ታላቁ ኢያሱ

0
35

የዐፄ ፋሲለደስ አራተኛ ልጅ የሆኑት የቀዳማዊ ዮሐንስ ልጅ ቀዳማዊ እያሱ፣ በስመ መንግሥታቸው አድያም ሰገድ ወይም ታላቁ እያሱ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው በ1674 ዓ.ም በመንገሥ እስከ 1698 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን አስተዳድረዋል። ጎንደርን ወደ ኃያልነት ዘመኗ ጫፍ ያደረሱ ታላቅ ንጉሥ ነበሩ። ዐፄ ቀዳማዊ እያሱ ከዐፄ  ፋሲለደስ ቀጥሎ በጎንደር ሁለተኛውን ቤተመንግሥት  የገነቡ ባለታሪክ ናቸው። ለኢትዮጵያ እድገት እና ስልጣኔ ቀናኢ የነበሩ እና ታማኝ የሕዝብ አገልጋይ የሆነ ዘመናዊ መንግሥት ለመገንባት በስልጣን ዘመናቸው ሁሉ ጥረዋል። ከጎንደር ነገሥታት ውስጥ  ጠንካራ ከሚባሉት መካከል ተብለው እንደሚጠቀሱም ታሪክ ፀሀፊው አባ ጋስፓረኒ ይጠቁማሉ።  ካለፉት ነገስታቶች የተለዩ የሚያደርጓቸውን አያሌ ስራዎችን ሰርተው ስላለፉት ታላቁ እያሱ ወይም ቀዳማዊ እያሱ በኩር በታሪክ ማህደር ታወሳለች። መልካም ንባብ።

 

ታማኝ መንግሥት ግንባታ

ታላቁ እያሱ መናገሻቸውን ጎንደር በማድረግ ኢትዮጵያን ለ28 ዓመታት ያህል ባስተዳደሩበት ወቅት የተሻለ የመንግሥት ስርዓት በመትከል ለሕዝብ ታማኝ የሆነ መንግሥት ለመገንባት ጥረዋል። በገነቡት አስተዳደራቸው ዝናቸው የገነነ ነበር። ሀቀኛ እና በስርአት የተገነቡ መስመሮችን የሚከተል መንግሥት ፈጥረዋል። ለዚህም በፊት እንደ ሀገሪቱ የሲቪል ሕግ ሆኖ ያገለግል የነበረውን ፍትሀ ነገስትን እንደገና የተከለሰበት እና አዲስ የሀገሪቱ ሕግ በእርሳቸው ዘመን እንደፀደቀ ይነገራል። በመላ ግዛታቸው የሚተገበር የግብር ማሻሻያ አድርገዋል። በተጨማሪም  የሀገሪቱን የንግድ እድገት የጨመረ የኬላ ቀረጥ አዋጅ አውጥተው ወደ ስራ አስገብተዋል። ይህ አዋጅ በቀረጥ እና በግብር የተነሳ ብዙ ብጥብጥ እና ችግር ስለነበር ሕዝባቸው አውቆ እና ወድዶ እንዲገብር የተለያዩ ሕጎችን በአዋጅ አሳውጀዋል። በአንድ አውራጃ አንድ ኬላ እንዲኖር፣ በአምስት በቅሎ ወይም አህያ ጭነት አንድ አሞሌ እንዲከፍል፣ በአምስት ግመል ጭነት ሁለት አሞሌ ጨው እንዲከፈል እንዲሁም በትከሻ የሚነግድ ቀረጥ እንዳይከፍል እና በጎንደር መካከል ያለው የከብት ገበያ ከቀረጥ ነፃ እንዲሆን ለሕዝቡ በአዋጅ አስነግረው ፍትሃዊነትን ለማንገስ ሞክረዋል። ዜጎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ሰርተው እንዲለወጡ መንገዱን በማመቻቸት ንግዱን አነቃቅተዋል። የመገበያያ ዘዴውን ለማሻሻልም በሀገሪቱ ጠፍቶ የነበረውን ገንዘብ ከወርቅ ከነሃስ እና ከብር በስማቸው አስቀር ው ጥቅም ላይ እንዲውል አድርገዋል።

 

የቤተመንግሥት ግንባታ

ጎንደር የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እና የነገሥታት መቀመጫ በነበረችበት ወቅት ነገሥታት የዬራሳቸውን ቤተ መንግሥት ይገነቡ ነበር። የመጀመሪያውን ግዙፍ ቤተመንግስት ከገነቡት ዐፄ ፋሲለደስ ዘመናዊ ሕንፃ በመቀጠል ቀዳማዊ እያሱ ሁለተኛውን ቤተ መንግሥት በጎንደር ከተማ አስገንብተዋል። ምንም እንኳ ቤተ መንግሥቱ ከዐፄ ፋሲሉ ቤተመንግሥት በመጠን ያነሰ ቢሆንም እጅግ የተሻለ ቅንጡ ነበር። በሌላም በኩል በጎንደር ከተማ ያለውን የደብረ ብርሃን ስላሴን ቤተክርስቲያን አስገንብተዋል።

 

የወህኒ አምባ ፍች

አድያም ሰገድ እያሱ ተብለው በ1674 ዓ.ም በአባታቸው ዙፋን ላይ ከነገሡ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ የለውጥ ስራዎችን ከውነዋል። በነገሡ በሦስተኛ ወራቸው ባለፉት ነገሥታት ተጠርጥረው ፀጥታ እንዳያደፈርሱ የተባሉ የነጋሲ ዘሮች ራቅ ብሎ በሚገኘው ወህኒ አምባ እየተወሰዱ ይታሰሩ የነበረበትን ታሪክ በመቀየር ታላቁ እያሱ ፈር ቀደዋል።  ንጉሡ ራሳቸው እስር ቤቱ ድረስ አቅንተው በዚያ የታሰሩ መኳንንቶችን እና መሳፍንት ሁኔታ ጎብኝተው ብቻ ሳይሆን ግብር አብልተው እስረኞችን በሹመት እየሾሙ ካባ እየሸለሙ ስልጣን እየሰጡ ወደ ስራ መልሰዋቸዋል። እርሳቸው በወቅቱ በነበረው ለታሰሩ መኳንንቶች እና መሳፍንት ሹመት ሰጥተው ከእስር በፈቷቸው ወቅት ከእንግዲህ ለስልጣን መጣላትን ትተው ሀገራቸውን በጋራ ለማሳደግ አንዲሰሩ፣ ሕዝባቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ አደራ ሰጥተው የአስተዳደራቸው አካል እንዳደረጓቸው መሪራስ አማን ‘የጥንቷ ኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘ መፅሃፋቸው ላይ አስፍረውታል።

መሪራስ አማን እንደፃፉት ንጉሡ ከተፈቱት መኳንንቶች እና መሳፍንት ምስጋና ድርሷቸዋል፤ “በወህኒ አምባ ታስረን የተረሳነውን፣ ሳንበድል ወንጀል ሳንሰራ በጥርጣሬ ተግዘን የነበርነውን እስረኞች ፈትተህ በዚያም ላይ ሹመህ ሸልመህ ለዚህ ደስታ ስላበቃኸን እግዚአብሔር መንግሥትህን ከልጅ ልጅህ አያውጣው። በሕይወታችን ሙሉ አንተን እና ሕዝብህን እንደምናገለግል ጠላቶችህን እንደምንቀጣ እግዚአብሔር ምስክራችን ይሁን” ብለው በአንድ ሀሳብ አሞግሰዋቸው ነበር። የግዞተኞቹን እጣ ፋንታ ለማሻሻልም ብዙ ጥረዋል።

 

የውጭ ግንኙነት ትንሳኤ

ዐፄ አድያም ሰገድ ወይም ቀዳማዊ እያሱ ከዐፄ ፋሲለደስ ጀምሮ ኢትዮጵያ ትከተል የነበረውን ዝግ የውጭ ፖሊሲ በመለወጥ የቀደሙትን ነገሥታት ፀረ አውሮፓውያን ፖሊሲ እና አቋም ለውጠዋል።   የሀገራቸውን ሕዝብ ለማሰልጠን እና ለማበልፀግ ከውጭ ሀገር  ጥበበኞችን አስመጥተው ሕዝባቸውን እንዲያስተምሩላቸው አድርገዋል።  ይህም ንጉሡን ከዘመኑ የቀደሙ አስተዋይ አስብሏቸዋል። ለዘመናዊነት ባላቸው ቀናኢነት ዳግማዊ ሚኒልክን ይቀድማሉ። በ1685 ዓ.ም የደች ዌስት ኢንዲስ ገዢ በራሱ አነሳሽነት ለደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን የሚሆን የደወል ስጦታ በማበርከት አድናቆቱን ገልፆላቸው ነበር።

ተቋርጦ የቆየውን የውጭ ሀገር ግንኙነት በማሻሻል ከፈረንሳይ ጋር ከሊውስ 14ኛ ጋር የባህር ኃይል እና የመርከብ ስራ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ለማስገባት ውል ተፈራርመው ነበር። በተመሳሳይም ከስፔን እና ከሆላንድ መንግሥታት ጋር የቃል ንግግሮችን ጀምረው የሆድ በሽታ እንደፀናባቸው ይነገራል። የንጉሡን የቆዳ ሕመም ለማከም ከፈረንሳይ ዶክተር ሸርል ጃክ ፖንሴ በጎንደር ቤተመንግሥት ተቀብለውታል። በተጨማሪም ከቱርክ ሀድ አሊ አቡበክር መጥቶ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።

“ንጉሡ ግሩም ብቃቶች አሏቸው።  ቀልድና ቁም ነገርን የመናገር ችሎታ አላቸው። ጣፋጭ እና የሚወደድ ለዛ እና የጀግና ቁመና አላቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ካየኋቸው እጅግ መልከ ቀና ናቸው። በየጦር ሜዳዎች እጅግ ደፋር እና አይሸነፌ ናቸው። የተለየ የፍትህ ፍቅር አላቸው። ለዜጎቻቸው ፍትህ በታላቅ ፍፅምና እንዲሰጣቸው ያደርጋሉ። ይህም ተወዳጅ አድርጓቸዋል። “ በማለት ማስታወሻ አስቀምጦ አልፏል።

በአጠቃላይ ታላቁ እያሱ ኢትዮጵያውን ከዳር እስከ ዳር በአንድነት አክብረው የተገዙላቸው ታላቅ ንጉሥ ነበሩ። በባህሪያቸው የተወደዱ አስተዋይ መሪ መሆናቸውንም ታሪክ ያወሳላቸዋል። እኛም በዚሁ አበቃን።

 

ሳምንቱ በታሪክ     

 

ንግሥት ኤልሳቤት

ቀዳማዊት ንግሥት ኤልሳቤት በ26 ዓመት እድሜያቸው በእንግሊዝ ዙፋን ላይ ኅዳር 8 ቀን 1550 ዓ.ም ተቀመጡ።  ንግሥት ኤልዛቤት እስከ 1595 ዓ.ም በእንግሊዝ ዙፋን ላይ በመግዛት እስከ 69ኛው እድሜያቸው ቆይተዋል። በቀዳማዊት ኤልሳቤት ዘመን እንግሊዝ የዓለማችን ኃያል ለመሆን በቅታለች።  የስነፅሁፍ ወርቃማው ዘመን የሚባልለት እንደ እነ ሸክስፒር እና እንደ ኤድመንድ ስፔንሰር ያሉ ጉምቱ ፀሀፍት የበቀሉበት ዘመን እንደነበርም ታሪክ ዋቢ ነው። ምንጭ-ሂሰትሪፕሌስ ዶት ኮም

 

አዋጅ  ለጎጃም ሕዝብ

ኢትዮጵያ በጣሊያን በተወረረችበት ወቅት ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለሊግ ኤፍ ኔሽንስ አቤቱታ ለማሰማት በስደት ቆዩ። ከዚያም በኋላ ከእንግሊዝ መንግስት ድጋፍ በማግኘት ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ እያሉ ለየክፍለ ሀገሩ ሕዝብ ከላኳቸው መልእክቶች ውስጥ አንዱ ለጎጃም ሕዝብ የተላከው አዋጅ ነበር።  አዋጁ ህዳር 9 ቀን 1933 ዓ.ም ተፃፈ::

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ አዋጅ ለጎጃም ሕዝብ ሲል ይጀምራል::

እውነተኛነቴን  ቃሌም የማይታበል መሆኑን ታውቃላችሁ። በኢጣሊያኖች ላይ የምትነሱበት ጊዜ ደርሷል። ይኸውም እንግዲህ ታላቂቱ እንግሊዝ እርዳታዋን ልታደርግልን ነው። ስለዚህ በትዕግስት ጠብቁ፣ ኃይላችንንም ከሚመጣው ክረምት በፊት ታዩታላችሁ።  እስካሁን ድረስ በጀግንነት ሲመራችሁ የቆየውን ደጃዝማች መንገሻ ጀምበሬን አሁን ለጊዜው ራስ ብለን ሾመነዋል። ኢጣሊያኖችን ድል ካደረግን በኋላ ዘውድ ሰጥተን በሙሉ ጎጃም ላይ እንሾመዋለን። ኢትዮጵያ በነፃነቷ ለዘላለም ትኑር!

ታላቂቱ ብሪታንያ ለዘላለም ትኑር!

ኅዳር 9 ቀን 1933 ዓ.ም የሚል ነበር።

 

ምንጭ፦ የታሪክ ማስታወሻ፣ ከደጃዝማች ከበደ ተሰማ

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የህዳር  8 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here