ታላላቆችን ማክበር

0
47

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? ለመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና እየተዘጋጃችሁ እንደሆነ እና የተሻለ ውጤት እንደምታመጡም ተስፋ እናደርጋለን::

ልጆች፣ የሕጻናት አዕምሮ የአየውንና የሰማውን እየመዘገበ ያስቀምጥ እና በወደፊት ሕይወቱ ላይ ይመነዝረዋል። ልጆች ከሌሎች ልጆች፣ ወላጆች እና ትልልቅ ሰዎች ጋር ያላቸው መስተጋብር የወደፊቱን ማንነታቸውን ይገነባል:: እኩዮቻቸውን እና ታላላቆቻቸውን ማክበር ደግሞ የኢትዮጵያዊነት እሴታቸው እና ለወደፊት ሕይወታቸው መሠረት ነው::

የአብሥራ ክንዴነው በሰላም አርጊው ቅድስት ድንግል ማሪያም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ናት:: የአብሥራ ታላላቆቿን  ማክበር በቤቷም ሆነ በትምህረት ቤት እንደምትማር ነግራናለች:: በቤት ውስጥ እናት እና አባቷ እንዲሁም ታላላቅ ወንድሞቿ ከእሷ በእድሜ የሚበልጥንም ሆነ እኩያዋ የሆኑ ልጆችን ማክበር እንዳለባት ይመክሯታል::

በትምህርት ቤቷ ደግሞ በግብረ ገብ እና ግዕዝ ትምህርቶች ሰውን ስለማክበር ትማራለች:: ሰውን ማክበር በሌሎች ዘንድ አክብሮትን እና ትልቅ ቦታን ያሰጣል:: ሰዎች ለሚያከብራቸው ሰው መውደድ እና በምላሹ  አክብሮትን እንደሚለግሱት በግብረ ገብ ትምህርት እንደተማረች የአብሥራ ነግራናለች:: ለጤናማ የእርስ በርስ ግንኙነትም መከባበር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የአብሥራ ነግራናለች::

የአብሥራ እንደነገረችን በግዕዝ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ከቋንቋው ባሻገር መልካምነት፣ ሰው አክባሪነት፣ ለሌሎች ማዘን እና ፈጣሪን መፍራት እንዲሁም ቃሉን መጠበቅ የመሳሰሉትን ርዕሰ ጉዳዮች ይማራሉ:: ወደ እምነት ተቋማት መሄድም ሰውን የማክበር ልምድን ያዳብራል::

ተማሪ የአብሥራ ታላላቆቿን እንደምታከብር ሁሉ ታናናሾቿን ደግሞ ትወዳለች፤ ትንከባከባለች:: በገባት እና በምትችለው መጠን በትምህርታቸው እና በሌሎች ጉዳዮች ታግዛቸዋለች:: ልጆች የአብሥራ ጎበዝ ናት አይደል? እናንተም እንደ የአብሥራ ታላላቆቻችሁን አክብሩ እንዲሁም ታናናሾቻችሁን ውደዱ፤ አግዙ::

 

ተረት

ብልሁ ጥንቸል

ኬማ የሚባል ጥንቸል ነበር:: ከዕለታት አንድ ቀን የኬማ እናት ኬማን ከጓሮ ካሮት አምጣልኝ በማለት አዘዘችው:: ኬማም ካሮቶችን ለማምጣት ክብ ሰሃን እና መቆፈሪያ ይዞ ወደ አትክልት ስፍራው ሄደ:: አትክልት ስፍራውም ላይ እንደደረሰ ካሮቶችን ከአፈሩ ውስጥ እየነቀለ አወጣቸው:: ከቤት የወሰደውን ክብ ሰሀን በካሮት ሞልቶ ወደ ቤቱ ለመመለስ ጉዞ ጀመረ::

ሰፈር ውስጥ የሚኖሩ መጥፎ ጥንቸሎች ኬማን መንገድ ላይ አገኙት:: እነዚህ ጥንቸሎች ተልከው የሚወጡ ጥንቸሎችን መንገድ ላይ ጠብቀው ዕቃ የሚቀሙ እና የሚደባደቡ ናቸው:: ኬማ ገና ሲያያቸው ፈራ::

ከጥንቸሎችም መካከል አንደኛው ኬማን በቁጣ ከጠራው በኋላ “የያዝከውን ካሮት ከነሰሀኑ አስቀምጠህ ሂድ!” በማለት አስፈራራው:: ኬማ ጥንቸሉ ያለው ነገር ቢያስደነግጠውም በጣም ብልህ ስለሆነ ምን ማድረግ እንዳለበት ማሰብ ጀመረ:: ወዲያውኑ አንድ ሀሳብ ብልጭ አለለት:: “እሺ ካሮቶቹን እሰጣችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእናንተ መካከል በጣም ፈጣን ሯጭ የሆነው ጥንቸል ካሮቶቹን ወስዶ ያከፋፍላችሁ” አላቸው:: ጥንቸሎቹ “ፈጣን ሯጭ እኔ ነኝ፤ አንተ አይደለህም፤ እኔ ነኝ” እየተባባሉ እርስ በርስ ተጣሉ::

በዚህ መካከል ኬማ ድምፁን ከፍ አድርጐ “ከምትጣሉ ለምን አሁን የሩጫ ውድድር አታደርጉም ያሸነፈው ጥንቸል ካሮቶቹን ያከፋፍላል:: ለራሱ ደግሞ ከካሮቶቹ አብልጦ ይወስዳል” አላቸው:: እነሱም በኬማ ሀሳብ ተስማምተው እየተሽቀዳደሙ ወደ ፊት ተፈተለኩ:: ኬማም መሄዳቸውን ሲያይ ካሮቶቹን ይዞ ወደ ቤቱ ሮጠ:: ችግሮች ሲያጋጥሙ በብልሀት ማለፍን ከተረቱ እንማራለን፡፡

 

ይሞክሩ

ለአህያ አናፋ ከተባለ ለአንበሳ ምን ይባላል?

የዶሮ ማደሪያ ስሙን ጥቀስ?

የምስጥ መኖሪያ ምን ይባላል?

መልስ

አገሳ

ቆጥ

ኩይሳ

ነገር በምሳሌ

  • ስንቁን የተቀማ ነጋዴ፣ ዋግ የመታው ስንዴ፤ ብርታት የሚገኘው ጤና ከመሆን እና ከምግብ ነው፡፡

 

  • መተው ነገሬን ከተተው፤

ትግስት ጥሩ ነው፡፡

 

  • ለማይሰጥ ሰው ስጡኝን ማን አስተማረው፤ ሳይሰጡ መቀበል የለም

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የታህሣስ  20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here