ታሪክ በበኲር

0
249

በኲር በቋሚነት ሳምንታዊ ጋዜጣ በመሆን መታተም የጀመረችው ታህሣሥ 7 ቀን 1987 ዓ.ም ነው። በወቅቱ ስምንት ገጾች እንዲሁም ከዜና ገጽ በተጨማሪ “ትኩረት”፣ “ማኅበራዊ”፣ “ዐውደ ባህል”፣ “ከልማት ዙሪያ” እንዲሁም “ስፖርት” የተሰኙ አምዶች ነበሯት፡፡

በኲር የግዕዝ ቃል ነው፡፡ የቃሉ ትርጓሜ የመጀመሪያ ማለት ሲሆን የክልሉ የመጀመሪያ ጋዜጣ መሆኗን ለመግለፅ ታስቦ ስያሜዋ እንደተሰጣት  ይነገራል። ጋዜጠኛ መዝሙር ኃዋዝ “የብዙኃን መገናኛ እድገት” በተሰኘዉ መፅሐፉ  እንደገለጸው በኲር ለክልሉም ለኢትዮጵያም የመጀመሪያዋ ክልላዊ ጋዜጣ ናት።

በኲር ጋዜጣ መታተም ከጀመረች ከሦስት ወራት በኋላ በኲር  የተሰኘ መፅሔት ይታተም እንደነበር መዝሙር በመፅሐፉ አስፍሮት ይገኛል። መፅሔቱ መጋቢት 1987 ዓ.ም. በወርኃዊነት መታተም ሲጀምር “ልማት”፣ “አተያይ”፣ “ካነበብነው ከሰማነው”፣ “ገፀ ሕግ”፣ “ባህል”፣”እናስተዋውቃችሁ”፣ “ሰውና ኑሮው” እንዲሁም “ኪነ ጥበብ” የሚሉ አምዶች ነበሩት፡፡

በኲር መፅሔት ልሣን የሚባል መፅሔት በአማራ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ በ995 መታተም ሲጀምር ድግግሞሽን ለማስቀረት በሚል ከሕትመት ውጪ ሆኗል፡፡

ሆኖም ሳምንታዊዋ በኲር ጋዜጣ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ የታሪክ ኩነቶችን በመዘገብ ለ30 ዓመታት ዘልቃለች። ዋና ትኩረቷ  ክልላዊ የልማት ክንዋኔዎችን መዘገብ ቢሆንም እግረ መንገድ ግን ለታሪክ ሽፋን የምትሰጥባቸው ሁኔታዎች ነበሩ። በርግጥ እንደተጀመረች ለባህል እና ለስፖርት የየራሳቸው አምድ ተሰጥቷቸው ቋሚ ሽፋን እንዲያገኙ ከመደረጉም ባለፈ ራሱን ችሎ ለታሪክ የተከፈተ አምድ ባይኖርም ባህል በሚል አምዷ ላይ ታሪካዊ ስፍራዎች እና ታሪካዊ ቅርሶች ሽፋን ይሰጣቸው ነበር። በክልሉ የሚገኙ እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት እና ሌሎች ገዳማት እንዲሁም መስጅዶች ታሪካዊ እና ሀይማኖታዊ እንድምታቸውን በሚያሳይ አግባብ ይዘገቡ ነበር።

ኪነ ጥበባት እና ካነበብነው ከሰማነው በተሰኙት አምዶች እንደየቀረቤታው ታሪክ ይዘገብ ነበር። ለአብነት በ1993 ዓ.ም የካቲት ቅፅ 5 ህትመት ላይ “የአረብ ሴቶች በለውጥ ማእበል ውስጥ” በሚል ርእስ የአረብ ሴቶች በአረቡ ዓለም የነበረባቸውን ጫና እና አሁን አሁን ያን ታሪክ የሚቀይሩ ቀንዲሎችን እንቅስቃሴ እና ትሩፋቶቻቸውን ለመዳሰስ የተሞከረበትን ዘገባ እናገኛለን። በዚህ ዓምድ ውስጥ በርካታ ጉዳዮች የተዳሰሱ ሲሆን በተለይ ለኢትዮጵያ ቅርበት ያላቸው እና ማህበራዊ ፋይዳቸው ጠንካራ የሆኑ የታሪክ ክስተቶች ይዳሰሱ እንደነበር ለማየት ተሞክሯል።

