ተፈጥሮን መጠበቅ ራስን መጠበቅ ነው!

0
131

የሰዉ ልጆች በምቾት እና በህይወት ይኖር ዘንድ ከፈጣሪ ከተሰጣቸዉ ገጸ በረከቶች መካከል አንዷ ለሆነችዉ መሬት ተገቢውን እንክብካቤ እና ጥበቃ ባለማድረጉ አሁን ላይ በየአካባቢዉ ከፍተኛ የሆነ ሙቀት አለፍ ብሎም በጎርፍ መጥለቅለቅ፣  የመሬት መንሸራተት፣ መደርመስ እና  መንቀጥቀጥ እየተከሰተ በሰዉ እና በእንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

ለመሬት እና ለአካባቢ ጥበቃ ተገቢውን እና ቀጣይነት ያለዉ እንክብካቤ ባለመደረጉ እና ችላ በመባሉ ዛሬ ላይ መሬት (ተፈጥሮ) አልቻልሁም አቅቶኛል እያለች  ለሰዉ ልጆችም የድረሱልኝ ጥሪዋን እና የማንቂያ ደወሏን እያሰማች ነው። ረጅም ዓመታትን በመሬት ላይ እንዳሻዉ ኑሮዉን  ሲመራ እና ህይወቱን ሲያስቀጥል የኖረዉ  የሰዉ ልጅ ለተፈጥሮ ሃብት ተገቢዉን እንክብካቤ እና ትኩረት ባለማድረጉ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ እየተከሰቱ ያሉ የተፈጥሮ አደጋወች የሰዉ ልጅን ሊያነቁት እና ምን እናድርግ ብሎ መፍትሔ እንዲፈልግ የሚያስችሉ ማንቂያወች ናቸዉ።

በሃገራችንም ሆነ በአለማችን እየተከሰቱ ያሉ ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን፣ በተቃራኒዉም በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የሰደድ እሳት፣ የመሬት መንሸራተት እና መንቀጥቀጥ የችግሩ ዋነኛ ምልክቶች ናቸዉ። እነዚህ ጉዳዮች እንዲፈጠሩ ያስቻላቸዉም የሰዉ ልጅ እና እንስሳት በሚያደርጉት ከአቅም በላይ የሆነ የመሬት እና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እንደሆነ ይታመናል።

የሰዉ ልጅ ለኑሮዉ ዋስትና ለሆነችዉ መሬት የሰጠዉ አናሳ እንክብካቤና ጥበቃ ዝቅተኛ  በመሆኑ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣዉን የህዝብ ቁጥር ተከትሎ ለእርሻ(ለምግብ)፣ ሰፋፊ መሬቶችን መጠቀም፤ ሲጠቀምም ተገቢዉን እንክብካቤ አለማድረጉ፣ ለምግብ ማብሰያ፣ ግንባታወች፣ ለቤት መስሪያ እና ለቤት ዉስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች መስሪያ የሚጠቀምባቸዉን በርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች በተለይም ዛፎችን ከመቁረጥና ከመጠቀም ባሻገር በምትካቸዉ  ባለመትከሉ እና  የሚተከሉትንም በተገቢዉ መንገድ ባለመንከባከቡ የዛፎች አለመኖርም ለከፍተኛ ሙቀት እና አፈሩንም በጎርፍ ለመሸርሸር እየዳረጋቸዉ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነዉ።

የሰዉ ልጅ ለምግብነት እና ለአልባሳት የሚጠቀምባቸዉን እንስሳትም በአግባቡ ባለመያዙ እና መሬቱን ከሚገባዉ በላይ በልቅ ግጦሽ፣ በደን ቆረጣ እና ቃጠሎ ተግባራት ላይ ማዘዉተሩ እና ለተፈጥሮ ሃብት አያያዝ ተገቢዉን እንክብካቤ ባለማድረጉ የአየር ንብረት ለዉጥ፣ የአፈር መሸርሸር እና መሰል ጉዳቶች ተከስተዋል። ይሁንና የሰዉ ልጅ የሚደርሱትን ጉዳቶችንም እያየ ጀሮ ዳባ ልበስ  በሚል መልክ ለመፍትሄዉ እምብዛም ቦታ ሳይሰጠዉ ቆይቷል።

ዛፎች በተቆረጡት ትክ ባለመተከላቸዉ፣ የአፈር  ክትር ባለመሰራቱ እና አፈሩን የሚይዘዉ  ሳር በልቅ ግጦሽ አማካኝነት በመጋጣቸዉ ሃይቆችና ወንዞች በደለል እየተሞሉ ከዉሃ ሃብት የሚገኘዉ ጥቅም እና የአሳ ሃብትን እንዲቀንስ  ሆኗል። በተለያየ ጊዜ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ብቻ በዓመት የምታጣዉ  የአፈር ደለል አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ቶን ነዉ፤ ይህን ያህል አፈርም ወደ ዉጭ ይወጣል እንደማለት ነው።

በዚህም በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢወች የምርት መቀነስ ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተከሰተ መሬትም  ያለተጨማሪ ግብአት ፍሬ አልሰጥ ካለ ቆየት ብላል። በዓለም ላይ በከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ምክንያት በሚያጋጥም ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር  ምክንያትም ከፍተኛ የሆነ ገቢ እንደምታጣ  የአፈር እና ዉሃ ጥበቃ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ኀይሉ ክንዴ /ዶር/ ለበኩር ጋዜጣ የካቲት 11 2016 ዓ/ም እንዳሳወቁት ዓለም በከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ምክንያት በሚያጋጥም ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር በየአመቱ ከስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ ታጣለች 34 በመቶዉ የሚሆን የሰብል ምርት መታጣትም ይከሰታል ።

ኢትዮጵያ  በመኸር እና በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬትን ከበቂ ዉሃ ጋር አቅፋ የያዘች ሃገር ብትሆንም ክልላችንም ካለዉ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 63 በመቶዉ የሚሆነዉ መሬቱ የተጎሳቆለ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር መረጃ ጠቁሟል።  በመሆኑም የተጎሳቆለዉን  መሬት እንዲያገግም በማድረግ የምርት መትረፍረፍ እንዲፈጠር፣ ምንጮች እንዲፈልቁ፣ የጠፉ እና በመጥፋት ላይ ያሉ እንስሰት እና እጽዋት እንዲመለሱ የማድረግ ስራወች ለነገ የማይባሉ እና በትኩረት ልንሰራቸዉ የሚገቡ ተግባራት ናቸዉ።

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ  ባለመሆኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግስት እና በማህበረሰቡ ዘንድ በትኩረት እየተሰራ  ነዉ። በዚህም  በክልሉ በሁሉም  ወረዳወች እና ቀበሌወች ላይ በየዓመቱ ከጥር አንድ ጀምሮ በስፋት እየተተገበረ ይገኛል። በመሆኑም የተፈጥሮ  ሃብት ጥበቃ ስራን  ሁሉም በእኔነት ስሜት ሊተገብረዉ የሚገባ ተግባር በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁላችንም እንረባረብ።

በኲር የካቲት 3  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here