ቱርክን ያሸነፉ መሪ   – አፄ ሠርፀድንግል

0
33

ወደ ኋላ 55 ዓመት ተመልሸ ተያያዥ ትውስታዬን ላንሳ። ዘመናዊውን የቀለም ትምህርት የጀመርኩበት ነው። በባህርዳር ከተማ አፄ ሠርፀድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት። በደርግ ዘመን የአፄ ጥላቻ ነግሶ ስለነበር፤ የትምህርት ቤቱ ነባር መጠሪያ አፄን ቀንሶ ሠርፀድንግል እንዲባል ተወሰነ። ለዘመን ምስጋና ይግባውና የደርግ ዘመን ሲጠናቀቅ የትምህርት ቤቱ መጠሪያም አፄን አካቶ የቀደመ ክብሩን ለመያዝ በቃ። በተለይ በንጉሡ ዘመን ትምህርት ለጀመርን አፄ ሠርፀድንግል የሚለው ስያሜ ልዩ ትውስታ አለው። ምክንያቱም ድንበራችንን ሊደፍር የሞከረውን የቱርክ ሰራዊት ሁለት ጊዜ ድል በማድረግ ሉዓላዊነታችንን ላስከበሩት ቀዳሚው የጎንደር ዘመነ መንግሥት ነጋሢ አፄ ሠርፀድንግል መታሰቢያ እንዲሆን ታስቦ መሰየሙን የተገነዘብነው ገና በልጅነት እድሜያችን  ነው።

የጎንደር ነገሥታት ታሪክ ሲነሳ በአብዛኛው ጎልቶ የሚገለፀው ከ1624 እስከ 1659 ዓ.ም የነበረው የአፄ ፋሲል የሥልጣን ዘመን ነው። ነገር ግን የጎንደር ነገሥታት ታሪክ የሚጀምረው ከ1555 ዓ.ም ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ አፄ ሠርፀድንግል፣ አፄ ያዕቆብ፣ አፄ ዘድንግል፣ አፄ ሱስኒዮስ ተከታትለው በመንገሥ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ ነበር። መቀመጫቸው ደግሞ በጣና ሐይቅ ዙሪያ በዋጅ፣ በጉዛራ፣ በደንቀዝ፣ በደብሳን፣ በጎርጎራ፣ በጎመንጌ፣ በአዘዞ እና አካባቢው ነበር። በመሆኑም  የጎንደር ነገሥታት ታሪክ የሚጀምረው ከአፄ ሠርፀድንግል ነው።

አፄ ሠርፀድንግል ገና ልጅ እያሉ በ13 ዓመት እድሜያቸው ነበር የንግሥና መንበሩን ያገኙት። ከ1555 እስከ 1589 ዓ.ም ድረስም በስልጣን ላይ ቆይተዋል። መስከረም 24 ቀን 1589 ዓ.ም በ47 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል። የሞቱበትን ዕለት መነሻ በማድረግም ለትውስታ ይሆን ዘንድ በዘመናቸው ካከናዎኗቸው አበይት ተግባራት መካከል በጥቂቱ እናነሳሳለን፤ መልካም ንባብ።

አፄ ሚናስ በ1555 ዓ.ም በመሞታቸው፤ አፄ ሠርፀድንግል በአባታቸው ቦታ በ13 ዓመት የልጅነት እድሜያቸው ለመንገሥ በቁ።   ወደ ሥልጣን በመጡበት ዘመን የሃገራችን ስርዓተ መንግሥት በቅጡ የተደራጀ አልነበረም። በዚህም የተነሳ በየአካባቢው ለሚከሰቱ ግጭቶች መፍትሄ መሻት ቀዳሚ ተግባራቸው ሆነ። ከሁሉም በላይ ግን በሰሜኑ የሃገራችን አካባቢ ቱርኮችና የባህረነጋሽ ጦር /የቀይ ባህር አካባቢ የዘመኑ ገዥ/ በጋራ እየፈጸሙት የነበረው እኩይ ተግባር በእጅጉ አሳሳቢ ሆነ። በዚህ የተነሳም በህዳር ወር 1570 ዓ.ም እንትጮ ላይ ጦርነት ለመግጠም ዝግጅት አደረጉ።

አፄ ሠርፀድንግል ጦሩን በሶስት ከፍለው የመሃሉ አዝማች ራሳቸው ሆነው ዘመናዊ መሣሪያ ከታጠቀ  ሰራዊት ጋር መፋለም ጀመሩ። ያልተለመደው የመድፍ ተኩስ ሲደመጥ የንጉሡ ሰራዊት ተደናግጦ ለመሸሽ ሞከረ። አፄ ሠርፀድንግል ግን ወታደሮቹን ማበረታታት ቀጠሉ። እግረኛው ከኋላ እንዲከተልና ፈረሰኛው ወደ መድፉ ጋልቦ ሄዶ በጨበጣ እንዲዋጋ አዘዙ። ተንጋግተው የሄዱ ፈረሰኞች በመድፍ ጥይት አለቁ። የቀሩት ጥቂቶቹ ተርፈው ወደ መድፉ በመጠጋት ቱርኮችን በጨበጣ ተዋግተው አሸነፉ።

“የኢትዮጵያ የአምስት ሺህ ዓመት ታሪክ፤ ከኖኅ እስከ ኢህአዴግ” በሚለው የታሪክ ፅሁፍ ፍስሃ ያዜ አንደገለፀው፤ ሽንፈት የገጠመው ባህረነጋሽ ወዲያውኑ ንጉሡን እርቅ ጠየቀ። አፄ ሠርፀድንግልም “ናና ታርቀን አብረን ሆነን ቱርኮችን እንዋጋ” ሲሉ መለሱለት። “ቱርኮቹንማ እንዴት አድርጌ እክዳለሁ” ብሎ እርቁን ተወዉ።

የቆመው ጦርነት በታህሳስ ወር እንደገና ቀጠለ። በዚህ ጦርነትም ባህረነጋሽ ይስሃቅ በጦር ተወግቶ ወደቀና ሞተ። የቱርኩን ፓሻ ከድር ደግሞ የንጉሡ ታማኝ ዘመድ ዮናኤል ጦር ወርውሮ ገደለው። አንገቱን ቆርጦ በማምጣትም ለንጉሡ አስረከበ። ከዚህ ድል በኋላ ብዙዎቹ ተመልሰው ወደ ንጉሡ ገቡ። በቱርኮች ሰፈርም በርካታ ገንዘብና ልዩ ልዩ እቃዎች፣ ጌጣጌጦች፣ መድፍ እና ዘመናዊ መሳሪያዎች ተማረኩ። የምፅዋ ወደብም ተመልሶ ወደ ንጉሠነገሥቱ ግዛትነት ተለወጠ።

የድሉን በዓል ምክንያት በማድረግም ስርዓተ ንግሥናቸውን እንደአባቶቻቸው በጥንታዊቷ አክሱም ፅዮን ለማክበር ወሰኑ። ጥር 15 ቀን 1570 ዓ.ም አክሱም ገቡ። ከፍተኛ አቀባበልም ተደረገላቸው። የድሉን እና የንግሥናውን በዓል አክብረው፤ ሹመት እና ሽልማት በመስጠት በታላቅ ደስታ ወደ እንፍራዝ/ጎንደር ዙሪያ/ ተመለሱ።

ቱርኮች ከኢትዮጵያ ወደብ ግዛት ሙሉ በሙሉ ካልጠፉ፤ ኢትዮጵያ መቸም የተሟላ ሰላም እንደማታገኝ ንጉሡ የተረዱት ዘግይተው ነበር። በመሆኑም በ1581 ዓ.ም እስከ ጠረፍ ድረስ በመሄድ ተዋጓቸው።

ንጉሡ በየብስ ጠረፍ፤ ቱርኮች በባህሩ ላይ በመርከብ ሆነው ተኩስ ገጠሙ። ቱርኮች በኢትዮጵያ ጦር ላይ ብዙ እልቂት አደረሱ። ይሁን እንጂ ቱርኮችን ለማጥፋት በወሰኑት አፄ ሠርፀድንግል የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር በፅናት ተዋግቶ አሸናፊ ሆነ። ከሞት የተረፈው የቱርክ ጦርም በጀልባ እና በመርከብ እየሸሸ ዳህላክ ደሴት ሄዶ ሰፈረ። ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ ለማጥፋት ግን በወቅቱ ኢትዮጵያ መርከብ ስላልነበራት አልተቻለም።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሃማሴን እና ጠረፉ፤ በአፄ ሠርፀድንግል እጅ ሆነ። ንጉሡ ሁለት ጊዜ ቱርኮችን በማሸነፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ጥረት አድርገዋል። የሃገር ውስጥ ሰላምን አስተማማኝ ለማድረግም ተግተው ሰርተዋል። ሌሎች የአስተዳደር ስራዎችም እያከናወኑ ያለ ረፍት ጥረት በማድረግ ለ34 ዓመት በሥልጣን ቆይተዋል። ህይወታቸው ያለፈው ደግሞ መስከረም 24 ቀን 1589 ዓ.ም በ47 ዓመታቸው ነው። ሰላሙን ሁሉ ለኢትዮጵያ በመመኘት ፅሁፉም በዚሁ ተቋጨ።

ሳምንቱ በታሪክ

“የክራሩ ጌታ” ሞተ

የክራሩ ጌታ፣ የኮሪያው ዘማች ካሳ ተሰማ የተወለደው በቀድሞው አጠራር ሸዋ ክፍለ ሃገር መናገሻ አውራጃ የካቲት ስድስት ቀን 1919 ዓ.ም ነው። የክራር ጨዋታን ከድምፅ ጋር አዋህዶ ማቅረብን አሳምሮ ያውቅበታል።

በ1950 ዎቹ መጀመሪያ የቃኘው ሻለቃ ወደ ኮሪያ ሲዘምት አብሮ ዘምቷል። ሲመለስም የብሄራዊ አገልግሎት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልሟል።

በ1964 ዓ.ም ይሰራበት ከነበረው ክብር ዘበኛ የጦር ክፍል በጡረታ ተሰናበተ። በውብ ክራር ተጫዋችነቱ የሚታወቀው ሃምሳ አለቃ ካሳ ተሰማ በ47 ዓመት እድሜው ጥቅምት አንድ ቀን 1966 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ምንጭ፦ ውክፔዲያ

 

ፕሬዚዳንቱ በአደባባይ ተገደሉ

ግብፅ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ አንድትወጣ የተደረገውን ትግል ተሳትፈዋል። ከእርሳቸው ቀድመው የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት ናስር ሲሞቱ፤ ከምክትል ፕሬዚዳንትነት ወደ ዋና ፕሬዚዳንትነት ተሸጋገሩ – አንዋር ሳዳት።

የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት አንዋር ሳዳት በአባታቸው ግብፃዊ፤ በእናታቸው ደግሞ የሱዳን ዝርያ አላቸው።

ግብፅ ሰላም እንድትሆን ከፍተኛ ፍላጎት አሳደሩ። በዚህም የተነሳ በጠላትነት ይተያዩ በነበሩት እስራኤል እና ግብፅ መካከል ለሰላም እንዲሰፍን ወደ እስራኤል ተጉዘው ባደረጉት ንግግር የእስራኤልን ሃገርነት ተቀብያለሁ አሉ።

የፕሬዝዳንቱ ስምምነት በአብዛኛው የአረብ ሃገራት ፍልስጤማውያንን እንደመካድ ተቆጥሮ ቁጣን ቀሰቀሰ። የአረብ የሽምቅ ተዋጊዎች ሳዳትን ለመግደል ዛቱ ፤ በአረቡ ዓለም ውጥረት ነገሰ።

የሳዳት ድርጊት ግብፅን ከአረብ ሊግ አባልነት ወጪ አደረጋት። መስከረም 26 ቀን 1974 ዓ.ም ደግሞ ካይሮ ላይ በተካሄደ ወታደራዊ ሰልፍ በስምምነቱ የተቆጡ የሃገራቸው እስላማዊ ጂሃዲስቶች በአደባባይ ጥይት ተኩሰው ገደሏቸው።

ምንጭ፦ አሶሸትድ ፕረስ

 

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here