ከዓለም ዙሪያ እና ታላላቅ ሰዎች በሚሉ አምዶች ታሪክ ሠሪ፣ እውቅ እና ታላላቅ ሰዎች ይስተናገዱ ነበር። በዓለም ተፅእኖ ፈጣሪ ከሚባሉት ከየዘርፉ ልዩ አበርክቶ ያላቸው የአስር ሰዎች ታሪክ ቀርቧል፤ ከሳይንሱ ጋሊሊዮ ጋሊሊ፣ ከህትመቱ ጉተንበርግ፣  ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ማህተመ ጋንዲ እና ሌሎቹም ታሪካቸው እና አስተዋፅዋቸው ሽፋን አግኝቷል።

ኢትዮጵያ አዲሱን ሁለት ሺህ ዓመት ስትቀበል በኲር ጋዜጣ ከዋዜማው ጀምሮ ልዩ እትሞችን ማውጣት የጀመረችበት አዲስ ምእራፍ ነበር ማለት ይቻላል። በዚህ አጋጣሚ ከሺህ ዓመቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሀገራዊ የታሪክ እውነታዎች የሚስተናገዱበት እድል በመገኘቱ ብዙ ታሪክ ነክ መጣጥፎች ተዘጋጅተዋል። ለአብነት “ኢትዮጵያ እና ሚሌኒየሞቿ” በሚል ርዕስ የሦስቱን የየራሳቸውን ሺህ ዓመት የከፈቱ ትውልዶች እና ያሳረፏቸው የታሪክ አሻራዎች በየሺህ ዓመታቱ ለማሳየት የተሞከረበት ዘገባ ይጠቀሳል። የኢትዮጵያ የንግድ ግንኙነት ታሪክ፣ ያለፉት ሺህ ዓመታት ታላላቅ ነገሥታት እና ንግሥታት ሽፋን አግኝተዋል።

ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ግን በኲር ማሻሻያ ስታደርግ ታሪክን ታሳቢ ያደረገች ይመስላል፤ ጥቂትም ቢሆን የሆነ ጥግ ሰጥታለች። በመሆኑም ሳምንቱ በታሪክ በሚል ገጿ የተለያዩ ሀገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ክስተቶች በመጠኑ መስተናገድ የጀመሩበት ሁኔታ እንዳለ መረዳት ይታያል። ለአብነት ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም  የወጣችውን የበኲር ህትመት ብናነሳ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመኗ ፖትስዳም ከተማ የሦስቱ ኃያላን ሀገራት መሪዎች ያደረጉትን ታሪካዊ ስብሰባ ለማውሳት ተሞክሯል። የእንግሊዙ ዊንስተን ቸርችል፣ የአሜሪካው ሀሪ ትሩማን እና የሶቭየት ሩሲያው ስታሊን የተሰበሰቡበት በስፋት “ፖትስዳም ኮንፈረንስ” እየተባለ የሚታወቀው ጉባኤ ሲሆን ጦርነቱን ለማጠናቀቅ ወሳኝ ውሳኔዎች ያለፉበት ነበር። በዚያው አምድ ውስጥ የመጨረሻውን ንጉሣዊ አገዛዝ ስላስወገደው የ1950 ዓ.ም  የኢራቅ መፈንቅለ መንግሥት  ሽፋን ሰጥታለች። በሌላም በኩል “የአፖሎ 11” የጨረቃ ጉዞ ተስተናግዶ እንደነበር የቆዩ እትሞቿን ስናገላብጥ አግኝተናል።

ከዚያ በኋላ ግን ታሪክ ራሱን ችሎ ሙሉ ዓምድ እንዲኖረው የተደረገበት ለውጥ በጋዜጣዋ የእድገት ጉዞ ውስጥ ተከስቷል። ለምሳሌ የ2010 ዓ.ም እትምን ለአብነት ብንወስድ “ጥንታዊት ኢትዮጵያ እና ስልጣኔ” በሚል ርእስ የበኲር የታሪክ አምድ ሰፊ የታሪክ ዳሰሳ አስነብቧል። ከአክሱም እስከ ዘመናዊው የታሪክ ዘመን ያለውን የታሪክ ሂደት በማሳየት የኢትዮጵያን የስልጣኔ ከፍታ እና ዝቅታ ለማሳየት ተሞክሯል።

የዓድዋ ድል ታሪክም በጋዜጣዋ ተገቢ ሽፋን አግኝቷል። ዘመናዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ድርሻ የነበራቸውን የ19ኛው ክፍለ ዘመን ታሪክ ሠሪ ገድሎች ለማስነበብ ጥረት ተደርጓል። በአክሱም፣ በላሊበላ እና በጎንደር ዘመነ መንግሥታት የነበሩ ታሪካዊ ክስተቶችን በየጊዜው ማስነበቧን ልብ ይሏል።

ዓለማቀፍ እና አፍሪካ ነክ ጉዳዮችንም በመዳሰስ በኲር ቀላል የማይባል ሽፋን ሰጥታለች። በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች ዙሪያ፣ በአረቦች እና እስራኤል ጦርነቶች፣ በኒውክሌር እሽቅድምድም ታሪክ ዙሪያ፣ ስለ ጃፓን ከተሞች የአቶሚክ ቦምብ ታሪካዊ ዘግናኝ ጥቃት፣ ስለ ባርነት ታሪክ እና መሰል አያሌ ዓለማቀፍ ክስተቶች ተስተናግደዋል።

የአፍሪካ ታላላቅ ሰዎችን ታሪክ እና አበርክቶዎች በተለያዩ ጊዜያት ለመዳሰስ ተሞክሯል። እንደ ጀሞ ኬንያታ፣ ማንዴላ፣ ቶማስ ሳንካራ ያሉ አብዮተኞች ታሪካቸው በበኲር ጋዜጣ ተከትቦላቸው እናገኛለን። በኲር ታሪካቸውን ካስነበበችላቸው የብእር አርበኞች መካከል ናይጄሪያዊው እውቅ ፀሀፊ ችንዋ አቼቤ  ለአብነት ይጠቀሳሉ። ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ሰፊ ድርሻ ስለነበረው ኢትዮጵያዊ ከተማ ይፍሩ፣ አክሊሉ ሀብተ ወልድ እና ሌሌችም ሽፋን አግኝተዋል።

ወደ ቅርቡ ዘመን ስንመጣ ደግሞ “ዐፄ ሠርፀ ድንግል፤ ለጠንካራ እና የተባበረች ኢትዮጵያ” በሚል ርእስ ስለ ንጉሡ ዘመን የታሪክ ክንዋኔዎች ለማሳየት የተሞከረበትን ዘገባ እናገኛለን። “ምስኪኗ ንግሥት ዘውዲቱ”፣ “የዘመነ መሳፍንት ታሪክ” እና ሌሎችም ተዘግበዋል። በሌላ በኩል “የደበርኪ ሽንፈት የወለደው የዘመናት ድል” በሚል ርእስ ስለጋፋት የቴክኖሎጂ ታሪክ ተዘግቦ እናገኛለን።

እነዚህን ለአብነት አነሳን እንጂ ታሪክ በበኲር ጋዜጣ የ30 ዓመታት ጉዞ ውስጥ በርካታ ሽፋኖችን አግኝቷል ለማለት የሚያስደፍር ሀገራዊ ሚና ተጫውታለች። “ውቂያኖስን በጭልፋ…” እንዲሉ የበኲርን ለቁጥር የሚታክቱ የታሪክ መጣጥፎችን እንዲህ በአጭሩ አውስቶ መጨረስ አይሞከርም እና  እንኳን ለበኲር 30ኛ ዓመት አደረሳችሁ በማለት መሰናበት መርጫለሁ።

(መሠረት ቸኮል)

በኲር የታህሳስ 7  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here