ትምህርት እና ተግዳሮቶቹ

0
150

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለም ላይ ከ222 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል:: የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ድንበር ዘለል ጦርነቶች እና በተፈጥሯዊ እና በሰው ሠራሽ ምክንያት የሚፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ ቀዳሚ መንስኤ መሆናቸውን አስቀምጧል:: መረጃው አክሎም እነዚህ ችግሮች እ.አ.አ በ2022 ብቻ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸውን ያሳያል፤ ከዚህ ቁጥር ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለመማር ዕድሜያቸው የደረሱ ሕጻናት ናቸው::

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ ግጭቶች በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደሩትን ተጽዕኖዎችንም ዳስሷል:: ከፈረንጆቹ ጥር 2020 እስከ ታኅሳስ 2021 ባሉት ጊዜያት ብቻ በ85 ሀገራት በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ አምስት ሺህ ጥቃቶች ተፈጽመዋል:: በእነዚህ ጊዜያት ያጋጠሙት በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች የትምህርት ተቋማት ለወታደራዊ ማዘዣነት እንዲውሉ ተደርጓል:: ይህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት እንዲገለሉ፣ ትምህርት ቤቶችም ያለ ተማሪ እና መምህር ተዘግተው እንዲከርሙ፣ የውስጥ ግብዓታቸውም እንዲዘረፉ ሆኗል::

ከአምስት ሺህ በላይ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ዘጠኝ ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን እና መምህራንን ለአስገድዶ ጠለፋ ሰለባ እንዳደረጋቸው የድርጅቱ መረጃ ያሳያል:: መምህራን እና ሌሎችም የመማር ማስተማር ተዋንያን ታስረዋል:: ይህም ታዲያ የትምህርት ጥራት አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ ሊያደርግ እንደሚችል ነው የድርጅቱ መረጃ የችግሩን አሳሳቢነት ያመላከተው::

ትምህርት እና የትምህርት ሥርዓቱ እንዲፈተን ያደረጉ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች በተለይ በአፍሪካ አድማሳቸው ሰፍቶ ይታያል:: ‘ሂዩማን ካፒታል አፍሪካ’ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የትምህርት ጥራት ላይ የሚሠራ የሀገራት ጥምረት ተቋም ነው:: ይህ ተቋም በአፍሪካ ያለው የትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስቧል:: እንደ መረጃው በአፍሪካ ከዐሥር ተማሪዎች ዘጠኙ በዐሥር ዓመታቸው መጻፍ፣ ማንበብ እና መሠረታዊ የሒሳብ ሥሌቶችን መሥራት አይችሉም::

ትኩረቱን በአፍሪካ ሀገራት ትምህርት ላይ አድርጎ የሚሠራው ‘ዴቨሎፕመንት ኦፍ ኤዱኬሽን ኢን አፍሪካ’ የተባለው  ድርጅት በበኩሉ ለአፍሪካውያን የትምህርት ውድቀት መሠረታዊ ምክንያት ናቸው ያላቸውን ችግሮች ዘርዝሯል:: መፈንቅለ መንግሥት፣ ጦርነት፣ አስተማማኝ ሰላም አለመኖር እና የአየር ንብረት ለውጥ በቀዳሚነት የዘረዘራቸው ምክንያቶች ናቸው::

ሀገራት ለትምህርት ዘርፉ የሚሰጡት ትኩረት አናሳ መሆን፣ የትምህርት አሰጣጡ ወጥነት የሌለው መሆን፣ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚመደበውን ሀብት ለሚፈለገው ዓላማ አለማዋል እና የፖሊሲ ማነቆዎችን በተጨማሪነት የዘረዘራቸው ለትምህርት ውድቀት ምክንያቶች ናቸው:: በእነዚህ እና በሌሎችም መሰል ምክንያቶች በአህጉሪቱ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን የአፍሪካ ሕብረት 37ኛውን የሕብረቱን ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት አስታውቋል::

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያትነት እየመጡ ባሉ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት፣ … እየተፈተነች ትገኛለች:: ከእነዚህ ችግሮች በሻገር መፍትሔ ርቋቸው አሁንም ድረስ በቀጠሉ ግጭቶች በርካቶች መኖሪያቸውን እንዲለቁ እያደረጋቸው ይገኛል:: ሁሉም ችግሮች የሰዎችን ሠርቶ የመለወጥ እንቅስቃሴ በመግታት ሚሊዮኖች እጃቸውን ለእርዳታ እንዲዘረጉ፣ በምግብ እጥረት ምክንያት ዓላማቸውን ከዳር እንዳያደርሱ ያደርጋቸዋል:: የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ 15 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብ እንደሚፈልጉ ሲያስታውቅ፣ ከእነዚህ ውስጥ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት እስከ 59 የሚሆኑት 41 በመቶ ዜጎች ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጡ መሆናቸውን ጠቁሟል:: ሕጻናት አስፈላጊ የተመጣጠነ ምግብ ካላገኙ ደግሞ በትምህርት አቀባበላቸው ደካማ ከመሆን ጀምሮ የጀመሩትን ትምህርት እስከ ማቋረጥ ያስገድዳቸዋል::

ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን እየፈተኑ ናቸው የተባሉት ችግሮች በኢትዮጵያ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ እንዳራቃቸው  ዓለም አቀፉ የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እ.አ.አ ነሐሴ 8 ቀን 2024 ይፋ አድርጓል:: ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው::

ግጭቶች ወይም ጦርነቶች በትምህርት ተቋማት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት የከፋ ነው፤ ለአብነትም የሰሜኑ ጦርነት በአማራ ክልል ያደረሰው ውድመት ከበቂ በላይ ማሳያ ነው:: በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ሚያዚያ 04 ቀን 2016 ዓ.ም እንዳስታወቀው ጦርነቱ ሁለት ሺህ 935 የትምህርት ተቋማት ከቀላል እስከ ከባድ ውድመት ደርሶባቸዋል::

ወደ ግጭት እና ጦርነት የሚያስገቡ የሐሳብ ልዩነቶችን ቀድሞ በመነጋገር መፍታት፣ ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት አስፈላጊውን በጀት መመደብ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በአፍሪካ የትምህርት ሥርዓት ላይ የተደቀነውን ስጋት ለመፍታት በትኩረት ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናውን ዩኒሴፍ አሳስቧል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ጥቅምት 18  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here