ያለንበት ወቅት የክረምቱን መውጣት ተከትሎ እንደወረርሽኝ እየተነሳ ባለ ወባ፣ አየሩ በተቀያየረ ቁጥር እየተነሳ ብቻ ሳይሆን ደጋግሞ እያገረሸ በሚመጣ ኮረና መሰል ከባድ ጉንፋን እንዲሁም አተት እና ኮሌራ በመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች እየተፈተንን ያለንበት በመሆኑ የዛሬ መጣጥፌን ጤና ይስጥልኝ! በሚለው የመልካም ምኞት መግለጫ ሰላምታ እንድጀምር ግድ ብሎኛል፤ ጤና ይስጥልን የበኩር ታዳሚያን!እንዴት ሰነበታችሁ? ሰላም፣ ፍቅር እና ጤና ከእናንተ ጋር ይሁንና ኑሮ እንዴት ይዟችኋል?
የኑሮ ውድነቱ እየፈተነን ባለበት በዚህ ዘመን እንደወረርሽኝ እየተነሱ በጅምላ በሚደቁሱን ተላላፊ ደዌያት ላይ የመድሀኒት እጦት /ተደራሽ አለመሆንና/ የዋጋው ንረት ሲታከልባቸው ኑሯችንን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዳደረጉብን ለማስረዳት መሞከር ለቀባሪ ማርዳት ይሆናልና ልለፈው::
ግን ደግሞ ችግሩ አሳሳቢ እና ጊዜ የማይሰጠው ከመሆኑ አንፃር በተለይ በአማራ ክልል የጤና ተቋሞቻቸው በጦርነት በወደሙባቸው በርካታ ወረዳዎች ለሚኖረው ሰፊ ህዝብ መድሃኒት እና የህክምና ቁሳቁስ የማቅረብ ሀላፊት ላለባቸው የጤና ጥበቃ ተቋማት ችግሩ ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን መጠቆም፣ ማሳሰብ እና መቀስቀስ ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባ ይሰማኛል::
ይኸው መሠረታዊ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ማህበረሰቡ ራሱ በሽታን አስቀድሞ ከመከላከል ይልቅ ለህመም እና ለወረርሽኝ የሚዳርጉ ያልተገቡ ተግባራትን ሲፈፅም ይስተዋላል እና እነዚህኑ ትዝብቶቼን በማንሳት በያለንበት እንድንወያይ እና ራሳችንን ከበሽታ በመከላከል በኩል የሚቻለንን ሁሉ እንድንወጣ ለማነሳሳት እንደአብነት ባህርዳር ከተማ ውስጥ ያስተዋልኳቸውን ፅዳት ነክ ችግሮች እንደማሳያ እጠቅሳለሁ::
የፅዳት አለመኖር ችግር በግለሰብ እና እንደማህበረሰብ በአካባቢም የሚፈጠር ነው:: የመተንፈሻ አካላትን የሚያውከውን ጉንፋንን ጨምሮ ተላላፊዎቹ ታይፎይድ እና ታይፈስ የተሰኙ በሽታዎች ዋነኛ መንስኤም ይኸው የግል እና የአካባቢ ፅዳት ጉድለት ነው::
ጉድለቱ በተለይ አካባቢን የሚበክለው የፅዳት መጓደል በአብዛኛው የሚፈጠረው ህዝብ በሚበዛባቸው ከተሞች ሲሆን በነዚህ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ በመጠጥ ቤቶች አካባቢ በየግድግዳው፣ በየአጥሩ እና በየዛፉ ስር መሸተኞች በግዴለሽነት የሚፀዳዱት ሽንት አንደኛው በካይ ቆሻሻ ነው:: ስፍራዎቹ መንገድ ዳር በመሆናቸው የተነሳ አላፊ አግዳሚን የሚበክሉ መሆኑ አያጠያይቅምና ከሁሉም በፊት ቆሻሻውን እየፈጠርን ያለን ወንዶች ያለንበትን የሰለጠነ ዘመን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ጦሱ ለሁላችንም የሚተርፍ መሆኑንም በመገንዘብ ይህንኑ ፀያፍ ባህሪ ልናርም ይገባል::
በዚህ ረገድ የመጠጥ ቤቶቹ ባለቤቶችም መፀዳጃ ቤት ማዘጋጀት ግድ መሆኑን ተገንዝበው ማዘጋጀት እና መፀዳጃ ቤት እያለ መንገድ ላይ የመጠቀም አባዜ ያለባቸውን ተጠቃሚዎችም መከልከል፣ ማረም እና የሚጠቀሙበትን ስፍራ አበባና አትክልት በመትከል ልማዱ እስኪተዋቸው በጥበቃ መከላከል ተገቢ ነው እላለሁ::
