“ሀገሬ የመምህራን ሀገር ነች። ስለዚህ የሰላም ሀገር ናት ማለት ነው:: ስኬቶቻችን እና ውድቀቶቻችንን በፍጹም ነፃነት እንወያይባቸዋለን። ሀገሬ የመምህራን ሀገር ስለሆነች የሰራዊት ካምፖችን ዘግተናል፤ ልጆቻችን በእጃቸው መጻሕፍትን እንጂ በትከሻቸው መሳሪያን እንዲሸከሙ አልፈቀድንም:: የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ውይይት፣ ንግግር እና ድርድርን ዋና መሳያችን አድርገናል:: ጥቃትን አንቀበልም። ሀገሬ የመምህራን ሀገር ስለሆነች ተቃዋሚዎቻችንን ለማሳመን እንጂ ለማሸነፍ ብለን ከሰላም ውጪ ያሉ አማራጮችን አንከተልም:: የወደቁትን ከመጨፍለቅ ይልቅ ማንሳትን እንመርጣለን::
ምክንያቱም ማንም ፍጹም እውነት እንደሌለው እናምናለን። ሀገሬ የመምህራን ሀገር ስለሆነች ነዋሪዎቿ በአብሮነት መንፈስ የሚተባበሩበትን በኢኮኖሚ ከፍ ያለች ሀገር መገንባት እንጂ እርስ በርስ በመፎካከር የሚጠፋፉባት ሀገር እንድትሆን አንልፈለግንም::” ይህን የተናገሩት በ1987 እ.አ.አ የኖቤል ተሸላሚው የኮስታሪካ ፕሬዚዳንት ኦስካር አሪያስ ሳንቸዝ ናቸው::
የዛሬዋ ዓለም ግን ኦስካር አሪያስ ሳንቼዝ የትምህርትን አስፈላጊነት ከተናገሩበት በተቃራኒ ሆናለች:: ‘ዴዘርት’ (www.deseret.com) የዜና አውታር እ.አ.አ መስከረም 25 ቀን 2024 ይፋ ባደረገው መረጃው በዓለም ላይ 92 ሀገራት በግጭት እና በጦርነት ውስጥ ይገኛሉ:: ይህም በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው::
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (UNESCO) እ.አ.አ የወርሀ ጥቅምት 2024 መረጃ እንደሚያመላክተው 251 ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል:: በኢትዮጵያም ከሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቶች እና ከአስተማሪዎች ጋር ላይገናኙ ተራርቀው እንደሚገኙ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል:: በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሚሊዮኖች ከትምህር ውጪ እንዲሆኑ ያደረጉ ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ግጭቶች እና ጦርነቶች ናቸው::
ግጭቶች ትምህርትን እንዴት ይጎዱታል? የሚለውን በተመለከተ ትኩረቱን ዓለም አቀፋዊ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ አድርጎ ዘገባዎችን የሚያጠናክረው ዴቬክስ (devex.com) የመረጃ አውታር በድረ ገጹ አስፍሯል:: በግጭት ወቅት የትምህርት ባለሙያዎች በቅርበት አይገኙም:: በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት አካባቢያቸውን ይለቃሉ:: የትምህርት ግብዓቶች አይኖሩም:: ግጭቱ እየተባባሰ ከሄደም መማሪያ ክፍሎች ይወድማሉ::
ይሁን እንጂ ትምህርት በራሱ ግጭቶችን ለመፍታት ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ድረ ገቱ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ያስረዳል:: መምህራን የሰዎችን አስተሳሰብ፣ አመለካከት እና አተያይ መቀየር ይችላሉ:: በግጭት ወቅት መምህራን ከተመደቡበት ሲርቁ ግን ትምህርት የግጭት መፍትሔነቱን ያጣል:: ትምህርት ግጭት በሚፈጠርባቸው አካባቢዎች የሚገኘውን ሕዝብ በማሰባሰብ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ እንዲገኝ በማድረግ ረገድ ትልቅ አበርክቶ አለው::
ትምህርት ሰዎች የራሳቸውን አስተያየት እና ውሳኔ እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል:: ግጭት ቀስቃሽ አካላት ሰዎች ወደ ማያባራ ጥል እንዲገቡ እና የቆይታ ጊዜውም እንዲራዘም በየጊዜው ለሕዝብ አጀንዳ ይፈጥራሉ:: አጀንዳቸውም ነባር እውነታን በማዛባት ማሰራጨት ሊሆን ይችላል:: ታዲያ ጥራት ያለው ትምህርት ለግጭት መፍቻ እንደ ቁልፍ መሳሪያ ሊወሰድ ይችላል::
ጥራት ያለው ትምህርት ዜጎች እውነታውን ራሳቸው አንብበው እንዲረዱ ያደርጋቸዋል:: እውነታውንም ለእነሱ ምን ትርጉም እንዳለው አድርገው በመተንተን እንዲጠቀሙት የሚያደርግ በመሆኑ የራሱን ውሳኔ እንዲያሳልፍ ያደርገዋል::
ትምህርት ምን ያህል ግጭቶችን ቀድሞ መከላከል እንደሚያስችል በኢራን የሆነውን ጥሩ ማሳያ ነው:: በኢራቅ ውስጥ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድኖች ሕዝብን ከመንግሥት ነጥለው ከጎናቸው ለማሰለፍ ሲሉ የእስልምና ሃይማኖታዊ መጽሐፍ የሆነውን ቁርዓን በራሳቸው አዛብተው በመተርጎም ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል:: ኢራቃውያን አረበኛ የተማሩ በመሆናቸው መጽሐፉን በራሳቸው አንብበው እንዲረዱ ስላደረጋቸው ለጊዜው የሽብርተኞችን የግጭት ድጋፍ ጥሪ ማክሸፍ ተችሏል::
መረጃው እንደሚያመላክተው በግጭት ምክንያት የትምህርት መቋረጥ የግጭቱን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት የሚችሉ ዜጎች እንዳይፈጠሩ እያደረገ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ:: ግጭቶችን ለመፍታት ታላላቅ መሪዎችን እና የተማረ ዜጋን ይጠይቃል።
ግጭቶች መፍትሔ ባልተሰጡበት ሀገር ሕጻናት ከትምህርት ውጪ ይሆናሉ:: ይህም የአንድ ሀገር የተማረ ዜጋ ቁጥር በእጅጉ እንዲቀንስ ያደርገዋል:: በዚህም አሁን ካለው ችግር እንዴት መውጣት እንደሚቻል የሚያመላክት፣ ወደ ፊትም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጥናት ለይቶ የሚያከሽፍ ተመራማሪ በአጭር ጊዜ ለማግኘት አይቻልም::
በሌላም በኩል ግጭት የተማሩ ምሁራን ከሀገር እንዲወጡ ያደርጋቸዋል:: እነዚህም ምክንያቶች ሀገራት በሁሉም የእድገት ዘርፎች ወደ ኋላ እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል::
በግጭት ውስጥ የቆዩ ተማሪዎች በርካታ አሰቃቂ ሁኔታዎችን ሊያሳልፉ ይችላሉ:: ከመኖሪያ ቀያቸው ይፈናቀላሉ:: ይህም ከተለመደው አኗኗራቸው ተለይተው እንዲቆዩ የሚያደርጋቸው በመሆኑ በቀላሉ ወደ ቀደመ ንቁነታቸው እንዳይመለሱ ሊያደርጋቸው ይችላል:: ከቤተሰብ አባላት መካከል በሞት ያጡት ሰው መኖር፣ ሰዎች ሲገደሉ በዐይናቸው ማየት፣ የተለያዩ አይነት መሳሪያ ድምጾችን በተደጋጋሚ መስማታቸው ሰላም ከሰፈነ በኋላም በቀላሉ ከስጋት ነጻ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል:: ይህም የተለመደ ባህሪያቸውን እንዲያጡ ያደርጋቸዋል::
የግጭቱ ውጤት እየባሰ የሚሄደው ሰላም ከሰፈነ ከብዙ ዓመታት በኋላ ነው:: ምክንያቱም ዛሬ ትክክለኛው ትምህርት ቤት የመግቢያ ዕድሜው ያለፈበት ተማሪ ከዓመታት በኋላ ዕድሜው ለትምህርት ከሚደርስ ተማሪ ጋር እኩል ለመማር ይገደዳል:: ይህም ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጫና በመዳረግ በራስ መተማመን የሌለው ድንጉጥ እና ፈሪ ትውልድ እንዲፈጠር በር ይከፍታል:: ከዚህ ባሻገር ግን ሥነ ልቦናዊ ጫናው በፈጠረው የአመለካከት እና የአስተሳሰብ መዛባት ምክንያት በተማሪዎች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር በማድረግ ያከተመው ግጭት ዳግም እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሊሆን ይችላል::
አንጻራዊ ሰላም የሰፈነባቸው አካባቢዎችን እየለዩ በፍጥነት ትምህርት ማስጀመር በግጭት ውስጥ የቆዩ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ሌላው ኅብረተሰብ ከቁዘማ ወጥቶ መደበኛ ሕይወቱን እንዲመራ፣ ወደ ፊትም ግጭት እንዳይፈጠር ለመሥራት ያመቻል::
በኢትዮጵያም አሁን ላይ አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል:: እናም ሀገሪቱ ልክ እንደ ኮስታሪካ ሁሉ ትምህርትን የዘላቂ ሰላም ዋነኛ መንገድ አድርጋ መጠቀም ይገባታል:: ይህ ሲሆን ዘላቂ ሰላም ተፈጥሮ ሀገርን ወደ ከፍታ የሚያወጡ ዜጎችን ቁጥር ማብዛት፣ ነገሮችን በውይይት እና ንግግር የመፍታት ጥበብን ማዳበር ይቻላል::
ለዚህም ዛሬ ላይ ከትምህርት ውጭ የሆኑ ዜጎች ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰው ትምህርታቸውን ያለምንም ስጋት እንዲማሩ ቅድሚያ ሁሉም ስለ ሰላም መሥራት፣ ዘብነቱንም ማሳየት ይገባዋል:: የነገ ችግሮቻችን በውይይት የመፍታት ስኬታችንን ዛሬ ላይ መጀመር፣ አሁናዊ ግጭቶችም በሰላማዊ መንገድ መቋጫ እንዲያገኙ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ከመንግሥትም ሆነ ከታጣቂ ኀይሎች ይጠበቃል:: ሕዝቡም ለልጆቹ የነገ እጣ ፈንታ ሲል ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ የሚጠበቅበትን ጫና ሊፈጥር ይገባዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም