ታላላቅ የአትሌቲክስ ፉክክሮች

0
156

ባለፉት ስድሳ ዓመታት ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ እና ዩጋንዳ በአትሌቲክሱ ዘርፍ፤ በመካከለኛ እና በረጅም ርቀት የበላይነታቸውን አሳይተዋል። የምሥራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለም የአትሌቲክስ መድረክ ወደር የማይገኝላቸው መሆናቸውን በተደጋጋሚ አሳይተዋል፤ እያሳዩም ናቸው።

ስልጠናቸውን በከፍተኛ ቦታዎች ማድረጋቸው፣ ያላቸው ከፍተኛ ተነሳሽነት፣ የተለየ የአመጋገብ ሥርዓት መከተላቸው፣ ባህላዊ አኗኗራቸው እና ዘረመላቸው ስኬታማ እንዳደረጋቸው ቲም ኬኒያ የተባለ ድረገጽ አስነብቧል። በተለይ በረዥም ርቀት በሁለቱም ጾታዎች ከ90 በላይ የዓለም ክብረወሰኖች የተሰበሩት በምሥራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች ብቻ ነው።

ለአብነት በቅርቡ በተደረገው የ2024ቱ የቺካጎ ማራቶን ኬኒያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች በኢትዮጵያዊቷ ትዕግስት አሰፋ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን ማሻሻሏ አይዘነጋም። ባለፉት ስድስት ዐስርት ዓመታት ውስጥም የምሥራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች በመካከለኛ እና ረዥም ርቀት ሲያንጸባርቁ፤ የአውሮፓውያን አትሌቶች ሚና አነስተኛ ነበር።

እ.አ.አ በ2008፣ 2012 እና 2016 የበጋ ኦሎምፒክ መድረክ የምሥራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች በተለይ ኢትዮጵያውያን እና ኬኒያውያን በመካከለኛ እና በረጅም ርቀት ከተዘጋጀው ሜዳሊያ 70 በመቶውን ወስደውታል። በተለይ  የኢትዮጵያ እና የኬኒያ አትሌቶች ከ1990 እ.አ.አ ጀምሮ የመም እና የጎዳና ላይ ውድድሮችን ያለማቋረጥ እየተፈራረቁ አሸንፈዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች ለመሮጥ የተወለዱ ናቸው በማለት ብዙ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመሰክሩላቸዋል። በበርካታ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ድንቅነታቸው  የሚመሰከርላቸው ኃይሌ ገብረ ስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣  ፖል ቴርጋት፣ ኢሉድ ኪፕቾጌ እና ቪቪያን ቺሮዮት ይገኙበታል። በዚህ የበኵር እትማችን በአትሌቲክስ ታሪክ በየ መድረኩ ሲገናኙ  ትንፋሽን የሚያስውጡ እና ልብን የሚያሞቁ ፉክክሮችን የሚያደርጉ አትሌቶችን እናስነብባችኋለን።

ዓለም ከማይዘነጋቸው የምሥራቅ አፍሪካ የአትሌቲክስ ፉክክሮች መካከል የሁለቱ ግዙፍ አፍሪካውያን የቀድሞ አትሌቶች ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ እና ፖል ቴርጋት የሚያደርጉት ፉክክር ቀዳሚው ነው። በዘርፉ ስመ ጥር የሆኑት እነዚህ አትሌቶች በአትሌቲክስ ህይወታቸው 19 ጊዜ ተገናኝተዋል።

እ.አ.አ ከ1993 እስከ 2007 ድረስ ለ14 ዓመታት ያህል ከመም እስከ ጎዳና ላይ ውድድር በተለያዩ መድረኮች ተፎካክረዋል። እርስ በእርሳቸው ከተገናኙባቸው 19 መድረኮች መካከል ፖል ቴርጋት በጎዳና ላይ ውድድሮች የተሻለ እንደነበር የግል የታሪክ ማህደሩ ያስነብባል። በጎዳና ላይ ውድድር ሦስት ጊዜ የተፎካከሩ ሲሆን ሁለቱን ማሸነፍ ችሏል።

