ታጅ ማሃል

0
134

ልጆች እንደምን ናችሁ? ዋነኛው ሥራችሁ የሆነውን ትምህርት በሥርዓት እየተማራችሁ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን!

 ልጆች በዓለም ላይ በሰው እጅ የተሠሩ ሆነው አስደናቂ ከተባሉ ቦታዎች መካከል በሕንድ የሚገኘውን ታጅ ማሃልን እናስተዋውቃችሁ፡፡

ልጆችዬ፣ ታጅ ማሃል በአስደናቂ ውበቱ ብቻ ሳይሆን በታላቅ ታሪኩ እና በረቀቀ የኪነ ህንፃ ንድፉ ታዋቂ ነው። አጠቃላይ ሕንፃው ያረፈበት ስፍራ 17 ሄክታር እንደሚሆን ይገመታል። ታሪኩ ከንጉሡ ፍቅረኛ በወሊድ ምክንያት መሞት በኋላ ለመታሰቢያ ይሆናት ዘንድ የተሰራ ነው።  እጅግ ይወዳት የነበረው ባለቤቷ ንጉሠ ነገሥት ሻህ ጃሃን  ያሠራው ነበር።

 ሰኔ 17 ቀን 1632 . እንደሞተች የሚነገርላት ሙንታዝ ማሀል ከመሞቷ በፊት የመቃብር ስፍራ እንዲገነባላት በተናዘዘችው መሰረት የተገነባ እጅግ የዘመናችን ድንቁ የሰው ልጅ የእጅ ሥራ ውጤት ነው። ግንባታው 1624 . ተጀምሮ 20 ዓመታት በላይ የቀጠለ ሲሆን ዋናው መካነ መቃብር 1635 . ተጠናቀቀ እና በዙሪያው ያሉት ህንጻዎች እና የአትክልት ስፍራዎች 1653 . ተጠናቀዋል።

ግንባታው ከሙጋል ኢምፓየር እና ከዚያም ባሻገር በሺዎች የሚቆጠሩ የእጅ ባለሙያዎችን አሳትፏል። ምንም እንኳን ፕሮጀክቱ በርካታ ችሎታ ያላቸው ዲዛይነሮችን እና ግንበኞችን ያሳተፈ የትብብር ውጤት ቢሆንም ዋናው አርክቴክት ኡስታዝ አህመድ ላሀውሪ እንደሆነ ይነገራል።

 ቁሳቁሶች ከተለያዩ ክልሎች የተገኙ ሲሆን ነጭ እብነ በረድ በራጃስታን ውስጥ ከማክራና፣ ከፑንጃብ፣ ከቻይና፣ ከቲቤት፣ ከአፍጋኒስታን እና ከስሪላንካ በዝሆኖች ተጓጉዘው የመጡ የከበሩ ድንጋዮች እና ሌሎችም ጥቅም ላይ ከዋሉት መሀል ይጠቀሳሉ።

 የታጅ ማሃል ሕንፃው ፍጹም የተመጣጠነ እና የተዋሃዱ መጠኖች ምሳሌ ነው። ወደ 73 ሜትር (240 ጫማ) ከፍታ ያለው ማዕከላዊ ጉልላት በአራት ትንንሽ ጉልላቶች የታጠረ ነው። እያንዳንዱ የአወቃቀሩ ጎን ትልቅ የቀስት ቅርጽ ያለው በር አለው፣ ውስብስብ የአበባ እና ሂሳባዊ (ጂኦሜትሪክ) ንድፎችን  የሚፈጥሩ ውድ የከበሩ ድንጋዮች አሉ።

