ትምህርትን ከፈተና ለማውጣት

0
228

ያለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ሕዝብ ኢኮኖሚዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥል የሚያደርገውን የትምህርት ዘርፍ ግን እጅጉን ፈትኖታል::

በ2016 ዓ.ም ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሚልቁ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው ከርመዋል:: በ2017 የትምህርት ዘመንም ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች አልተማሩም:: መምህራን የሚወዱትን ሙያቸውን በነጻነት እንዳይናገሩ፣ በነጻነት ተንቀሳቅሰው ሥራቸውን እንዳይሠሩም ሆነው ከርመዋል::

 

ግጭቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የትምህርት ተቋማት ከትምህርት ውጪ ሆነው እንዲከርሙ ከማድረግ ባለፈ ለተለያየ አይነት ጉዳት ተዳርገው የትምህርት ተቋማትን ደረጃ ለማሻሻል የሚውለው በጀት ለመልሶ ግንባታ እንዲውል አድርጓል::

ግጭቱ በትምህርት ዘርፉ ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ግን በአዲሱ ዓመት (በ2018 የትምህርት ዘመን) እንዳይቀጥል ሁሉም ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ እየተጠየቀ ነው:: የመገናኛ ብዙኃን ደግሞ በተደራሽነታቸው ልክ ግጭቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ አጉልቶ በማሳየት ሁሉም ለመፍትሄው እንዲሠራ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አሳስቧል::

በተዋረድ የሚገኙ የትምህርት ባለድርሻ አካላትም ችግሩ የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቋረጥ እያደረገ በመሆኑ ለችግሩ ማብቂያ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆኑን እያስታወቁ ነው:: የችግሩ ተጽእኖ በርትቶ ከታየባቸው አካባቢዎች መካከል የምሥራቅ ጎጃም ዞን ይገኝበታል:: የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ጌታሁን ፈንቴ የ2017 ዓ.ም የትምህርት እንቅስቃሴ ቀድሞ ከነበረው ዓመት (2016ዓ.ም) ጋር ሲነጻጸር እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሁሉንም ተማሪዎች ግን ወደ ትምህርት መመለስ እንዳልተቻለ ተናግረዋል:: ሁሉንም ትምህርት ቤቶች መክፈት አልተቻለም ብለዋል::

 

በ2016 ዓ.ም 964 ትምህርት ቤቶችን ያልከፈተው ዞኑ በ2017 የትምህርት ዘመንም 639 ትምህርት ቤቶቹ ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል:: በዓመቱ መዝግቦ ለማስተማር በዕቅድ ተይዞ የነበረው የተማሪ ቁጥር 713 ሺህ እንደነበርም አስታውሰዋል:: ይሁን እንጂ 623 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነው መክረማቸውን አስታውቀዋል:: በዚህም 90 ሺህ ተማሪዎች ብቻ በትምህርት ገበታ እንደነበሩ ልብ ይሏል:: ይህ የተማሪ ቁጥር በ2016 ዓ.ም ተመዝግበው በመማር ላይ ከነበሩት ጋር ሲነጻጸር በ77 ሺህ ያደገ ነው:: ይህም ተስፋ ሰጪ ሆኖ ተጠቁሟል::

ችግሩ በትምህርት መዋቅሩ፣ በተማሪዎች፣ በመምህራን እና በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል የሚባል እንዳልሆነ አቶ ጌታሁን ጠቁመዋል:: ታዳጊዎች ትምህርት ቤት ባለመዋላቸው ምክንያት ላልተገባ ሥነ ምግባር እንዲጋለጡ አድርጓል ባይ ናቸው:: ትምህርት ላይ ጊዜያቸውን ማሳለፍ የነበረባቸው በርካታ ታዳጊዎች ላለዕድሜ ጋብቻ ተዳርገዋል፤ ላልተፈለገ እርግዝና የተጋለጡትም ውስን አይደሉም፤ ያልተገባ ፍልሰት የታዳጊዎችን ሕይወት እያበላሸም ነው ብለዋል::

 

መመህራን፣ የወላጅ መምህራን ማኅበር (ወመህ) አባላት፣ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ሙያተኞች እና አመራሮችም ቀጣይነት ያለው የተማረ የሰው ኃይል ለመገንባት በሚያደርጉት ጥረት ዋጋ መክፈላቸውን ለግጭቱ ተጽእኖ ማሳያ በማድረግ መምሪያ ኃላፊው አንስተዋል::

ይህ በእዲህ እንዳለ በችግር ውስጥም ሆኖ ዓመቱን ሙሉ ሲማሩ የከረሙ የስድስተኛ፣ የስምንተኛ እና የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ማስፈተን መቻሉን ተናግረዋል:: የተፈታኝ ተማሪዎች ቁጥር ከ2016 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር የተሻለ እና ለቀጣይ ዓመትም ተስፋን የሚፈነጥቅ እንደሆነ አስረድተዋል::

በአሁኑ ወቅትም የ2018 የትምህርት ዘመንን በተሳካ ሁኔታ ጀምሮ ለማጠናቀቅ የ90 ቀናት የቅድመ ዝግጅት ዕቅድ ተቀምጦ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል:: በግጭቱ 627 ትምህርት ቤቶች ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ጠቁመዋል:: የውስጥ ግብዓታቸው ተዘርፏል፤ የመምህራን መጠለያዎች ከነሙሉ ዕቃቸው ወድመዋል፤ መማሪያ ክፍሎች ለመማር ማስተማር ምቹ እንዳይሆኑ ተደርገው ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቀዋል:: የትምህርት ቤቶቹ የጉዳቱ መጠን ወደ ገንዘብ ሲቀየር ከ546 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳለውም ጠቅሰዋል::

 

የተለያየ የጉዳት መጠን ያስተናገዱ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹነት ያላቸው አድርጎ ማደራጀት የቅድመ ዝግጅቱ አንዱ አካል መሆኑን አቶ ጌታሁን ገልጸዋል:: የጸጥታው መደፍረሱ ባስከተለው ችግር ምክንያት ለጉዳት የተዳረጉ የተማረ ትውልድ ማፍሪያ ማዕከላትን ለማደራጀት ሕዝቡ በችግሩ ዙሪያ የጋራ መግባባት እንዲኖረው ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት ቀዳሚው ጉዳይ መሆኑን አስታውቀዋል:: ለዚህም “የዞናችንን ትምህርት ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ ሀሳብ ከቀበሌ እስከ ዞን የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል:: የንቅናቄ መድረኩ በቀጣይ የክረምት ወራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል::

ትምህርት ከፈተና እንዲወጣ ዋነኛው መፍትሄ ሕዝቡ ነው:: ሕዝቡ ልጆቹ ዕውቀት የሸመቱባቸውን እና የሚሸምቱባቸውን የትምህርት ተቋማት ችግሮች ቀርቦ እንዲመለከት፣ ከችግር የሚወጡበትን መንገድ ለይቶ እንዲሠራ፣ በቀጣይም ለተቋማቱ ከለላ እንዲሆን ማንቃት እና ማብቃት ላይ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል::

 

የዞኑ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶችን እንደገና ለማደራጀት በሚደረገው ጥረት በቁሳቁስ፣ በገንዘብ እና በጉልበት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል:: ትምህርት ቤቶች ያሏቸውን ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ እየተሠራ ያለውን ሥራ ለቅድመ ዝግጅቱ ጅምር አድርገው አንስተዋል:: ይህም የትምህርት ቤቶችን ገቢ በማሳደግ መማር ማስተማሩን ምቹ ለማድረግ እንደሚያግዝ ነው ያነሱት:: መማሪያ ክፍሎችን መጠገን፣ የትምህርት ቤቶችን አጥር መልሶ መገንባት እና ማጠናከር በቀጣይነት የሚከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል::

 

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች እና የትምህርት መቀጠል ይመለከተኛል የሚል አካል ሁሉ የደረሰውን ጉዳት በመረዳት መልሶ ለመገንባት እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል::

እንደ አቶ ጌታሁን ማብራሪያ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የትምህርት ዘርፉ ሌላኛው አቅም ነው:: ትምህርት ቤቶችን መልሶ በማደራጀት እና ገጽታቸውን በመቀየር ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ይገኛል:: በመንግሥት፣ በአልማ እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ ከ207 በላይ ፕሮጀክቶች እየተሠሩም ነው::

ፕሮጀክቶቹ መጸዳጃ ቤቶችን ጨምሮ ቤተ መጻሕፍትን እና ማስፋፊያ ክፍሎችን ያካተቱ ናቸው:: 63 ግንባታዎች ለ2018  የትምህርት ዘመን ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል:: ከ46 በላይ ፕሮጀክቶች በቅርብ ይጠናቀቃሉ ያሉት መምሪያ ኃላፊዉ፣ 98ቱ በጸጥታ ችግር ምክንያት ግንባታቸው የቆሙ መሆናቸውን አስታውቀዋል:: ሁሉም ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የዞኑን የትምህርት ተቋማት ደረጃ በእጅጉ እንደሚያሻሽሉት ያላቸውን ተስፋ አክለዋል::

 

የተማሪዎችን የመማሪያ መጻሕፍት ቀድሞ ማሟላትም ሌላው የሦስት ወራቱ ዕቅድ አካል ሆኖ እየተሠራበት ነው:: ቀድመው የመጡትን መጻሕፍት ወደየወረዳዎቹ በመላክ ማሠራጨት ተችሏል:: አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ መጻሕፍት ወደ ዞኑ እየተጓጓዙ ነው ያሉት አቶ ጌታሁን፣ በፍጥነት እንደሚሰራጩም አረጋግጠዋል::

የተማሪ መቀመጫ ወንበርም በቅድመ ዝግጅት ሥራው ወቅት የሚሟላ ተግባር ነው:: አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ (ደብተር፣ እስክርቢቶ፣ ደብተር፣ ቦርሳ፣ ዩኒፎርም፣…) ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ ነውም ብለዋል::

በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት የባከኑ የትምህርት ጊዜያትን ሊያካክስ የሚችል የመማር ማስተማር ሥራ ለማከናወን መምሪያው እና ባለድርሻ አካላት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል::

 

በቀጣይ ዓመት ትምህርት ቤት የማይገባ አንድም ተማሪ አይኖርም የሚል የቁጭት ዕቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱም ተጠቁሟል:: ማኅበረሰቡም እስካሁን በግጭት ያለፈው ጊዜ ይበቃል፤ ትምህርት ቤቶች ይከፈቱ፤ ሕጻናት ወደ ትምህርት ይመለሱ ብሎ ሊሞግት እንደሚገባ አቶ ጌታሁን አሳስበዋል:: መምህራንም ከወዲሁ ጠንካራ ስነ ልቦና ተላብሰው ለቀጣይ የተሻለ ትምህርት አሰጣጥ እንዲነሳሱ ጠይቀዋል:: በክረምቱ የሚሰጠው የመምህራን የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል::

በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው እና አሁንም ድረስ የቀጠለው ግጭት ከስድስት ሺህ 154 በላይ ትምህርት ቤቶች ለጉዳት መዳረጋቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ይጠቁማል:: ቢሮው ይህንን መረጃ ይፋ ያደረገው ግጭቱ በትምህርት ዘርፉ ላይ ያደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ከአጋር አካላት ጋር ምክክር ባደረገበት ወቅት ነው:: ግጭቱ 57 በመቶ የሚሆኑ የትምህርት ተቋማትን ለጉዳት እንደዳረገም መረጃው አክሏል::

 

ግጭቱ ትምህርት ቤቶችን ለጉዳት ከመዳረግም ባለፈ በ2017 ዓ.ም ብቻ ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ሲያርቅ፣ አራት ሺህ 821 ትምህርት ቤቶች ሳይከፈቱ የትምህርት ዘመኑን እንዲያሳልፉ አድርጓል::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከብዙኃን መገናኛ መሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር ምክክር ባደረገበት ወቅት የጸጥታ ችግሩ በትውልድ ላይ ብክነት እየፈጠረ መሆኑ ተመላክቷል:: ይህ ወቅት በቃ የሚባልበት መሆን እንዳለበትም ተጠቁሟል::

የ2018 የትምህርት ዘመንን ከችግር በጸዳ መንገድ ለማስኬድ ከወዲሁ መሠረተ ልማትን ማሟላት፣ ትምህርት ቤቶችን መጠገን፣ በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ መሥራት እንደሚገባም ተመላክቷል:: የተጀመሩ የትምህርት ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ እና ለተማሪዎች ምዝገባ ቀድሞ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ቢሮዉ አሳስቧል::

 

 

 

ግዕዝ በአማርኛ

ሠረቀ – ወጣ፣ ፈነጠቀ

ሰረቀ –  ሰረቀ (ሌብነት)

አመት – አገልጋይ

ዓመት – ዘመን

ሰዐለ – ስዕል ሳለ

ሰአለ –  ለመነ

 

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here