በመም ውድድሮች ግን ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ሁሉንም ውድድሮች በማሸነፍ የበላይነቱን አሳይቷል። ለአብነት በፈረንጆች ሚሊኒየም በሲድኒ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር ርቀት ያደረጉትን ፉክክር በዓለማችን ከታዩ ድንቅ አጨራረሶች መካከል የዓለም አትሌቲክስ በቀዳሚነት አስቀምጦታል። አንገት ላንገት በመተናናቅ እልህ አስጨራሽ ፉክክር ባደረጉበት በዚህ መድረክ ሻለቃ ኃይሌ በዘጠኝ ማይክሮ ሴኮንድ ቀድሞ በመግባት አሸናፊ መሆን ችሏል።

“በፖል ቴርጋት እና በሌሎች ኬኒያውያን አትሌቶች ምክንያት ብዙ ክብረወሰን እንድሰብር አግዞኛል። እነርሱ ባይኖሩ ይህን ማድረግ አልችልም ነበር። ይህ አስደናቂ ነገር ነው”። በማለት ስለፉክክሩ በአንድ ወቅት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ መናገሩ የሚታወስ ነው። በሁለቱ የቀድሞ አትሌቶች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት ለሌሎችም አርአያ መሆን እንዳለበት መረጃው አስነብቧል።

የቀነኒሳ እና የሌላኛው ኬኒያዊ አትሌት ኢሊዩድ  ኪፕቾጌ ፉክክርም በአትሌቲክስ ታሪክ ተደጋግሞ የሚነሳ ነው። እ.አ.አ በ2003 ነው የሁለቱ ታላላቅ አትሌቶች ፉክክር የጀመረው። በኦስሎ ብስሌት ጨዋታዎች የተጀመረው ፉክክር በ2024ቱ የፓሪስ የዓለም ሻምፒዮናም ቀጥሏል። በመጀመሪያ ግንኙነታቸው ኬኒያዊው አትሌት ሲያሸንፍ ቀነኒሳ በቀለ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ነበር የጨረሰው።

በዚህ መልኩ የተጀመረው ፉክክር ባለፉት 21 ዓመታት እስከ ማራቶን ዘልቋል። ቀነኒሳ በቀለ በ2004 እ.አ.አ ነበር ግሪክ አቴንስ ላይ በተደረገው ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ የተሳተፈው። በወቅቱ በ10ሺህ ሜትር ሻለቃ ኃይሌ ለአልጋ ወራሹ ዙፋኑን ያስረከበብት በመሆኑ ብዙዎች ያስታውሱታል። በዚህ የኦሎምፒክ መድረክ ቀነኒሳ ከኢሊዩድ ኪፕቾጌ ጋር የተፎካከረው በአምስት ሺህ ሜትር ነበር።

ሞሮኳዊው አትሌት ሀኪም ኤል ጉይሮጅ ርቀቱን በበላይነት ባጠናቀቀበት መድረክ ቀነኒሳ እና  ኪፕቾጌ በ11 ማይክሮ ሴኮንድ ልዩነት ተከታትለው ጨርሰዋል። በ2008 እ.አ.አ የቤጂንግ ኦሎምፒክ ቀነኒሳ በዐስር እና አምስት  ሺህ ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያ አሳክቷል። በአምስት ሜትር ሺህ ርቀት የተካፈለው ኬኒያዊው አትሌት ቀነኒሳን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ነበር ያጠናቀቀው።

ዝምተኛው አትሌት ቀነኒሳ በፈረንጆች 2019 ነበር ፊቱን ወደ ማራቶን በማዞር ውደድር የጀመረው። ተቀናቃኙ አትሌት ኢሊዩድ  ኪፕቾጌ ደግሞ ቀደም ብሎ እ.አ.አ በ2013 ማራቶን መጀመሩን የግል የታሪክ ማህደሩ ያሳያል። እ.አ.አበ2019 በወርሃ መጋቢት በተደረገው 36ኛው የለንደን ማራቶን ሁለቱ አትሌቶች በማራቶን የተገናኙ ሲሆን ኪፕቾጌ በበላይነት አጠናቋል። ቀነኒሳ ደግሞ ሦስተኛ ሆኖ ጨርሷል።

ቀነኒሳ በመም ውድድሮች የተሻለ አትሌት መሆኑን ከ2005 እስከ 2011 ባሉት ዓመታት ፉክክሩን በማሸነፍ አስመስክሯል። በጎዳና ላይ ሩጫ ግን ኪፕቾጌ የተሻለ መሆኑን ቁጥሮች ይናገራሉ። በተፎካከሩበት አራት የማራቶን ውድድሮች ሁሉንም ኬኒያዊው አትሌት አሸንፏልና ነው።

የጥሩነሽ ዲባባ እና የኬኒያዊቷ ቪቪያን ቺሪዮት ፉክክርም ሌላው አስደናቂ የሚባል የምሥራቅ አፍሪካ ፉክክር ነው። ሁለቱ አትሌቶች በአጠቃላይ 17 ጊዜ ተፎካክረዋል። ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት 15ቱን በማሸነፍ የበላይነት አላት። ኬኒያዊቷ አትሌት ደግሞ በቀሪው በሁለቱ ውድድር አሸንፋለች። ጥሩነሽ እና ቺሪዮት በፈረንጆች ሚሊኒየም ማግስት በ2001ዱ የቤልጂየም ኦስተንዴ የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር ነው ፉክክራቸውን የጀመሩት።

እ.አ.አ በ2008 የቤጂንግ ኦሎምፒክ ጥሩነሽ ዲባባ በአምስት እና ዐስር ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ አዲስ ክብረወሰን ማስመዝገቧ አይዘነጋም። በአንጻሩ ቪቪያን ቺሪዮት በተወዳደረችበት የአምስት ሺህ ሜትር አራተኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው።

ኬኒያዊቷ የቀድሞ አትሌት በቤልጂየም ብራስልስ የዓለም ሀገር  አቋራጭ እና በለንደን ማራቶን ውድድሮች ብቻ ነው ጥሩነሽን ማሸነፍ የቻለችው። ምንም እንኳ ኬኒያዊቷ አትሌት በተወዳደረችበት በርካታ መድረኮች ጥሩነሽን ማሸነፍ ባትችልም ቀላል ግምት ግን የሚሰጣት አልነበረችም። ሁለቱም አትሌቶች ያለጥርጥር በምሥራቅ አፍሪካ ከታዩ ቀዳሚ ምርጥ ሴት አትሌቶች መሆናቸውን የዓለም አትሌቲክስ ይመሰክራል። ሁለቱ አትሌቶች ከተቀናቃኝነታቸው ባሻገር ጥሩ ወዳጆች መሆናቸውም ይነገራል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአንድ ሺህ 500 ሜትር ርቀት ጉዳፍ ፀጋዬ እና ኬኒያዊቷ ፌዝ ኪፒዮጎን እንዲሁም በ800 ሜትር ጽጌ ዱጉማ እና ሌላኛዋ ኬኒያዊት ሜሪ ሞራ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከሚታዩ ምርጥ የምሥራቅ አፍሪካ ፉክክሮች ናቸው።

አሁን ላይ ግን አውሮፓውያን እና አሜሪካውያን የስልጠና መንገዳቸውን በማዘመናቸው ምሥራቅ አፍሪካውያን የሚኮሩበትን የመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቆጣጠር ጀምረዋል። በተጨማሪም በምሥራቅ አፍሪካ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የሀብት ውስንነት አትሌቶችን ወደ አውሮፓ አስኮብልሎ ፉክክሩ  እንዲቀዘቅዝ አድርጓል ነው የተባለው።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ጥቅምት 11  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here