ከፅዳች ችግር ሳንወጣ ሌላው ዋነኛ ችግር ከአንዳንድ ማህበራዊ ሀላፊነት የጐደላቸው ተቋማት ወደ ጐርፍ ማፋሰሻ ቦዮች የሚለቀቅ ፍሳሽ ቆሻሻ ነው::
ለድርጅቶቹ ስም እና ዝና ሲባል አሁን ስማቸውን መጥቀስ ያልፈልግኳቸው ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ድርጅቶች ውጋጁን በራሳቸው “ሴፍቲ ታንክ” የሚባለው ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ውስጥ መያዝ ሲጠበቅባቸው ከከተሞቹ የጐርፍ ማስወገጃ ቦይ ጋር ውስጥ ለውስጥ እያገናኙ መልቀቃቸው ነው ችግሩ:: በእነዚሁ አካባቢዎች አልፎ ለመሄድ የሚቸገረው እና አፍንጫውን እያፈነ ለአስም ተዳረግን በሚል የሚያማርር ብቻ ሳይሆን ለጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት ፅዳት ተቆጣጣሪዎች ጥቆማ የሚሰጠው ኗሪ ብዙ ቢሆንም ችግሮቹ ግን ሲወገዱ አይታይም:: ይህንን ችግር በመፍታት በኩል በዋናነት ማዘጋጃ ቤት እና ጤና ጥበቃ ባለሙያዎች ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል::
በየአካባቢው የሚገኙ ኗሪዎችም በጋራ እየወጡ መብታቸውን ማስከበር ይጠበቅባቸዋል ባይ ነኝ!
ከፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች የሚፈጠርን የበሽታ መንስኤ የሚያመጣው ሌላው ችግር ያገለገሉ ቁሶችን መፋሰሻ ቦዮች ላይ መጣላችን ነው::
የየከተሞቻችን የከተማ አገልግሎት ጽ/ቤቶች (ማዘጋጃ ቤቶች) ደረቅ ቆሻሻን ማስወገጃ መዋቅር ዘርግተው፣ ማህበራትን አደራጅተው፣ ቁስ አሟልተው እየሠሩ መሆኑ እየታወቀ ብዙዎቻችን ግን ቆሻሻውን በጆንያ አጠራቅሞ ማቆየት እና መላክ ሲቻል በየጐዳናውና በየቦዩ ጨለማን ተገን እያደረግን አንዳዶቻችን ደግሞ በግላጭ ጭምር ቆሻሻ እየጣልን አካባቢን ስንበክል እንታያለን::
በዚህ ረገድ በተለይ በጐዳና ላይ ንግድ የተሰማራን ወገኖች በአካባቢ ብክለት ግንባር ቀደም ነን::
በጣም ጥቂት የሚባሉ ጨዋ ሰዎች ከሚሸጡት እና ከሚገዟቸው ምርቶች የሚገኙ ማሸጊያ ኘላስቲክ፣ ልጣጭ እና ቅርፊት የመሳሰሉ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ሰብስበው ለደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ በተዘጋጀ ገንዳና ጆንያ ውስጥ የሚያስቀምጡ ቢሆንም ብዙዎቻችን ግን ለዚህ የታደልን አይደለንም::
ድንች እና እንቁላል ቅቅል፣ ሸንኮራ አገዳ እና ሙዝ የሚሸጡባቸውን ጐዳናዎች እስኪ ልብ በሉ! ግብር በማንከፍልበት፣ ኪራይ በማንጠየቅበት ሥፍራ መነገዳችንን እንደመልካም አጋጣሚ ወስደን ቢያንስ ቅሬቱን በጆንያ ልንሰበስብ ሲገባ አሰፖልቱን ሁሉ የልጣጭ ቆሻሻ ማስወገጃ ገንዳ እያስመሰልነው እንገኛለንና ስቅቅ ሊለን ይገባል::
የኛው ቆሻሻ በሂደት ወደ አቧራነት እየተቀየረ ለጉንፋን ሲዳርገን፣ መፋሰሻ ቦዮችን እየዘጋ በሚያቁረው ውሃ የወባ መራቢያ ሆኖ ለወረርሽኝ ሲያጋልጠን ኋላ ላይ መንጫጫት ምን ይረባል? “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚለውን የአበው ወርቃማ ብሂል የምንጠቀምበትስ መቼ ነው?
ይኸው የቆሻሻ አወጋገድ ችግር በጐዳና ላይ ብቻ የተወሰነም አይደለም:: እስኪ አመት በዓል በመጣ ቁጥር የዚያን ሰሞን የሰፈራችን ጠረን ለማስታወስ ሞክሩ! በየቤታችን ከምንፈፅመው እርድ የሚገኝን ውጋጅ ከላቫ እስከ አጥንት፣ ከፈርስ እስከ አንጀት፣ ከቆዳ እስከ ጭንቅላት ግቢአችን ውስጥ ጉድጓድ ቆፍረን መቅበር አለያም በየከተማችን የቆሻሻ ማስወገጃ መዋቅር በኩል ማስወገድ እየተቻለ ከግቢያችን ውጪ በየጥጋጥጉ አይደለም እንዴ የምንጥለው?! ከአጥር ጊቢአችን ውጪ ያለው ጐዳና የእኛ አይደለም ወይ? ውሎ ሲያድር የሚፈጥረው መጥፎ ጠረንስ እንዴት ይዘነጋናል! ይኼ ከግቢዬ ከወጣ ምን አገባኝ አይነት አመላካከት በተለይ ለአንድ የከተማ ኗሪ የሚመጥን አይደለምና፤ ከማህበራዊ ህይወት የሚያወጣ ብቻ ሳይሆን ለመናቅም ይዳርጋልና “ሁሉም አካባቢውን ቢያፀዳ አለም ትፀዳለች” ለሚለው ብሂል መገዛት መልካም ነው እላለሁ::
ራሳችን በምንፈጥራቸው ቆሻሻዎች ሳቢያ ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጥን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሽታ ሲገጥመን ቶሎ ለማጽዳት እና ሌሎችን ላለመበከል የምናደርገው ጥረትም እጅግ ደካማ እንደሆነ ታዝቤአለሁ::
ለአብነት ያህል ኮረና የተባለው ወረርሽኝ በተከሰተ ጊዜ ጭምብል እና ሳኒታይዘርን በመጠቀም የስርጭቱን መጠን በመግታት በኩል ጥሩ ጥረት ማድረጋችን ይታወቃል:: ታዲያ እንዲህ አይነት ጥሩ ተሞክሮ ካለን ዛሬ ኮረናን መሠል ኃይለኛ የጉንፋን ወረርሽኝ ሲከሰት መጠቀም የማንፈቅደው ለምንድን ነው? እነዚህን ቁሶች ባንጠቀም እነኳ ዘመድ፣ ጓደኛ ወይም ባልደረባ ጋር ስንገናኛ “ይቅርታ ጉንፋን ይዞኛል ሰላም አልልህም፤ ራቅ በል… ማለት ማንን ገደለ? የስጦታ መልካም ሽቶ ይዞ እንደመጣ ሰው አፍንጫና ከንፈርን ሲፈትጉ በዋሉበት መዳፍ አፈፍ እያረጉ ጉንጭ ለጉንጭ መሳሳም ምን ይሉታል?
ታይፈስ እና ታይፎይድ፣ ጉንፋን እና ኮረና፣ አተት በሉት ኮሌራ በትንፋሽ እና በንክኪ እንደሚዛመቱ በተለይ ለከተማ ኗሪ የተሰወረ አይደለምና በእነዚሁ በሽታዎች በተጠቃን ጊዜ ቶሎ በመታከም እና በመኖሪያ ቤታችን እየተወሰንን ንክኪን ባለመፍጠር ሌሎችን ከብክለት እና ወረርሽኝ መታደግ አስፈላጊ ነው:: ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት የሚባለውም ይኸው ነው::
አሁን ባለንበት ዘመን ቆሻሻን በማስወገድ፣ የአካባቢን ንፅህና በመጠበቅ እና ውብና ማራኪ መንደሮችንና ከተሞች ከመፍጠር አኳያ በተለይ በከተሞች አካባቢ ከመንግሥታዊ ተቋማት ይልቅ የእኛ የኗሪዎች ድክመት ጐልቶ ታይቶኛልና ለግል እና ለአካባቢ ፅዳት ትኩረት ሰጥተን ለእኛው ጤንነት እኛው ዋስትና አንሁን እላለሁ::
በቀላሉ ወደ አፈረነት የማይቀየሩ የኘላስቲክ ዕቃ መጠቅለያዎች አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ ህግ እስከማውጣት በዘለቀ ትኩረት ሃገሩን ንፁህና ተመራጭ የቱሪስት መነሀሪያ ማድረግ ከቻለው የኡጋንዳ መንግሥት መልካም ተሞክሮ በመቅሰም በኩል መንግሥት፣ አካባቢ መበከል ነውር ነው በሚል የማስቲካ ሽፋን እንኳን በኪሱ አቆይቶ ቅርጫት ውስጥ የማስቀመጥ ድንቅ ልማድ ካለው የአስመራ ከተማ ኗሪ ደግሞ እኛ ጐረቤቶቻቸው ተሞክሯቸውን መቅሰም ብልህነት ነው::
በአጠቃላይ ታሞ መዳን የሚናፍቅበት ጊዜ እና ዘመን እንዳይመጣ የግል እና የአካባቢ ንፅህናን ከመጠበቅ ጀምሮ ከመታከም በፊት በሽታን ለመከላከል እንረባረብ እላለሁ:: ሠላምና ጤና ለእናንተ ይሁን!
(ጌታቸው ፈንቴ)
በኲር ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም