሚችሉ በወቅቱ  ለቀጣይ የውድድር ዓመት ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት ጭምር ነው። እንዲሁም ደካማ ጎናቸው ላይ ሠርተው ራሳቸውን የሚያሻሽሉበት ነው፤ ይህ የተጫዋቾች የረፍት ወቅት። የተስተካከለ የሰውነት ውቅር የሌላቸው ተጫዋቾችም ራሳቸውን የሚያጎለብቱበት ወቅት ነው።

ተጫዋቾች በረፍት ወቅት የሚሠሩት ልምምድ እንደያቅማቸው መለያየት ይኖርበታል። በአውሮፓ እና በሌሎች ዓለማት ዓመቱን ሙሉ ቋሚ ተሰላፊ ወይም በመጀመሪያው አሰላለፍ ያሳለፉ ተጫዋቾች ምንም እንኳ እንደየ ሀገራት ሊጎች ቢለያይም ከአንድ እስከ ሁለት ሳምንት  ሙሉ ረፍት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። በኛ ሀገር ያለው ባህል ግን እንደዚህ አለመሆኑን ባለሙያው ያምናል። ምክንያቱ ደግሞ በረፍት ወቅት እና በቅድመ ውድድር ዝግጅት መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት ጠባብ መሆኑ ነው።

ታዲያ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ተጫዋቾች ከአምስት ቀን እስከ አንድ ሳምንት ሙሉ ረፍት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል- የባለሙያው ምክረ ሀሳብ ነው። ተጫዋቾች ከሙሉ የረፍት ጊዜያቸው ከተመለሱ በኋላ አካል ብቃት ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንዳለባቸው ተጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪ የጥንካሬ እና የመተጣጠፍ ሥራዎችን መሥራትም ይጠበቅባቸዋል።

በጅምናዚየም የሚሠሩትን ጨምሮ ከንክኪ ነፃ የሆኑ እና ለጉዳት የማያጋልጡ  ቀለል ያሉ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን ግን ማድረግ ይችላሉ ተብሏል። ይሁን እንጂ በሀገራችን በረፍት ወቅት ተጫዋቾች መደበኛ ባልሆኑ ፉትሳል እና መሰል ውድድሮች ላይ ሲያዝወትሩ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ ተጫዋቾችን የበለጠ ለጉዳት የሚያጋልጣቸው በመሆኑ ከእነዚህ ውድድሮች መራቅ ይኖርባቸዋል ብሏል፤ የፊዚዮ ቴራፒ ባለሙያው አቶ ዓባይ ባዝዘው።

ሌላው በዚህ የረፍት ወቅት ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ አመጋገብ ነው። የረፍት ወቅት አመጋገብ ሲባል በተለይ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በአህጉራችንም በተሳሳተ መንገድ እየተተረጎመ እንደሆነ የስነ ምግብ ባለሙያው ይናገራሉ። የሀገራችን ተጫዋቾች በየትኛውም ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ የአመጋገብ ስርዓት መከተላቸው በራሳቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዳያሳዩ መንስኤ ሆኗል።

የእግር ኳስ ተጫዋቾቻችን ዘንድሮም የተወሰኑ የምግብ ምርጫዎችን ከዓመት እስከ ዓመት የመመገብ ባህል ይስተዋልባቸዋል። ከድካም እና ከጉዳት ለማገገም ደግሞ አመጋገባቸውን ማስተካከል እንደሚኖርባቸው የስነ ምግብ ባለሙያው መክረዋል። በውድድሮች ምክንያት በሰውነታቸው ውስጥ በቂ  ኃይል ሰጪ (ካርቦ ሀይድሬት) ንጥረ ነገር ከሌለ እርሱን የሚተካ ምግብ መመገብ ይኖርባቸዋል ብሏል፤ የዘርፉ ባለሙያ። ክለቦችም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ተጫዋቾችን ሊያግዙ ይገባል።

ሌላው አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ በተለይ በረፍት ወቅት  ተጫዋቾች ቡድናዊ ሳይሆን ግላዊ አመጋገብን ማዳበር ይጠበቅባቸዋል። የግብ ጠባቄዎች እና የሌሎች ተጫዋቾች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተመሳሳይ ባለመሆኑ አመጋገባቸውን ግላዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው የተባለው። በተጨማሪም የእያንዳንዱ የተጫዋቾች የሰውነት ውቅር የተለያየ በመሆኑ ግላዊ አመጋገብ ችላ መባል የለበትም ባይ ናቸው፤ አቶ ዳንኤል።

ተጫዋቾች በረፍት ወቅት የኃይል ሰጪ ምግቦችን አጠቃቀም ምጣኔም መቀነስ አለባቸው ተብሏል። ተገቢ የሆነ እና ሳይንሳዊ አመጋገብን አለመከተል በእግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ ዘላቂ ችግር ያስከትላል። በአውሮፓ እግር ኳስ አልፎ አልፎ ሜዳ ላይ ህይወታቸው የሚያልፉ እና ከእግር ኳስ ከተገለሉ በኋላ ክብደታቸው የሚጨምሩ ተጫዋቾች ለዚህ ችግር የሚዳረጉበት ምክንያት ካመጋገብ ጋር የተያያዘ መሆኑ ተነስቷል። ተጨዋቾች በአዲሱ የውድድር ዓመት በተሻለ ብቃት ወደ ውድድር ለመመለስ  ጽሞና ወስደው አዕምሯችው እና አካላቸው ሊያርፍ በሚችልባቸው ቦታዎች ማሳለፍ ይገባቸዋል። ከዚያም ቀስ በቀስ ወደ ልምምድ መግባት ይኖርባቸዋል።

በ2017 የውድድር ዓመት የወንዶች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19 ክለቦች እንደሚሳተፉ አወዳዳሪው አካል አሳውቋል። ታዲያ የክለቦች ቁጥር መጨመር ተጫዋቾች በርካታ ጨዋታዎችን እንዲያደርጉ ያስገድዳል። ይህ ደግሞ በተጫዋቾች ላይ የጨዋታ መደራረብ እና ጫና ያሳድራል። ከዚህ አንጻር ተጫዋቾች ጉዳት እንዳይገጥማቸው እና ከፍተኛ ድካምን መቋቋም እንዲችሉ ከወዲሁ በምን መልኩ አቅማቸውን መገንባት እንዳለባቸው ማሰብ ይጠበቅባቸዋል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here