ታላላቆችን ያፈራዉ ቤት ችግር

0
135

የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

ደብረ ብርሃን እና አካባቢው ለአትሌቲክስ ስፖርት ምቹ ከሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች መካከል ከቀዳሚዎች ተርታ ይሰለፋል። አካባቢው ከባህር ወለል በላይ ከ2,700 እስከ ሦስት ሺህ ሜትር ከፍታ እንዳለው ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ከአየር ንብረቱ ተስማሚነት እና ምቹነት  ባሻገር ደብረ ብርሃን ከተማ እና አካባቢው ለአትሌቲክስ ስፖርት ያለው ፍቅር የተለየ ነው። በመሆኑም ቦታውን ለዘርፉ ተመራጭ አድርጎታል።

የደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የተቋቋመው በ2001 ዓ.ም ሲሆን ማዕከሉ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ በተደራጀ መልኩ ሥራ መጀመሩን ያገኝነው መረጃ ያመለክታል።   ማሰልጠኛ ማዕከሉ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 20 ወንድ እና 20 ሴት አትሌቶችን እየያዘ ሲያሰለጥን ቆይቷል።  ከአምስት አመታት በፊት በአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከሉ የአንድ አትሌት ቆይታ ሁለት ዓመታት ብቻ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከሁለት እስከ አራት ዓመታት ተደርጓል። አትሌቶች በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ብቁ መሆናቸው ከተረጋገጠ ግን አራት ዓመታት እንዲቆዩ አይገደዱም። ይህ ደግሞ አትሌቶች ብቁ ሆነው ከማሰልጠኛ ማዕከሉ እንዲወጡ አግዟቸዋል።

ማዕከሉ ባለፉት 15 ዓመታትም በዓለም እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የታዩ ስመ ጥር አትሌቶችን አፍርቷል። ለብሄራዊ ቡድን በርካታ አትሌቶችን አብቅቷል፤ ለክለቦችም ቢሆን ብዙ አትሌቶችን መግቧል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች ላይም ክልሉ ለሚያስመዘግበው ውጤት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ይህ የማሰልጠኛ ማዕከል ነው።

የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከሉ እስካሁን ከ120 በላይ ወጤታማ አትሌቶችን አፍርቷል። ከእነዚህ ውስጥ 72ቱ ብሄራዊ ቡድኑን ያገለገሉ እና እያገለገሉ ያሉ ጭምር ናቸው። ለአብነት በ800 ሜትር ከመሀመድ አማን በኋላ በወጣቶች የዓለም ሻምፒዮና ወርቅ ያሳካው መለሰ ንብረት፣ በዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር ሻምፒዮን የሆነችው ታገኝ ወልዱ፣ በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና አሸናፊ የሆነችው ቃል ኪዳን ፈንቴ፣ ታላቁ ሩጫን ሦስት ጊዜ ያሸነፈው አቤ ጋሻው፣ የኔዋ ንብረት እና የመሳሰሉት የደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ተጠቃሽ ፍሬዎች ናቸው።

እነዚህን እና ሌሎችንም ድንቅ አትሌቶች ያፈራ እና ለሀገር ያበረከተ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አሁን ላይ ችግር እንደገጠመው አሰልጣኝ አማረ ሙጨ ለአሚኮ በኵር ስፖርት ዝግጅት ክፍል ተናግሯል። አሰልጣኝ አማረ ሙጨ በደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጣኝ ናቸው። አሰልጣኙ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ዐስር ዓመታት በማዕከሉ በአሰልጣኝነት አገልግሏል፤ አሁንም እያገለገለ ይገኛል። የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከሉ አሁን ላይ የገንዘብ ችግር ገጥሞት ሥራ አቁሟል።

ማሰልጠኛ ማዕከሉ  የገንዘብ እጥረት ገጥሞት መንገዳገድ የጀመረው ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን አሰልጣኝ አማረ ያስረዳሉ። ይህ የሆነው ደግሞ በጀት ሲመደብ ከአምስት ዓመታት በፊት በነበረው የሀገሪቱ የገበያ ሁኔታ በመሆኑ ነው ይላሉ አሰልጣኙ። አሁን ላይ የገበያ ሁኔታው እና የኑሮ ውድነቱ በመጨመሩ እየተመደበ ያለው በጀት ወቅታዊ የገበያ ሁኔታውን ያላገናዘበ በመሆኑ ሥራ ለማቆም ተገደናል ብለዋል አሰልጣኙ።

በተጨማሪም በሰሜኑ ጦርነት በተፈጠረው ችግር የማሰልጠኛ ማዕከሉ ጉዳት ደርሶበታል።  የጅምናዚየም መሳሪያዎች እና ሌሎችም የስፖርት ቁሳቁሶች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። የመሮጫ መሙ (Track) አለመጠናቀቁም ሌላኛው ችግር መሆኑን አሰልጣኙ አብራርቷል።  እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተቀርፈው ማሰልጠኛ ማዕከሉ ሥራ እንዲጀምር አሰልጣኝ አማረ ሙጨ ጠይቋል። እየተመደበ ያለው በጀት እና ማሰልጠኛ ማዕከሉ የሚፈልገው በጀት ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ወቅቱን ያገናዘበ በጀት እንዲመደብላቸውም ጠይቋል።

የማብስያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ብርድ ልብስ እና ሌሎች የስፖርት ቁሳቁሶች ማሰልጠኛ ማዕከሉ ሥራ  ሲጀምር የተገዛ በመሆኑ አርጅቷልና መቀየር አለበት ብሏል። የደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከልን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ነው። ቢሮ ባለቤትነቱን ለሌሎች ተቋማት በመስጠት ችግሩን መቅረፍ ይኖርበታል የሚል የመፍትሄ ሀሳብ ተነስቷል።

የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በወሎ ዩንቨርስቲ ባለቤትነት ስር የሚተዳደር ሲሆን አሁን ላይ ወደ ከፍታ እየተንደረደረ ይገኛል። “ታዲያ ልክ እንደ ተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በደብረ ብርሃን የሚገኙ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ማሰልጠኛ ማዕከሉን እንዲደግፉ የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ማድረግ ይገባዋል” ብሏልም አሰልጣኙ።

የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከሉ ባለቤት የሆነው የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ በተገቢው መንገድ ክትትል እና ምልከታ የማድረግ ችግር አለበት የሚል ቅሬታም ተነስቷል።  የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ እርዚቅ ኢሳ ከሰሜን ሸዋ ዞን ወጣቶች ስፖርት መምሪያ ጋር ችግሩን ለመቅረፍ የተነጋገሩ ቢሆንም እስካሁን ግን ከወሬ ባለፈ ተጨባጭ ለውጥ አልመጣም ነው የተባለው።

ከአምስት ዓመታት በፊት በአማራ ክልል በተዘጋጀ የማሰልጠኛ ማዕከላት ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ አንድ ማሰልጠኛ ማዕከል እንደየ ደረጃው ባለቤትነታቸው እንደሚወሰን ያትታል አዋጁ።እናም በዚህ አዋጅ መሰረት የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ባለቤትነቱን ቢያነሳ የማሰልጠኛ ማዕከሉ ችግር ይቀረፋል የሚል ተስፋ ይዘዋል።  ከክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ይልቅ ደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ወይም በአቅራቢያ የሚገኝ ተቋም ቢይዘው ውጤታማ ይሆናልም የሚል እምነት አላቸው።

በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው  የደብረ ብርሃን እና የተንታ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የግብአት ማሟላት ሥራ እንዲከናወን የአማራ መልሶ ግንባታ ኮሚቴን መጠየቃቸውን በአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ፋሲሊቲ እና የማዝወተሪያ ስፍራ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ባንተአምላክ ሙላት ተናግረዋል። ክልሉ የበጀት እጥረት ስላለበት በነበረው በጀት እንዲጠቀሙና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ድጋፍ እንደሚያደርግ ጭምር ከከንቲባው ጋር መነጋገራቸውን ደግሞ የገለጹት የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጋሻው ተቀባ ናቸው።

ከዞኑ፣ ከከተማ አስተዳደሩ እና ከከተማ አስተዳደሩ ስፖርት መምሪያ ጋር በጉዳዩ ላይ ተነጋግረናል ያሉት ምክትል የቢሮው ኃላፊው፤ ሥራው እንደ አዲስ እየተጀመረ መሆኑንም ነግረውናል። የሰልጣኞች ምልመላ መደረጉን እና የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከሉ አጥር በከተማ አስተዳደሩ አማካኝነት እየተሠራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

የመሮጫ መም (Track)  ማስተካከል እና የተጀመሩትን ማጠናቀቅ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊነት እና ተግባር ቢሆንም የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ለማጠናቀቅ የበጀት እጥረት ስላጋጠመው አሁን የታሰበ ነገረ የለም ተብሏል። ሌላው የማሰልጠኛ ማዕከሉ በማን ይመራ ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሕጋዊ አሠራርን ተከትለው ምላሽ የሚሰጡ መሆኑን አቶ ጋሻው ተናግረዋል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here