ታላቁ የቮሊቦል ባለሙያ

0
74

ከሀገር ውጪ የቮሊቦል ብሄራዊ ቡድን ያሰለጠነ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነው፤ ከአንጋፋው ዓለም አቀፍ ኢንስትራክተር አለማየሁ ሸዋታጠቅ ቀጥሎ በሀገራችን በዘርፉ ሁለተኛው የቮሊቦል ኢንስትራክተር ነው። በተጫዋችነት ዘመኑ የምስራቅ እና የመካከለኛው አፍሪካ አራት የቮሊቦል ዋንጫዎችን በማንሳት  እስካሁን ቀዳሚ ሰው ነው፤ በኢትዮጵያ ታላላቅ የቮሊቦል ክለቦችን አሰልጥኗል። በአሁኑ ሰዓት ሦስተኛ ደረጃ የቮሊቦል አሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት ያለው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ነው፤ አሁንም ለቮሊቦል ስፖርት የማይቀዘቅዝ ፍቅር እና ስሜት አለው- ኢንስትራክተር አማኑኤል ኢሳያስ።

 

ኢንስትራክተር አማኑኤል ኢሳያስ በተጫዋችነት ዘመኑ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጪም ተጫውቶ አሳልፏል። በአሰልጣኝነት ዘመኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለሦስት ዓመታት ያህል አገልግሏል። ከሀገር ውስጥ ወላይታ ዲቻን፣ ሙገርን እና ብሄራዊ አልኮል የቮሊቦል ክለቦችን ማሰልጠኑ አይዘነጋም። ወደ ታንዛኒያ አቅንቶ ሁሉንም የብሄራዊ ቡድኖች፣  ቲፐር እና ሜትሮ የተባሉ የቮሊቦል ክለቦችንም ማሰልጠኑን የግል የታሪክ ማህደሩ ያስነብባል፡፡

 

በኢትዮጵያ የቮሊቦል ስፖርት ታሪክ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሁለት የቮሊቦል ኢንስትራክተሮች ስማቸው ተመዝግቧል። የመጀመሪያው የቮሊቦል ኢንስትራክተር አለማየሁ ሸዋታጠቅ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኢንስትራክተር አማኑኤል ኢሳያስ መሆኑን የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አመልክቷል። የመጀመሪያ ደረጃ  የአሰልጣኞች ስልጠናን በታንዛኒያ፣ ሁለተኛ ደረጃን በቦትስዋና እና ሦስተኛውን በግብጽ ስልጠናዎችን መውሰዱን ተናግሯል። ሁሉንም ስልጠናዎች ያለምንም እገዛ በራሱ ተነሳሽነት በግሉ መውሰዱን ያስረዳል። የቮሊቦል ስፖርትን ገና መጫወት ሲጀምር ታላቅ አሰልጣኝ የመሆን ህልም የነበረው ኢንስትራክተር አማኑኤል ኢሳያስ አሁን ላይ ተሳክቶለት ውጤታማ ከሆኑ የቮሊቦል ባለሙያዎች በቀዳሚነት ስሙ ይቀመጣል።

 

አሰልጣኙ በአርባምንጭ ከተማ ነው ተወልዶ ያደገው። ባደገበት የአርባምንጭ ከተማም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ ከቮሊቦል ስፖርት ጋር መተዋወቁን ከአሚኮ በኵር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል። በ1980 ዓ.ም በሀገር አቀፉ የቮሊቦል ሻምፒዮና ላይ ጋሞ ጎፋ ዞንን ወክሎ በመጫወት ባለተሰጥኦ መሆኑን አስመስክሯል።

የቀድሞው ተጫዋች በወቅቱ  በተለያዪ ክለቦች ዕይታ ውስጥ ቢገባም ከአንድ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ቡና የቮሊቦል ክለብ መዳረሻው ሆኗል። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ድንቅ ጊዜያትን ያሳለፈው ተጫዋቹ ሦስት የምስራቅ እና የመካከለኛው የአፍሪካ ቮሊቦል ዋንጫ እና በሀገር ውስጥም ሦስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎች አንስቷል።  በቡናማዎቹ ቤት ባሳየው ድንቅ ብቃት በዚሁ ዓመት ለወጣቶች የቮሊቦል ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦለታል። ታዲያ አማኑኤል ኢሳያስ ለአፍሪካ ቮሊቦል ሻምፒዮና ከዋናው የቮሊቦል ብሄራዊ ቡድን ጋር ወደ ዛምቢያ በመጓዝ ከዋንጫ ጋር መመለሳቸውን ያስታውሳል።

 

በ1984 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡና የቮሊቦል ክለብ በመድረኩ አልሳተፍም ማለቱን ተከትሎ እርሱን ተክቶ ውኃ ሥራዎች ድርጅት የቮሊቦል ክለብ እንዲሳተፍ ተደርጓል። ኡጋንዳ በነበረው ውድድርም ውኃ ሥራዎች ድርጅት አማኑኤል ኢሳያስን ጨምሮ ሌሎችንም ተጫዋቾች ወደ ቦታው ይዞ አቅንቷል። ታዲያ ከኢትዮጵያው ተወካይ ክለብ  ጋርም ዋንጫን ማሳካት ችሏል።

 

ከውድድሩ በኋላ የውኃ ሥራዎች ድርጅት የቮሊቦል ክለብ የቡድን አባላት ወደ እናት ሀገራቸው ሲመለሱ ለቡደኑ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው አማኑኤል ኢሳያስ ግን  ከታንዛኒያው ክለብ ቲፐር ጋር መፈራረሙን ተከትሎ በዚያው ቀርቷል። በአጭር ጊዜ ውስጥም በአዲሱ ክለቡ ተጽእኖ ፈጣሪ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል። በቲፐር ክለብ እየተጫወተ ጎን ለጎን የአሰልጣኞች ስልጠና በመወስደ ራሱን ለቀጣይ ህይወቱ አዘጋጅቷል። ብዙም ሳይቆይ ቲፐርን ተጫዋች እና አሰልጣኝ ሆኖ በማገልገል የአሰልጣኝነት ህይወቱን ጀምሯል።

በአጠቃላይ በታንዛኒያው ክለብ ቲፐር አምስት ዓመታት አሰልጥኗል።  በቲፐር ቆይታውም የተለያዩ ዋንጫዎችን አሳክቷል። የታንዛኒያ ብሄራዊ የቮሊቦል ሊግ፣ የምስራቅ እና የመካከለኛው የቮሊቦል ሻምፒዮና፣ የቦኒፌካፕ (የጎረቤት ሀገራት ክለቦች የሚሳተፉበት) እንዲሁም የኬሌሙ ውድድር ዋንጫን አሳክቷል። ከቡድን ሽልማት በተጫማሪ በግሉም የተለያዩ ሽልማቶችን ያሸነፈ ሲሆን የብሄራዊ ሊጉ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋችነትን እና ሌሎችንም ክብሮች ተቀዳጅቷል።

 

በ1992 ዓ.ም የታንዛኒያ ወንዶች ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን በይፋ አሰልጣኝ ሆኖ ተቀጥሯል። በጊዜው ታንዛኒያ በአፍሪካ የቮሊቦል መድረክ መሳተፍ የጀመረችበት ወቅት ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ወደ ሀገሩ በመመለስ ወላይታ ዲቻን በመረከብ ለክለቡ የመጀመሪያውን ዋንጫ ማሳካት ችሏል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ስፖርቱን እስከ ማቆም የተገደደበት አስቸጋሪ ጊዜያትን አሳልፏል።

 

