የአማራ ክልል ካለፉት ሁለት ዓመታት በላይ በሰላም እጦት ውስጥ እያለፈ ይገኛል:: በእነዚህ ዓመታትም ትምህርት ቤት የናፈቃቸው፣ ጓደኞቻቸውን ማግኘት የጓጉ፣ ከዕውቅት ለጋሽ መምህሮቻቸው ጋር መገናኘት የሻቱ ነገር ግን ከትምህርት ገበታ ለመራቅ የተገደዱ ተማሪዎች ቁጥር ውስን አይደሉም::
የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው በእነዚህ ዓመታት ከትምህርት የራቁ ተማሪዎች ቁጥር ሰባት ሚሊዮን ገደማ ነው:: ይህም ተማሪዎችን ለስነ ልቦናዊና ሌሎች ችግሮች አጋልጧል፡፡ የዛሬው መጣጥፍ ባለታሪካችን ደግሞ አንዷ ናት፡፡
ለደኅንነቷ ሲባል ስሟ ያልተጠቀሰው ባለታሪካችን በ2016 ዓ.ም ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆና መክረሟን ታስታውሳለች:: ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ የደረጃ ተማሪ የነበረችው ተማሪዋ ከትምህርት ውጪ ሆና የቆየችበት አንድ ዓመት ብዙ ያልተገቡ አስተሳሰቦች ወደ አዕምሮዋ እንዲመጡ እንዳደረጋት ተናግራለች::
ትምህርት ከዛሬ ነገ ይጀመራል የሚል ተስፋን ሰንቃ የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ ራሷን ታረጋጋ ነበር፤ በምታነባቸው መጻሕፍት ደግሞ (በተለይ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ገብተው፣ ችግርን ተቋቁመው ወደስኬት ጎዳና ያመሩ ገጸ ባህሪያት) በችግር ሳትበገር፣ ተስፋም እንድትሰንቅ አደረጋት:: ከልጅነቷ ጀምሮ ሐኪም የመሆን ርዕይን ያነገበችው ተማሪዋ፣ ይህም ተጨማሪ ብርታት እንደሆናት ነው የነገረችን::
በሌላ አካባቢ የሚገኙ ጓደኞቿ በዓመቱ የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቀው ለቀጣይ እየተዘጋጁ መሆኑን ሲነግሯት እኔስ መቼ ነው ወደ ትምህርት የምመለሰው በሚል ለሌላ ጭንቀት ተዳርጋ እንደነበርም ነው ያስታወሰችው::
ይህ በእንዲህ እንዳለ በክል የተፈጠረው ግጭት ግን ቀጠለ፤ ባለታሪካችን ግን ዳግም ለሁለተኛ ዓመት ከትምህርት ውጪ ሆኖ መክረምን አልፈቀደችም:: ሰላም ወዳለበት አካባቢ መሄድን መፍትሄ አደረገች፤ ቤተሰብም ሐሳቧን ደገፉላት:: ባሕር ዳር ከተማን ደግሞ ምርጫዋ አደረገች::
ከ2017 የትምህርት ዘመን ጀምሮም በባሕር ዳር ከተማ ትምህርቷን እያስቀጠለች በአሁኑ ወቅት ስምንተኛ ክፍል ደርሳለች:: (የክልሉ ሰላም መታወክ ባይገጥመው ኖሮ በዚህ ዓመት ዘጠነኛ ክፍል ትገባ እንደነበር ልብ ይሏል)::
ብዙዎች ከለመዱት አካባቢ መራቃቸው፣ ከቤተሰብ እና ጓደኞቻቸው እንዲሁም ከሚያውቋቸው መምህራን መለየታቸው፣ የኢኮኖሚ አቅም ውስንነት እና ሌሎችም ችግሮች የቀደመውን የትምህርት አቀባበል ለማስቀጠል ፈተና እንደሚሆንባቸው ይታመናል:: እነዚህ ችግሮች ግን ተማሪዋን ከዓላማዋ ወደ ኋላ አላደረጓትም:: ለዚህ ያበቃትም ቀድማ ያስቀመጠችው ዓላማ እና የቤተሰብ ድጋፍ ነው::
ግጭቱ በቀጠለባቸው አካባቢዎች ለሦስተኛ ዓመት ከትምህርት የራቁ ተማሪዎች መኖራቸውን ተማሪዋ ተናግራለች:: ይህም ታዳጊዎች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲገቡ በማድረግ የትውልድ ክፍተትን ይፈጥራል ስትል ነው ስጋቷን ያጋራችን:: ይህም ሀገር ተረካቢ እንድታጣ የሚያደርግ በመሆኑ አደጋውን በዚህ ልክ ተረድቶ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ ገልጻለች::
ተማሪዎች በሚኖሩበት አካባቢ ትምህርት ቤቶች ካልተከፈቱም አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው አካባቢዎች ሄደው ትምህርታቸውን እንዲያስቀጥሉ፣ ማኅበረሰቡ እና መንግሥትም ትምህርት እንዲጀመር የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠይቃለች::
በክልሉ የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ፣ ያልተከፈቱ ትምህርት ቤቶችም እንዲከፈቱ ጥረት ከክልል ጀምሮ በተዋረድ ያሉ ባለድርሻዎች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ:: ይሁን እንጂ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት አልመጣም፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች አሁንም ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸውና ነው::
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ደግሞ አንዱ አብነት ሲሆን 790 ሺህ 474 ተማሪዎችን መዝግቦ ማስተማር የትምህርት ዘመኑ ዕቅድ ነው:: ነገር ግን በሩብ ዓመቱ ማሳካት የቻለው የዕቅዱን 17 ነጥብ ሰባት በመቶ ብቻ መሆኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ጌታሁን ፈንቴ አስታውቀዋል:: 824 ትምህርት ቤቶች ወደ መደበኛ ሥራቸው አለመመለሳቸውን ያስታወቁት ኃላፊዉ፣ ቀሪ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸዉ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት::
ምዕራብ ጎጃም ዞንም 426 ሺህ 29 ተማሪዎችን ለማስተማር ዕቅድ ነበረው:: የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ የስጋት ደሴ ጥቅምት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር:: እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ 89 ሺህ 738 ተማሪዎች ብቻ እንደተመዘገቡ ነው የጠቀሱት::
አቶ ካሳሁን አዳነ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አማካሪ ናቸው:: ትምህርት ቤቶች በሚዘጉበት ወቅት ተማሪዎች የሚያጡት ዕውቀትን ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቦናቸውን፣ ዕድሜያቸውን፣ ሕልማቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን ምኞት ጭምር መሆኑን ገልጸዋል:: በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች በማይከፈቱበት ወቅት ተማሪዎች በቀላሉ ተስፋ ከመቁረጥ፣ ትምህርትን ችላ ከማለት፣ ከቀየ ርቆ በመጓዝ ለነገ ሕይወት በማይበጅ ተግባር ላይ ከመሰማራት እንዲቆጠቡ ነው ያሳሰቡት::
ወላጆችም ልጆቻቸው ወዳልተፈለገ መንገድ እንዳይገቡ መምከር፣ ትምህርት እንዲጀመርም ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል:: ትምህርት ሲጀመርም ተማሪዎች የገጠማቸውን መሰናክል ማለፍ እንደሚችሉ አስበው መማር እንደሚኖርባቸው ነው ምክረ ሐሳብ ያቀረቡት::
መምህራንም በሥነ ልቦና የተጎዱ እና የትምህርት ፍላጎታቸው የቀነሱ ተማሪዎችን በመደገፍ ለውጤት ማብቃት እንደሚኖርባቸው ለአሚኮ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል:: የተማሪዎችን ፍላጎት፣ አቅም፣ የሥነ ልቦና ዝግጅት እና የሚደርሱባቸውን ተጽዕኖዎች ለይቶ ለመደገፍ በቅርበት ማወያየት፣ ችግሮች ከእነሱ በላይ እንዳልሆኑ መንገር እንደሚገባቸው አስታውቀዋል::
የክልሉ የትምህርት ሥራ እንደዚህ ጊዜ የተጎዳበት እና ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ወቅት የለም ያሉት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን ወርቅነህ ናቸው:: በትምህርት መቋረጥ ምክንያት በትውልዱ ላይ መጥፎ ጠባሳ እንዳይጥል ሁሉም መረባረብ እንዳለበት ያነሱት ቢሮ ኃላፊው በጋራና በትጋት በመሥራት የክልሉን ትምህርት መታደግ እንደሚገባም አሳስበዋል::
ከቢሮው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው አሁን ላይ በብዙ አካባቢዎች የተጀመሩ የትምህርት ተሳትፎ ሥራዎች መሻሻል እያሳዩ ይገኛሉ:: ይህንንም በሁሉም አካባቢዎች በማስፋት ሁሉም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት እንዲመዘገቡ፣ ትምህርት እንዲጀምሩ እና ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ትውልድ የማነፅ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅ ተናግረዋል::
አማርኛ በአማርኛ
አማጠነ – እንዲፈጸምለት አጥብቆ ጠየቀ
ጊድራ ሠራኝ – ግፍ ፈጸመብኝ
መለመኛ አጣ – ፈጽሞ ደኸዬ
ቧዘዘ – ባዘነ
ጢንጉራ – በጣም ትንሽ
ተዝካሩ ተበላ – አለቀለት፤ አበቃ
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሕዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