ታጅ ማሃል ቻርባግ ወይም ባለ አራት ክፍል የአትክልት ስፍራ በመባል በሚታወቀው ሰፊ የሙጋል የአትክልት ስፍራ ውስጥ ተቀምጧል። የአትክልት ስፍራው መቃብሩን በሚያንፀባርቁ የእግረኛ መንገዶች እና የውሃ ሰርጦች የተከፋፈለ ሲሆን ይህም አስደናቂ የእይታ ውጤት ይፈጥራል። እያንዳንዳቸው 40 ሜትር (131 ጫማ) ቁመት ያላቸው አራት ቀጫጭን ማማዎች በተነሳው መድረክ ጥግ ላይ ተቀምጠዋል። እነዚህ ማማዎች (ሚናራዎች) የመሬት መንቀጥቀጥ በሚከሰትበት ጊዜ ዋናውን መቃብር ለመጠበቅ ይረዳሉ፡፡ በትንሹ ወደ ውጭ ዘንበል ያሉ በመሆናቸው መዋቅሩ ላይ ያለውን ትልቅነት ይጨምራሉ።  ማዕከላዊው ክፍል ውስጥ የሙምታዝ ማሃል እና የሻህ ጃሃን መቃብር ይገኛል። በዓለም ቅርስነት 1975 .  የተመዘገበው ታጅ ማሃል በድንቅ የኪነ ሕንፃ ንድፉ የተመለከተውን ሁሉ የሚያስደምም የሰው ልጅ የጥበብ ማሳያ ተደርጎ ይቆጠራል። ታጅ ማሀል በአሁኑ ዘመን በርካታ ጎብኚዎች ከመላው ዓለም የሚጎበኙት ዘመናትን የተሻገረ አስገራሚ የዓለም ቅርስ ነው ይላል የታጅ ማሃል ይፋዊ ድረ ገጽ።

ጎበዙ አየለ

አየለ ተማሪ ነው፡፡ ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ተነስቶ ደርሶ መልስ አንድ ኪሎ ሜትር ይሮጣል፡፡ ይሄ ማለት ሲሄድ ግማሽ ኪሎ ሜትር ሲመለስ ግማሽ ኪሎ ሜትር ማለት ነው፡፡ ከዚያ ተዝናንቶ ቀላል ጂምናስቲኮችን ይሠራል፡፡ ቀጥሎ ቁርሱን ይበላ እና ወደ ትምህርት ቤቱ ይሄዳል፡፡

በትምህርት ቤትም በስፖርት ክፍለ ጊዜ ከክፍል ጓደኞቹ ጋር ኳስ ይጫወታል፤ ሩጫም ይወዳደራል፡፡

የትምህርት ቤቱ የስፖርት መምህርም አየለን በጣም ያበረታቱታል፡፡ ሩጫም ስለሚያለማምዱት በየጊዜው የሩጫ ፍጥነቱን ያሻሽላል፡፡ አየለ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ውድድር ሲኖር ከእኩዮቹ ጋር ሁልጊዜ ይወዳደራል፡፡ ወደፊት ሀገሩን የሚያስጠራ ሯጭ መሆን ይፈልጋል፡፡ ልጆች አየለ ጎበዝ ነው አይደል? እናንተም እንደ አየለ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባችሁ ከታሪኩ ትማራላችሁ፡፡::

ሞክሩ

ከዓለም በቆዳ ስፋት ሁለተኛው አህጉር ማን ይባላል?

የአባቴ አንድ ልጅ አለው፤ ማን ነው?

የኬንያ ዋና ከተማ ማን ይባላል?

መልስ

አፍሪካ

እኔ

 ናይሮቢ

ነገር በምሳሌ

  1. ሹመት ሲገኝ ዘመድ አይገድም

ትልቅ ደረጃ የደረሰን ሁሉም ይፈልገዋል::

 

  1. መልካም ተመኝ መልካም እንድታገኝ

ጥሩ  ስታደርግ  ጥሩ  ይገጥምሃል፡፡

 

  1. የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው

እያለው እንደሌለው የሚቸገር ማለት ነው::

(ቢኒያም መስፍን)

 

በኲር የታህሣስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here