ወደ ትውልድ መንደሩ አርባምንጭ በመጓዝ ከስፖርቱ ጋር እስከመለያየት ደርሷል። በቮሊቦል ስፖርት ምክንያት በቤተሰቦቹ ሳይቀር ተገፍቷል። ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ የቮሊቦል ስፖርት ህይወቱ አልጋ ባልጋ እንዳልነበረ የተናገረው አሰልጣኙ ብዙዎችም ዘርፉን ትቶ ወደ ሌላ ሙያ ፊቱን እንዲያዞር ይጎተጉቱት ነበር። በ2007 ዓ.ም ግን ድጋሚ ወደ ስፖርቱ በመመለስ ወላይታ ዲቻ የቮሊቦል ክለብን በመረከብ ለሦስት ዓመታት ያህል አሰልጥኗል። በወላይታ ዲቻ ቆይታውም ክለቡ ሁለተኛውን የደርባ ሜድሮክ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን እንዲያሳካ አድርጎታል። ከዚያም ሙገር የቮሊቦል ክለብን በመቀላቀል ለአንድ ዓመት ያህል በአሰልጣኝነት አሳልፏል። በሙገር ቤት ክለቡን እንደገና በወጣቶች የማዋቀር ዕቅዱ በክለቡ የቀድሞ አመራሮች ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከአንድ ዓመት በላይ መቆየት አልቻለም።

 

እናም ወደ ብሄራዊ አልኮል የቮሊቦል ክለብ በማቅናት ለሁለት ዓመታት ያህል በአሰልጣኝነት መቆየቱን አስታውሶናል። ይሁን እንጂ ልክ እንደ ሙገር በብሄራዊ አልኮል ቤትም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ዋንጫ ሳያሳካ ከቮሊቦል ክለቡ ጋር ተለያይቷል። በአሰልጣኝነት ህይወቱ በብሄራዊ አልኮል ያሳለፋቸው ሁለት ዓመታት ለእርሱ አስቸጋሪ ጊዜያት እንደነበሩ የቮሊቦል አሰልጣኙ  ያስታውሳል። “በወቅቱ በክለቡ ውስጥ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት የነበረ በመሆኑ ተጫዋቾች ሳይቀር በጽኑ የተፈተኑበት ነበር” ብሏል።

አርአያዬ ኢንስትራክተር አለማየሁ ነው የሚለው የቮሊቦል አሰልጣኙ በእድሜ ዘመኑ ለመማር ያለው ዝግጁነት እና ጽናት ስኬታማ እንዲሆን አስችሎታል። በየጊዜው ራሱን በማብቃት በአፍሪካ ደረጃ ካሉ ምርጥ የቮሊቦል ባለሙያዎች ተርታ ራሱን አስመዝግቧል። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ስፖርት አሠራር ኢንስትራክተር መሆን ብቻውን ለውጥ አያመጣም ያለው አሰልጣኙ የፌዴሬሽኑን ይሁንታ ካገኘ ግን ወጣቶች ላይ መሥራት የዘወትር ህልሙ መሆኑን አስረድቷል።

 

እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ የቮሊቦል ስፖርት እንደ ቀደሙት ዓመታት የተሻለ እንዲሆን አሰልጣኞችን ማብቃት ሌላኛው ዕቅዱ ነው። በሌላው ዓለም ላይ ያሉ ዓይነት ተጫዋቾች ኢትዮጵያም ሊኖራት ይገባል ያለው አሰልጣኙ  ይሄን ለማድረግ ደግሞ መንገዱን ማሳየት እንዳለበት ያምናል። ይህን ለማድረግ ግን ዕድሉን ባለማግኘቱ አሁን ላይ ወደ ታንዛኒያ ማምራቱንም አልሸሸገም። በሀገሬ እንድሰራ እድል አልተሰጠኝም የሚለው ኢንስትራክተር  አማኑኤል አሁን ላይ የታንዛኒያውን ክለብ ለአንድ ዓመት ለማሰልጠን ተስማምቷል። የታንዛኒያ የወንዶችን፣ የሴቶችን እና የወጣቶችን የቮሊቦል ቡድኖችን የሚያሰለጥን ይሆናል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here