ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል ግንባር ቀደም ሀገር ናት። ሰፊ እና እምቅ የቱሪዝም ባለቤት እንደሆነችም ይነገርላታል። የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የላልይበላ ውቅር ዐቢያተ ክርስቲያን፣ የጎንደር ዐቢያተ መንግሥት፣ የአክሱም ሃውልት፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ የኦሞ ሸለቆ የከርሰ ምድር ጥናት ስፍራ እና ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች ያሉባት ድንቅ ሀገር ናት።
ዐሥራ ሦስት የሚሆኑ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት አማካኝነት የዓለም ቅርሶች ሆነው እንደተመዘገቡ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በ2015 ዓ.ም ዓመታዊ መጽሔቱ ላይ አስፍሯል።
በኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት ሲነሳ ደግሞ የአማራ ክልል በቱሪዝም ሀብት ፀጋው በቀዳሚነት ይጠቀሳል፤ አራት ቅርሶችንም በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበ ክልል ነው።
ውብ ተፈጥሯዊ እና መልክዓ ምድራዊ ገፅታዎች፣ ብርቅዬ እንስሳት እና ዕፅዋት፣ ታላላቅ ወንዞች እና ሐይቆች፣ አስደናቂ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት እና ዋሻዎች፣ ታሪካዊ ቦታዎች እና ዐቢያተ መንግሥታት፣ ሃይማኖታዊ ቦታዎች፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ባሕላዊ አለባበሶች እና አጨፋፍሮች፣ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክብረ በዓላት የአማራ ክልል ዋና ዋና መገለጫዎች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ተነግሮላቸው የማያልቁ፣ ታይተው የማይጠገቡ እና የማይሰለቹ የሚጎበኙ ቦታዎች በየጊዜው በሚፈጠር ግጭት እንግዶች ተንቀሳቅሰው እንዳይጎበኟቸው እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ይህ ደግሞ የክልሉን እና ሀገራዊውን ምጣኔ ሀብት በእጅጉ ጎድቶታል::
ኑሯቸውን በዘርፉ ላይ ጥገኛ ያደረጉ ዜጎችም በእጅጉ ተቸግረዋል፤ ለአብነትም ላልይበላ፣ ጎንደር እና ባሕር ዳር አካባቢዎች ችግሩ ከጠናባቸው መካከል በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው::
በክልሉ በተከሰተው ግጭት እና አለመረጋጋት ምክንያት ወደ ክልሉ የሚመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት የሰዎችን እንቅስቃሴ ገድቧል። ይህም ኑሯቸውን በቱሪዝም ያደረጉ ነዋሪዎችን ለከፋ ችግር እንዳጋለጣቸው ሐሳባቸውን ለበኩር በስልክ ያካፈሉን ነዋሪዎች ከተለያዩ ቦታዎች አጋርተውናል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ክልሉ እንደፈለጉ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ክልሉ የሚያገኘውን ገቢ ከማሳጣት ባሻገር አስጎብኚ ማሕበራት፣ በሆቴል ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ አስጎብኚዎች (ጋይዶች)፣ በቅሎ አከራዮች፣ ባለሆቴሎች፣ ፎቶ አንሺዎች፣ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የመጓጓዣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ምግብ አብሳዮች፣ የቱሪስት ፖሊሶች እና ሌሎች አካላት ለችግር ተጋልጠዋል።
ሐሳባቸውን በስልክ ካጋሩን መካከል በጎንደር ከተማ አስተዳደር የአስጎብኚዎች ማሕበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ አበባው ጥላሁን አንዱ ነው፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ወደ ሀገሪቱ ብሎም ወደ አማራ ክልል የሚገቡ ጎብኚዎች ቁጥር በእጅጉ በመቀነሱ ኑሯቸው በቱሪዝም ላይ የተመሠረተ ዜጎች ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን ነው የተናገረው። “ቤተ መንግሥቱ ተመልካች አጥቷል” የሚለው አበባው ኑሯቸውን በዘርፉ ያደረጉ ወገኖች አልሞቱም እንጂ በሚያሳዝን ሁኔታ የዕለት ጉርሳቸውን አጥተው በከፋ ችግር ውስጥ ይገኛሉ” በማለት ነው የችግሩን አሳሳቢነት ያብራራው።
ሀገሪቱ ብሎም ክልሉ የገባበት ቀውስ እና የፀጥታ ችግር የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ስለገደበው በዘርፉ የተሰማሩ ወገኖች ቤተሰባቸውን ማስተዳደር አለመቻላቸውን ይናገራል፤ በዚህም ምክንያት “ተመልሰው የእናት እና አባት ጥገኛ ለመሆን ተገደዋል” ነው ያለው። ችግሩ እልባት ካልተሰጠው በቀጣይ በዘርፉ የሚሰማሩ ሙያተኞች እንዳይርቁ ስጋቱን በማንሳት፣ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሔ ሊያስቀምጥ እንደሚገባ ተናግሯል።
በዘርፉ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን እና የአቶ አበባውን ሀሳብ የሚጋሩት ደግሞ በጎንደር ከተማ አስተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ አይቸው አዲሱ ናቸው። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ዘርፉ ችግሮችን እየተጋፈጠ የመጣ ቢሆንም አሁን ላይ ለባሰ ችግር ተጋልጧል ይላሉ።
እንደ ቡድን መሪው ማብራሪያ በጎንደር ከተማ ከሰባት ሺህ በላይ በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች የከፋ ችግር ገጥሟቸዋል። “ሰላም እና ቱሪዝም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው” የሚሉት አቶ አይቸው ለሰላም መስፈን ሀገራዊ ርብርብን እና መግባባትን ይጠይቃል ብለዋል።
ከእልህ መጋባት እና ከመደናበር ፖለቲካ በመውጣት በሰከነ መንገድ ችግሮችን ፈትቶ ለምጣኔ ሀብቱ መሻሻል መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ወገኖች ለረሃብ በመጋለጣቸው አስቸኳይ መፍትሔ ይፈልጋል ብለዋል።
ችግሮችን በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል ከተጎጂዎች ጋር በመሆን ማሳወቃቸውን በማንሳት፣ አስፈላጊውን ድጋፍ እስኪያገኙ ጥረቶች እንደሚቀጥሉ አክለዋል።
በኢትዮጵያ ሊጎበኙ ከሚችሉ ግንባር ቀደም የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች አንዷ ናት – ላልይበላ ከተማ። አብዛኛው የከተማው ነዋሪዎች ከቱሪዝም በሚያገኙት ገቢ ይተዳደራሉ። ነገር ግን በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የሚፈጠሩ ተደጋጋሚ ቀውሶች ዘርፉን በእጅጉ እየጎዳው መሆኑን የቅዱስ ላልይበላ እና አካባቢው አስጎብኚ ማሕበር ጸሐፊ ሞገስ አበበ ለበኩር ተናግሯል።
በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ደረጃው ቢለያይም የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ነው የሚያስረዳው። የክልሉ ሰላም መደፍረስ ችግሩን ውስብስብ እያደረገው ነው ብለዋል። አስጎብኚ ማሕበራት፣ ባለሆቴሎች፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናት፣ በቅሎ አከራዮች፣ ባለታክሲዎች፣ ምግብ አብሳዮች፣ ፎቶ አንሺዎች እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች የገቢ ምንጫቸው ተዳክሞ ችግር ውስጥ ናቸው ብለዋል።
በተለይ አስጎብኚዎች ገቢያቸው ሙሉ ለሙሉ ቁሟል በሚባልበት ደረጃ መሆኑን ይናገራል። ችግሩ ሥር የሰደደ እና ሰፊ በመሆኑ በቀን ሥራ ፍለጋ እየተሰቃዩ ነው ብለዋል። በመሆኑም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የላልይበላ ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ እንደገለፁት በየጊዜው እየተከሰተ ባለው ግጭት እና አለመረጋጋት በቱሪዝም ገቢ በምትተዳደረው ላልይበላ ከተማ በትሩን አሳርፏል ይላሉ። በሰላሙ ጊዜ በዓመት ከ40 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች የመጡበት ጊዜ መኖሩን ያስታወሱት ኃላፊው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በዓመት ከ776 የማይበልጡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ብቻ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በዋናነት ደግሞ አስጎብኚዎች፣ የቱሪስት ድጋፍ ሰጪዎች፣ በቅሎ አከራዮች፣ የሆቴል ሠራተኞች፣ ከ10 ሺህ በላይ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናት የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
እንደ ዲያቆን አዲሴ ማብራሪያ ችግሩ የከፋ በመሆኑ አስጎብኚዎች የቀን ሥራ የሚሠሩበትን መንገድ እየፈለጉ መሆኑን ለበኩር ተናግረዋል። ይበልጥ ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ራሳቸውን የሚደጉሙበት መንገድ እንዲፈጠር ለክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ማሳወቃቸውም ተመላክቷል።
የአማራ ክልል ባሕልና እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) አስተያየት ሰጪዎች ያነሱትን ችግር ሙሉ ለሙሉ ተጋርተዋል። ምክትል ኃላፊው ለበኩር እንደተናገሩት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጀምሮ የቱሪዝም ዘርፉ ክፉኛ ተጎድቷል። በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ዜጎችም ከሥራ ተፈናቅለዋል።
ከሥራ የተፈናቀሉትን እና የተዘጉትን የዘርፉ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ጥናት ተካሂዷል፣ የጉዳት መጠኑም ተለይቶ ለሚመለከተው አካል ቀርቧል። ችግሩን የሚከታተል ባለሙያ ከቢሮው ባለሙያ መመደቡንን ያነሱት ምክትል ኃላፊው ችግሩ በክልሉ አቅም ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን አብራርተዋል። በመሆኑም የሚመለከተው ሁሉ የሚችለውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም